የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ከተጀመረ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል

በርካታ ግቦችን እያስተናገደ የሚገኘው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑ ላይ ደርሷል። ትላንት ኢትዮጵያ በኬኒያ 2-0 ስትሸነፍ ዩጋንዳም ከደርዘን በላይ ግብ አስቆጥራ ጅቡቲን ረታለች፡፡

ስምንት ሀገራትን በሁለት ምድብ ከፍሎ እያሳተፈ የሚገኘው ይህ ውድድር ከትላንት በስቲያ ከምድብ ሁለት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀመር ቡሩንዲ ዛንዚባርን 5-0፤ በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ታንዛኒያ ደቡብ ሱዳንን 9-0 መርታት ችለዋል። ምድቡን ከቡሩንዲ እኩል ሶስት ነጥቦች ብትይዝም አስተናጋጇ ሀገር ታንዛኒያ በግብ ክፍያ በመብለጥ መምራት ጀምራለች፡፡

ትላንት ከምድብ አንድ ሁለት ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ ቀን 8:00 ውድድሩ እየተደረገ በሚገኝበት ቻማዚ ስታዲየም ኢትዮጵያ ኬኒያን ገጥማ ሽንፈትን ቀምሳለች፡፡ ሳቢ ባልሆነው እና ረጃጅም ኳሶችን ብቻ በተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለምንም ግብ ለእረፍት የወጡ ሲሆን ከእረፍት መልስ የሀራምቤ ክየከዋክብት የሉሲዎቹን የመከላከል ስህተት ተጠቅመው ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡

77ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ቶፒስታ ሲቱማ ለማሻማት ስሞክር ተከላካየዋ መስከረም ካንኮ በእጅ ነክታለች በማለት የእለቱ ዳኛ የሰጠችውን የፍፁም ቅጣት ምት አጥቂዋ ጀንትሪክ ቪካንጎዋ ወደ ግብነት በመለወጥ ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡ ሆኖም ኳስን መስረተው ለመጫወት ሲሞክሩ እና የቅብብል ስህተት ሲስተዋልባቸው የነበሩት ሉሲዎቹ በዚሁ ስህተታቸውን በመጠቀም አማካዩዋ ሲቲያስ ሙሱንጉ ከሩት ኢንጎሲ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብላ ተከላካዮቹን በማለፍ ሲቲያስ ሙሱንጉ ሁለተኛው ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በኬኒያ 2-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

በኢትዮጵያ ኬኒያ ምድብ ውስጥ የሚገኙት ዩጋንዳ እና ጅቡቲ 10:00 ላይ ባደረጉት ጨዋታ ጠንካራዋ ኡጋንዳ በጅቡቲ ላይ በርካታ ግቦችን አስቆጥራ 13ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ምድቡን በበላይነት መምራት ጀምራለች ፡፡ በጨዋታው ላይ አጥቂዋ ናሉኬንግ ጁሌት አራት ግቦችን ስታስቆጥር ኡኩዋፑት ፋአዚላ ደግሞ ሶስት ግቦችን ለዩጋንዳ ማስቆጠር ችላለች፡፡

ዛሬ በመክፈቻው ጨዋታቸውን ማድረግ የቻሉት የምድብ ሁለት ቡድኖች ሁለተኛ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑ ሲሆን 8:00 ደቡብ ሱዳን ከ ዛንዚባር በ10:00 ደግሞ ቡሩንዲ ከ ታንዛኒያ ይጫወታሉ፡፡ ነገ ደግሞ 8:00 ኬንያ ከ ጅቡቲ፣ በ10:00 ዩጋንዳ ከ ኢትዮጵያ የሚጫወቱ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ