​ሴካፋ 2017፡ ኢትዮጵያ ነገ ቡሩንዲን ትገጥማለች

ኬንያ እያስተናገደችው ባለው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ከአንድ ቀን እረፍት በኃላ ሐሙስ ቀጥለው ሲደረጉ ኢትዮጵያ በቡኩንጉ ስታዲየም ቡሩንዲን ትፋለማለች፡፡
ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳንን 3-0 በመርታት ለጨዋታው ስትቀርብ ቡሩንዲ በበኩሏ ዩጋንዳን ነጥብ አስጥላ ወደ ጨዋታው ታመራለች፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታው እንዲረዳው ዛሬ ከ4፡00 ሰዓት ጀምሮ ለ45 ደቂቃ የቆየ ቀለል ያለ ልምምድ በካካሜጋ ትምህርት ቤት ሜዳ ሰርቷል፡፡ ብሄራዊ ቡድን ደቡብ ሱዳንን ከረታበት ጨዋታ በኃላ በቀናት ልዩነት የሚያደርገው ጨዋታ በመሆኑ በተወሰነ መልኩ የተጫዋቾች ለውጥን ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በዛሬው ልምምድ ላይ አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ በመጠነኛ ጉዳት እረፍት ተሰጥቶት ያልተሳተፈ ሲሆን ለነገው ጨዋታ መድረሱ ነገር 50/50 ነው ተብሏል፡፡

የዋሊያዎቹ ተጋጣሚ ቡሩንዲ በመጀመሪያው ጨዋታ በጥብቅ መከላከል እና ፈጣን መልሶ ማጥቃት ዩጋንዳን መፈተን ሲችሉ ስሙ ከአንጎላ ክለቦች ጋር የተያያዘው ፊስቶን አብዱልራዛክ እና በክረምት 2009 ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመራል ተብሎ ሲጠበቅ የበረው የሲምባው አጥቂ ላውዲት ማቩጎ ጥምረት ላይ ተማምነዋል፡፡ ማቩጎ በ2015 ብሩንዲ ኢትዮጵያን በቻን ማጣሪያ ቡጁምቡራ ላይ 2-0 ስታሸንፍ ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት በጉዳት እና ጉልበት የጨረሱ ተጫዋቾችን ከጫና ነፃ ለማድረግ የተወሰኑ ለውጦች በጨዋታው ላይ ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ “ተጫዋቾቻችን አንድ ቀን ብቻ አርፈው ነው የሚጫወቱት፡፡ ይህ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ከደቡብ ሱዳን ጋር ይዘናቸው የገባናቸው ልጆች ጥሩ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡ እነዚህ ልጆች እንዳለ ይዞ መግባቱ ጉልበታቸውን ስለጨረሱ እንዳለ ፈታኝ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ መጠነኛ ጉዳት ያስተናገዱ አሉ፡፡ የሚያሳስቡን ነገሮች ናቸው ግን ከሙያ ጓደኞቼ ጋር ተመካክረን ለጨዋታው እንቀርባለን፡፡” ዋሊያዎቹ በመጀመሪያው ጨዋታ ያለቀላቸውን ለመቁጠር የሚያዳግቱ የግብ እድሎች ሲያመክኑ የተመለከትን ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ  ተጫዋቾቹ ግዜ እንዲሰጣቸው እና የግብ ማስቆጠር ችግሩ በሂደት እንደሚቀረፍ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

ማቻኮስ ላይ በምድብ አንድ በኮንፌድሬሽን አንድ የሆኑት ታንዛኒያ እና ዛንዚባር እንዲሁም አጣብቂኝ ውስጥ የገባቸው ሩዋንዳ ከተጋባዧ ሊቢያ ይጫወታሉ፡፡ ዛንዚባር ማክሰኞ ሩዋንዳን 3-1 በመርታት ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያሳካች ሲሆን ታንዛኒያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ነጥብ ጥላለች፡፡ ሩዋንዳ ነገ ከሊቢያ ላይ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ካልቻለች ከምድብ መሰናበቷን ታረጋግጣለች፡፡ ምድቡን ኬንያ በአራት ነጥብ ስትመራ ዛንዚባር በሶስት እንዲሁም ሊቢያ በሁለት ይከተላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከብሄራዊ ቡድኑ ባሻገር በአንድ ኮሚሽነር እና ረዳት ዳኛ እየተወከለች ትገኛለች፡፡ በጨዋታ ኮሚሽነርነት አቶ አሸናፊ እጅጉ እንዲሁም የፊፋ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝ ትግል ግዛው በምድብ አንድ የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ትግል በመክፈቻ ጨዋታ ኬንያ ሩዋንዳን 2-0 ስትረታ ጨዋታውን ከመሩ አርቢትሮች መካከል ነበር፡፡

የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫን የማስተላለፍ ሙሉ መብት በገዛው የታንዛኒያው አዛም ቲቪ ላይ ጨዋታዎቹ የቀጥታ ስርጭት የቴሌቪዥን ስርጭት ያገኛሉ፡፡ የክፍያ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነው አዛም ቲቪ በታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ቡሩንዲ የስርጭት አድማስ ሲኖረው ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ባለመግባቱ በሃገራችን ጨዋታዎች የመከታተል እድል አይኖረንም፡፡ ሴካፋ የሱፐርስፖርት ከኬንያ መውጣትን ተከትሎ ለጨዋታዎቹ የቴሌቭዥን ስርጭት ለማግኘት ሲቸገር ተስተውሏል፡፡

ሰኞ ህዳር 25

ዩጋንዳ 0-0 ቡሩንዲ

ማክሰኞ ህዳር 26

ዛንዚባር 3-1 ሩዋንዳ

ኢትዮጵያ 3-0 ደቡብ ሱዳን

ኬንያ 0-0 ሊቢያ

ሐሙስ ህዳር 28

8፡00 – ታንዛኒያ ከ ዛንዚባር (ማቻኮስ)

9፡00 – ኢትዮጵያ ከ ብሩንዲ (ካካሜጋ)

10፡00 – ሩዋንዳ ከ ሊቢያ (ማቻኮስ)

አርብ ህዳር 29

9፡00 – ዩጋንዳ ከ ደቡብ ሱዳን (ካካሜጋ)

ቅዳሜ ህዳር 30

8፡00 – ሩዋንዳ ከ ታንዛኒያ (ማቻኮስ)

10፡00 – ኬንያ ከ ዛንዚባር (ማቻኮስ)

እሁድ ታህሳስ 1

9፡00 – ኢትዮጵያ ከ ዩጋንዳ (ካካሜጋ)

ሰኞ ታህሳስ 2

8፡00 – ሊቢያ ከ ዛንዚባር (ማቻኮስ)

9፡00 – ደቡብ ሱዳን ከ ቡሩንዲ (ካካሜጋ)

10፡00 – ኬንያ ከ ታንዛኒያ (ማቻኮስ)

የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ በሶከር ኢትዮጵያ እንዲቀርብ ያስቻለው ጎ ቴዲ ስፖርት ነው፡፡ ጎ ቴዲ ስፖርት በኢትዮጵያ የማራቶን ትጥቆች ወኪል አከፋፋይ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *