የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ በኬንያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

በታንዛንያ አስተናጋጅነት ሲደረግ የቆየው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ዛሬ ሲጠናቀቅ ኬንያ አዘጋጇ ታንዛንያን በማሸነፍ የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች፡፡

ከፍፃሜው አስቀድሞ 7:30 ላይ ዩጋንዳን ከቡሩንዲ ያገናኘውን የደረጃ ጨዋታ ዩጋንዳ 2ለ0 በማሸነፍ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች፡፡

ቀጥሎ ለዋንጫ 10:30 ላይ አዘጋጇ ታንዛኒያን የገጠመችው ኬንያ 2-0 አሸንፋለች። ኢትዮጵያውያኑ ወጋየው ዘውዴ (በረዳት ዳኝነት) እና አስናቀች ገብሬ (በአራተኛ ዳኝነት) በተሳተፉበት በዚህ ጨዋታ በውድድሩ ላይ ጥንካሬዋን በጉልህ ያሳየችው ኬንያን አሸናፊ ያደረጉ ጎሎችን ጀንትሪክ ሺካንግዋ በ71ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት እና በ88ኛው ደቂቃ በጨዋታ ማስቆጠር ችላለች።

ከጨዋታው ፍፃሜ በመቀጠል የኮከቦች ሽልማት የተካሄደ ሲሆን ጀንትሪክስ ሺካንግዋ ከኬንያ በአስር ግቦች በውድድሩ ከፍተኛ ግብ አግቢነት ተሸልማለች። ምዋናሀሚሲ ኦማሪ ከታንዛኒያ ኮከብ ተጫዋች እንዲሁም ውድድሩን አንድም ግብ ሳታስተናግድ የፈፀመችው የኬንያዋ አኔዲ አንዴይ ምርጥ ግብ ጠባቂ በመባል ተሸልማለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ