የህክምና ባለሙያው ከተለመደው ሚና ውጪ..

ትናንት ጅማሮውን ባደረገው የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለወትሮው ከተለመደው ውጪ የህክምና ባለሙያውን በሌላ ሚና መመልከት ችለናል።

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ ያደረጉት የሊጉ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያለ ጎል በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። ታዲያ በጨዋታው እንቅስቃሴ ላይ የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ጉዳት አስተናግደው የህክምና ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ወቅት አንድ ትኩረት የሚስብ ነገር ተደጋግሞ መመልከት ችለን ነበር።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የህክምናው ባለሙያው ሽመልስን ከተለመደው ሙያዊ አገልግሎቱ ውጭ በቅርብ ርቀት ተጫዋቾችን አግኝተው ማረም ያልቻሉትን ነገር በህክምና ባለሙያው በኩል መልዕክት ሲያስተላልፉ ተመልክተናል።

ይህ እምብዛም በሊጋችን በግልፅ ያልተለመደው ተግባር እንዴት እየሰሩበት እንደሆነ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን አናግረናቸው ይሄን ብለውናል።

” የህክምና ባለሙያ በአንድ ክለብ ውስጥ የቴክኒክ ክፍሉ አባል ነው። ስለ ተጫዋቾች አሰላለፍ ስታወጣ እና ሌሎች ነገሮችን ማድረግ ስትፈልግ ከህክምና ባለሙያው ጋር አስቀድመህ ትነጋገራለህ። ለምሳሌ ትናንት ሱራፌል ህመም ስለነበረው እረፍት ላይ ነበር ማሳረፍ ፈልጌ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ተጫዋቾች ህመም እየተሰማቸው ቡድኑን ለማገልገል ሲሉ ሜዳ ላይ መቆየት ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ ቡድኑ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አለው። በዚህ ሰዓት ነው የህክምና ባለሙያው ሽመልስን ‘ስትሄድ ህመሙ ከከፋበት ተቀይሮ እንዲወጣ በግልፅ ንገረው’ በማለት የላኩት። በተጨማሪ ሜዳው ውስጥ ተጫዋቾችህ አለመረጋጋት ፣ አለመናበብ እና ስሜታዊ ሲሆኑ የጨዋታው እንቅስቃሴ በጉዳት ምክንያት ሲቋረጥ ተጫዋቾቹን ወደ እኔ ጠርቼ እስካናግር ድረስ በሆነ አጋጣሚ የጨዋታው እንቅስቃሴ ቢጀምር ማስተላለፍ የምፈልገውን መልክት ሳላደርስ ልቀር በመሆኑ የህክምናው ባለሙያ የእያንዳንዱን ተጫዋች ስብዕና ባህሪ በቅርብ ርቀት የሚረዳ በመሆኑ ከህክምናው ባሻገር እግረ መንገዱን የምትፈልገው መልዕክት ሜዳ ውስጥ ነግሮልህ ይወጣል።

“ይህ የመልክት ማስለተላለፍ መንገድ ድሮም ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለው (ነፍሱን ይማረውና) ዘላለም አዱኛ ያደርግልኝ ነበር። እንዲያውም በጣም ከመልመዱ የተነሳ እንዳዴ ‘ኮች የምነግርልህ ነገር አለ?’ ይለኝ ነበር። ምክንያቱም ሜዳ ውስጥ ከእኛ በተሻለ ለተጫዋቾቹ ቅርብ ናቸው። ስለዚህ ይህን መጠቀምህ ሥራህን ስለሚያቀልልህ ከዛ አኳያ ነው ይህን መንገድ በተደጋጋሚ እከተል የነበረው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ