በዮናታን ሙሉጌታ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአንድ ወር መቋረጥ በኋላ የስምንተኛ ጨዋታዎቹ ቀጥለው ሲካሄዱ ማክሰኞ ምሽት የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከሊጉ መሪ አዳማ ከተማ ያለውን የነጥብ ርቀት አጥብቧል፡፡ የጨዋታውን እንቅስቃሴም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች የጨዋታ አቀራረብ
ባለሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ4-3-3 ፎርሜሽን ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን በምስሉ ላይ እንደተመለከተው በመሀል ሜዳ ላይ አሉላ ግርማን ከምንተስኖት አዳነ ጋር በማጣመር ከሁለቱ ፊት እና ከአጥቂዎቹ ጀርባ ባለው ቦታ ላይ ደግሞ አዳነ ግርማን በጨዋታ አቀጣጣይነት (play maker) ሚና ተጠቅሟል፡፡ ከሁለቱ የመሀል አማካዮች አሉላ ወደፊት እየተጠጋ የመጫወት እንዲሁም ምንተስኖት ለተከላካይ መስመሩ ሽፋን የመስጠት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ የቡድኑ ዋና ጥንካሬ ተደርገው በሚወሰዱት የግራና የቀኝ መስመሮች ላይ ራምኬል ሎክን እና በበኃይሉ አሰፋ መጎዳት ምክንያት በቦታው የተተካውን አቡበከር ሳኒን አሳልፏል፡፡
የመሳይ ተፈሪው ወላይታ ድቻ በአብዛኛው ከሚታወቅበት የሦስት ተከላካዮች (Back three) አጨዋወት ወደ 4-4-2 የተቀየረ ሲሆን ይህም አደገኛ ለሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ከመስመር ለሚነሳው የማጥቃት እንቅስቃሴ መፍትሄ ለማበጀት የተደረገ ይመስላል፡፡ በአማካይ ክፍል ላይም ቡድኑ አማኑኤል ተሾመንና ወንድማገኝ በለጠን ሲያጣምር በአመዛኙ አለማየሁ ኳስ የማስጣሉን ሚና እየተወጣ እንዲሁም ወንድማገኝ ኳስ የማደራጀትና የአማካይ ክፍሉን ከአጥቂዎቹ ጋር የማገናኘት ሥራን እንዲሰራ የታሰበ ይመስላል፡፡ሁለቱ የቡድኑ የመስመር አማካዮች ሰለሞን ሀብቴና ፀጋ አለማየሁም በመከላከልም በማጥቃትም ጊዜዎች እንደየሽግግሩ የቡድኑን ሚዛናዊነት የመጠበቅ ሚና ነበራቸው፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ
ሁለቱ ቡድኖች ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ ባደረጉበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳስን ከኋላ መስርተው እየተጫወቱ ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ግማሽ ድረስ በመግባት ከዚያም የኳሱን ፍሰት ወደ ሁለቱ ክንፎች በመውሰድ ከመስመር አጥቂዎቻቸው በሚነሱ ኳሶችቨየግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ በዚህም አጨዋወት በጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃወች በግራ በኩል ተሰልፎ ከነበረው ራምኬል ሎክ በኩል የተወሰኑ የማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ችለው ነበር፡፡ ነገር ግን 20ኛው ደቂቃ አካባቢ ራምኬል ሎክ እና አቡበከር ቦታ ተቀያይረው እስከ መጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ድረስ አቡበከር በግራ ራምኬል ሎክ በቀኝ ሆነው ቢጫወቱም በ40ኛው ደቂቃ አካባቢ ራምኬል ሎክና አዳነ ግርማ ለብሪያን ኡሙኒ የፈጠሩለትና ያልተጠቀመበት አጋጣሚ ይጠቀስ እንደሆነ እንጂ በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ባለ ሜዳዎቹ ሌላ ይህ ነው የሚባል የሚያስቆጭ አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አስፈሪነት የሚጀምረው ኳስ የመስመር አጥቂዎች እግር ስር ስትደርስ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት የመሀል አማካዮች በተለይም ወደፊት ተጠግቶ ለመጫወት ይሞክር የነበረው አሉላ ግርማ እና በትላንቱ ጨዋታ የplay maker ሚና የነበረው አዳነ ግርማ ኳስን ከተከላካዮቹ ተቀብሎ በመሀል ሜዳ ላይ ኳስን የማደራጀት ብቃታቸው አናሳ መሆኑ ቡድኑ በቂ እድሎችን እንዳያገኝ አድርጐታል፡፡ ለዚህ ሁኔታ የሁለቱ ተጨዋቾች ሚና ከተፈጥሮአዊ አጨዋወታቸው ጋር የማይጣጣም መሆኑ፣ እንዲሁም ከመስመር አጥቂዎቹም ሆነ በእለቱ በአብዛኛው በመከላከሉ ላይ ያመዝኑ ከነበሩት የመስመር ተከላካዮች በቂ እገዛ አለማግኘታቸው እንደምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በተለይ አዳነ ግርማ ወደኋላ እየተሳበ ኳስን ለመቀበል ጥረት ያደረገባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም በተደጋጋሚ አጋጣሚዎች ከመጨረሻ አጥቂው ብሪያን ኡሙኒ ጋር ሲደረብ አልፎ አልፎም ከብሪያን ኡሙኒ ፊት ሲገኝ እና ቡድኑ ከፊት አራት አጥቂዎች ያሉት ሲያስመስለው ክብሰትሁላመ እስከ ሁለቱ የመሀል አማካዮች ምንተስኖት እና አሉላ ድረስ ሰፊ ክፍተት የታየ ነበር፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ ጊዮርጊሶች ያሳዩት ይህ የተዳከመ የመሀል ሜዳ እነቅስቃሴ በተጋጣሚያቸው የበላይነት እንደወሰድባቸው አድርጐም ነበር፡፡ ወላይታ ድቻዎች በሚከላከሉበት ጊዜ በተለይ በተከላካይ እና በአማካይ መስመራቸው መሀል (between the lines) ለተጋጣሚያቸው ክፍተት ባለመስጠት የተሻሉ ነበሩ፡፡ ይህም ለጊዮርጊሶች የሳሳ የመሀል ክፍል የተሳካ የኳስ ፍሰት ለመፍጠር አስቸጋሪ እንዲሆንበት አድርጓል፡፡ ድቻዎች ተጋጣሚያቸው በሚያጠቃበት ሰዓት በተቻለ መጠን ከሁለቱ አጥቂዎቻቸው በቀር ሌሎቹ ተጨዋቾች ከኳስ ጀርባ በመሆን እና ኳስን በማስጣል በፍጥነት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የጨዋታ አጋማሽ ለመድረስና ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረዋል፡፡ የወላይታ ድቻ የማጥቃት አጋጣሚዎች ይፈጠሩ የነበሩት በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የግራ መስመር አማካይ ከነበረው ሰለሞን ሀብቴ እንዲሁም የቀኝ መስመር ተሰላፊው ፀጋ አለማየሁ የተሻለ ሊባል በሚችል መልኩ የማጥቃት ተሳትፎ ከነበረው የቀኝ መስመር ተከላካዩ አናጋው ባደገ ጋር በሚፈጥረው ጥምረት ነበር፡፡ እነዚህን ፈጠን ያሉ እነቅስቃሴዎች ለመግተት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ወላይታ ድቻዎች በርከት ያሉ ቅጣት ምቶችን በማግኘት ከቆሙ ኳሶች አድሎችን ፈጥረዋል፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ የወላይታ ድቻን ቡድን ምንም እንኳን የመሀል ሜዳ የበላይነት የነበረው ቢሆንም ነገር ግን የመጨረሻ የጐል ማግባት እድሎችን ለሁለቱ አጥቂዎች መፍጠር አቅቶት ጐል ሳያስቆጥር ወደ መልበሻ ቤት ለመመለስ ተገዷል፡፡ ነገር ግን በሁለቱም መስመሮች በኩል የተጋጣሚያቸውን ዋነኛ የማጥቃት አማራጮች በመዝጋት እንዲሁም ከመሀል በሚነሱ ኳሶችም አደጋ እንዳይጋረጥባቸው በማድረጉ በኩል ተሳክቶላቸው ነበር፡፡
የሁለተኛው አጋማሽ
ጊዮርጊሶች በሁለተኛው አጋማሽ የመሀል ሜዳውን ሚዛን የሚያስጠብቅላቸውን ወሳኝ ቅያሬ አድርገው ወደ ሜዳ ተመልሰዋል፡፡ የግራ መስመር ተከላካዩን ዘካሪያስ ቱጂን አስወጥተው የተከላካይ አማካዩ ተስፋዬ አለባቸውን ቀይሮ በማስገባት አሉላ ግርማን ወደ ተፈጥሮአዊ ቦታው ወደ ቀኝ መስመር ተከላካይነት በመመለስ እንዲሁም በቀኝ መስመር ተከላካይነት ተሰልፎ የነበረውን አንዳርጋቸው ይላቅን ወደ ግራ መስመር በማዘዋወር ነበር ጊዮርጊሶች ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት፡፡ በድቻዎች በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ ቴዎድሮስ መንገሻን ጉዳት ባጋጠመው አጥቂ በዛብህ መልዩ ከተኩበት ቅያሬ በቀር ተጨማሪ ተጨዋች ሳይቀይሩ ተመልሰዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታውን ሂደት የለወጡት ሁለት አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ጨዋታው እንደተጀመረ በ47ኛው ደቂቃ የተገኘችውና በአዳነ ግርማ አማካይነት የተቆጠረችው ፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም የወንድማገኝ በለጠ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለተኛው አጋማሽ ያደረጉት ቅያሬ፡፡ እነዚህ አጋጣሚዎች ለጨዋታው ሌላ መልክ አላብሰውታል፡፡ ፈረሰኞቹ በተጋጣሚያቸው ላይ ያገኙት የቁጥር ብልጫ የተሻለ የመሀል ሜዳ የበላይነት ሰቷቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ቡድኑ አሁንም የፈጣሪ አማካይ የማጣት ችግሩ የሚገባውን ያህል የበላይነት ወስዶ የጐል እድሎችን እንዳይፈጥር አድርጐታል፡፡ ወላይታ ድቻዎች የአዳነ ግርማ በግል ጥረቱ ከሳጥናቸው ውጪ ድንቅ የሆነችውን ጐል ካስቆጠረባቸውም በኋላም ለማጥቃት ከመሞከር አልቦዘኑም፡፡ በውንድምአገኝ መውጣት የተፈጠረውን ክፍተት ፀጋ አለማየሁን በመሳይ አጪሶ በመተካት እንዲሁም በድሉ መርዕድን በሰለሞን ሀብቴ በመቀየር ተጋጣሚያቸው ኳስ ሲይዝ ሙሉ ለሙሉ በራሳቸው አጋማሽ ላይ በመከላከል እንዲሁም የማጥቃት ክፍተት ሲያገኙ ወደተጋጣሚ አጋማሽ በፍጥነት ለመግባት በሚሞክሩት ሁለቱ አጥቂዎቻቸው ኳስ ለመጣል እድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ በቡድናቸው የመስመር አጠቃቅ ያልረኩት የሚመስሉት የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ማርቲን ዎይ ሁለቱን የመስመር አጥቂዎች በተደጋጋሚ ቦታ እያቀያየሩ ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ በኋላም ዳዋ ሂጤሶን ና ናትናኤል ዘለቀን በሁለቱ የመስመር አጥቂዎቻቸው አቡበከር ና ራምኬል ሎክ በመቀየር ዳዋ የግራ መስመሩን እነዲይዝ አድርገው አዳነን የፊት አጥቂ በማድረግ ብሪያን ኡሙኒን ወደ ግራ መስመር አውጥተውታል፡፡ ሶስተኛውም ጐል ከዚህ ቅያሬ በኋላ በብሪያን አማካኝነት ተቆጥራለች፡፡
ጨዋታው የበለጠ ክፍት በነበረበት የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ምናልባትም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ሲገኙ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ በቁጥር በመብለጥና እድሎችን ለመፍጠር በማሰብ በሚመስል ሁኔታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሰላፊዎች በግልፅ ሁለት ቦታ ተከፍለው ይታዩ ነበር፡፡ ድቻዎች ለማጥቃት ወደፊት በሚሄዱበት ጊዜ የጊዮርጊስ ሦስቱ የፊት አጥቂዎችና እንዲሁም የአጥቂ አማካዮች ከአራቱ ተከላካዮችና ከሁለቱ የመሀል አማካዮች በሩቅ ተነጥለው በመሀል ሜዳው አጋማሽ ላይ ሲቆሙ ለመመልከት በጣም ቀላል ነበር፡፡ ይህ አይነለቱ አጨዋወት ምናልባት ወላይታ ድቻዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲቋረጥ ለመልሶ ማጥቃት አመቺ ይሁን እንጂ በመከላከሉ ረገድ ግን እንደ ትልቅ ክፍተት የሚታይ ነው፡፡ ምናልባትም በአስር ተጨዋቾች ጨዋታውን እንዲጨርሱ መገደዳቸው ተጫዋቾች ሰፊውን የሜዳ ክፍል አካለው እንዲጫወቱ ስላደረጋቸውም እና አድካሚም በመሆኑ ወላይታ ድቻዎች ከመከላከል ወደማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር ፍጥነት አልባ ሆኗል ይህም ለብቻው ተቆርጦ ይቀር የነበረውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ክፍል ሰብሮ ለመግባት እና ቢያንስ ወጤቱን ለማጥበብ በቂ የጎል እድሎችን እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ በጥቅሉ የትናንቱ ጨዋታ ላሸናፊው ቡድን ተፈጥሯዊ አማካይ ለቡድኑ ምን ያህል ወሳኝ ንደሆነ ያመላከተ ሆኗል፡፡ በተለይም ቡድኑ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው ላይ ጠንካራ የተከላካይ ኣማካዮች እና የተከላካይ መስመር ያላቸውን ቡድኖች ለመግጠም የግድ ሰፊ እይታ ያለው ለአጥቂዎች የመጨረሻ ኳስ መስጠት የሚችል እንዲሁም የቡድኑን ሚዛን በጠበቀ መልኩ ኳስ የሚያሰራጭ አማካይ ያስፈልገዋል፡፡