ታክቲክ – ውጤታማ የሆነው የአብዱልከሪም የሚና ለውጥ (ኢትዮጵያ ቡና 2-0 ዳሽን ቢራ)

ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት መርሃ ግብር አንዱ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና ዳሽን ቢራ ጨዋታ ማክሰኞ በአበበ ቢቂላ ተካሂዶ ኢትዮጵያ ቡና ከጨዋታ ብልጫ ጋር (ዳሽን ቢራ በ90 ደቂቃ ውስጥ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የግብ ሙከራ አለማድረጉ ልብ ይሏል) በኤልያስ ማሞ እና ያቤውን ዊልያም ግቦች ታግዞ 2-0 አሸንፏል፡፡ ጨዋታውን የተመለከተው ሚልኪያስ አበራ በታክቲካዊ ትንታኔው የጨዋታውን አበይት ታክቲካዊ ሁነቶች እንዲህ አቅርቧቸዋል፡፡

የተሸሻለው የቡና የቅብብሎሽ ስኬታማነትና የተመጠነ ልኬት

በተጫዋቾች መካከል የሚደረጉ የኳስ ቅብብሎች ትክለኝነት (passing accuracy) ወሳኝ እና መሰረታዊ የእግርኳስ ስኬትማነት ቁልፍ ነው፡፡ የቅብብሎቹ ፍጥነት ፣ ልኬት እና ቅብብሎቹ የሚደረጉበት የጨዋታ ሒደቶች (Phases) ከውጤታማ የኳስ ቅብብሎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ በአመዛኙ ቅብብሎች ትክክለኛነት እና ምጣኔ ሲጎድላቸው ይስተዋላል፡፡ በእግርኳሳችን ቅብብሎች ያላቸው ዋጋ እምብዛም ቦታ ሲሰጠውም አይታም፡፡ ኳስን ከአንድ ተጫዋች ወደ ሌላኛው ከማሸጋገርና ወደፊተኛው መስመር በፍጥነት ለማድረስ በበለጠ ጥራታቸው እና ታክቲካዊ ጠቀሜታቸው ላይ ያመዘነ ምልከታ ሲደረግባቸው አልተለመደም፡፡

በዘመናዊው እግርኳስ በተጫዋቾች መካከል የሚደረጉ ስኬታማ ቅብብሎች መጠነ ሰፊ ታክቲካዊና ቴክኒካዊ ጠቀሜታዎች ይይዛሉ፡፡ የተጋጣሚን የጨዋታ ዘይቤ ለመታዘብ ፣ የተጠቀጠቀ የባላጋራ የመከላከል አደረጃጀት ለማስከፈት ፣ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለመያዝ ፣ የፈጠራ ክህሎታቸው የላቁ ተጫዋቾችን የመፍጠር ጊዜ እና ነፃነት እንዲሁም ቦታ ለመስጠት እና የመሳሰሉትን በሜዳ ላይ የሚገኙ የውጤታማ ቅብብል ፋይዳዎች ናቸው፡፡ ተመልካችን ለማዝናናት እና ማራኪ አጨዋወትን ለማሳየትም ይኸው የቅብብል ጥራት አይነተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡

በአበበ ቢቂላ ስታድየም ከቡና አዎንታዊ ጎኖች አንዱ እና ለድላቸው አይነተኛውን ሚና የተጫወተላቸውም ልኬቱ የተስተካከለ እና የተመጠነ ተደጋጋሚ ቅብብሎችን መከወኑ ነው፡፡ የቡና ተጫዋቾች የሚያደርጓቸው ቅብብሎች የታሰበላቸውን ተጫዋቾች ያማከሉ ነበሩ፡፡

በ4-2-3-1 ፎርሜሽን ጨዋታውን ሲያደርግ ለነበረው ኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ አማካዮቹ ኤርሚያስ በለጠ እና አብዱልከሪም መሃመድ በቡድኑ የማጥቃት እና የመከላከል አጨዋወት ላይ መጠነኛ እና አንፃራዊ ሚዛናዊነትን ሲፈጥሩ ነበር፡፡ የመጀመርያ ጨዋታውን ለኢትዮጵያ ቡና ያደረገው ኤርሚያስ ብዙም ላልተዋሃደው የወንድይፍራው ጌታሁን እና ኢኮ ፊቨር ጥምረት ሽፋን ከመስጠቱም በላይ በጎንዮሽ እንቅስቃሴ (lateral movement) በአህመድ ረሺድ እና እያሱ ታምሩ ለሚመራው ጠንካራ የማጥቃት መስመር ላይ ከለላ ሲሆን ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኤርሚያስ ጨዋታን ቀድሞ የመረዳት ብቃት ከጎኑ ለነበረው እና የሳጥን – ሳጥን (Box – Box) አማካይነት ሚናን ሲወጣ ለነበረው አብዱልከሪም የፊትለፊት የማጥቃት እንቅስቃሴ የራስ መተማመን ከፍ ያደረገ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በመጀመርያው አጋማሽ በ28ኛው ደቂቃ ላይ በኤልያስ ማሞ አማካኝነት ያገኛት ጎል በሜዳው ቁመት ከመሃለኛው ክፍል በተነሳ የአጭር ቅብብሎሽ ተደጋጋሚ ሂደት ነበር፡፡ በብቸኛ አጥቂነት የተሰለፈው ያቤውን ዊልያም በሳጥን ውስጥ ቆሞ እንዳይነጠልና ከማጥቃት አማካዮቹ ጋር ያለውን ርቀት ወደኋላ እየተመለሰ የጨዋታው አካል ለመሆን የሚያደርገው ጥረት ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡

ከእረፍት መልስ በ83ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ራሱን ነጻ አድርጎ ከኤልያስ የተቀበለውን ኳስ ያለምንም እንከን ወዶልነት የቀየበት መንገድም የሚያስወድሰው ሊሆን ይገባዋል፡፡ ወደ ደካማው (በመከላከል ሒደት) መስመር እየሄደ የዳሽኑን የቀኝ መስመር ተከላካይ ያሬድ ዘውድነህ የመከላከል አቅም ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ አቋም ሲያሳይ ነበር፡፡ ይህንን ድክመት ለመጠቀም በሚመስል መልኩ በተደጋጋሚ ወደ ቀኝ መስመር በመጠጋ የዳሽንን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት ደረገው ሙከራ መልካም የሚባል ነበር፡፡

image 2

የአብዱልከሪም ተጽእኖ

ኢትዮጵያ ቡና በዚህ የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ስር ካመጣቸው አዎንታዊ ለውጦች መካከል የተለያዩ ተጫዋቾችን ከዚህ ቀደም በማይታወቁበት የመጫወቻ ቦታ አሰልፎ ከተጫዋቾቹ የተሻለውን ብቃት ማውጣት የሚቸልበትን መንገድ መዘርጋቱ ነው፡፡

በቀኝ መስመር ተከላካይነቱ በይበልጥ የሚታወቀው አብዱልከሪም በዚህ ጨዋታ ከሁለቱ የተከላካይ አማካዮች ወደ ግራ ባደላው አቋቋም አስደናቂ አቋሙን አሳይቷል፡፡ የሳጥን-ሳጥን (Box-Box) ኃላፊነትን በመወጣት እና በለመደው የግራ መስመር የአግድሞሽ ሩጫ በማድረግ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት በእጅጉ ሲያግዝ ታይቷል፡፡ በሜዳው ቁመት የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በቡና ስር ሲሆን ይበልጥ በሜዳው የግራ ክፍል በሁሉም ክልሎች በመገኘት የመቀባበያ አማራጮችን በመፍጠር የጨዋታውን ፍሰት የሚጠብቅበት መንገድ የተለየ ነበር፡፡ ቡና በሚያጠቃበት ሰዓት ግዜውን የጠበቀ የፊት ለፊት ሩጫው እና ቦታ አጠባበቁ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራወች እንዲያደርግ አግዞታል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ላይ ከዳሽን የጎል ክልል (ከሳጥን ውጪ) በረጅሙ የሞከራት ኳስ አግዳሚውን ታካ ወጥታለች፡፡

የዳሽን አጨዋወት ድክመት መሰረቶች

ዳሽን ቢራ በሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጥሩ አቋም ማሳየት አልቻለም፡፡ የቡድኑ ተጫዋቾች የቦታ አያያዝ እንቅስቃሴም በአስከፊ ሁኔታ የተጠና አልነበረም ማለት መድፈር ሊሆን አይችልም፡፡ አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ወደ 4-3-3 የተጠጋ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን ቢጠቀሙም የተጫዋቾቹ እንቅስቃሴ እና የነበራቸው የሜዳ ውስጥ አቋም ቡድኑ ፍጹም ቅርጽ ይዞ/ጠብቆ የሚጫወት አላስመሰለውም፡፡

ዳሽን በተናጠል የተጫዋቾች ብቃትም ይሁን በቡድን የነበራቸው ብቃት እጅግ ደካማ ነበር፡፡ በሁለቱም የጨዋታ ሒደቶች (Attacking and defending phases) ሁሉም ተጫዋቾች ማለት ይቻላል የነበራቸው አቋም ሲበዛ ደካማ ነበር፡፡

በአብዛኛው ልምደ ብዙ ተጫዋቾች ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ ተጫዋቾችን ያቀፈው ዳሽን በዕለቱ ጨዋታ ሲጫወትበት የነበረው ቅርጽ ተከላካዩ ፣ አማካዩ እና አጥቂው ክፍል በሜዳው ቁመት እጅግ ተራርቆ እና በእያንዳንዱ ተጫዋች መካከል የሚገኘው የጎንዮሽ ክፍተት እጅግ ሰፍቶ ተመልክተናል፡፡

በተከላካይ መስመሩ ላይ በተለይ በቀኙ ክፍል ያሬድ ዘውድነህ በጨዋታው የነበረው እንቅስቃሴ ግራ አጋቢ ነበር፡፡ በተጠና የጨዋታ ሒደት ላይ ያልተመሰረተው የፊት ለፊት ሩጫ (overlapping run) ግዜውን ያልጠበቀ በመሆኑ በቅርቡ ካለው የመሃል ተከላካዩ ያሬድ ባየህ ጋር ያለው ክፍተት ሰፊ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ይህም የቡናው የግራ መስመር አማካይ አማኑኤል ዮሃንስ የቀኙ ክፍተትን (right-channel) በነጻነት እና በተደጋጋሚ ሲጠቀምበት ታይቷል፡፡ በዚሁ መስመር የቀኝ ሳጥን – ሳጥን የተከተለ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ምንያህል ይመርም እንዲሁ እንቅስቃሴው ውል አልባ ነበር፡፡ በመስመሮች መፍጠር የሚገባውን የቁጥር ተጽዕኖ ፣ የመከላከል ኃላፊነት እና በቀኝ መስመር የማጥቃት አጨዋወት እንዲመራ ከገባው መስፍን ኪዳኔ ጋር የነበረው የጨዋታ ግንኙነት እጅግ የተዳከመ ነበር፡፡

አሰልጣን ታረቀኝ አሰፋ በሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሶስት የተለያዩ ፎርሜሽኖችን (4-3-3 ፣ 4-2-3-1 እና 4-4-2) ለመጠቀም ቢሞክሩም በሁሉም ሲስተሞች የተጫዋቾቹ እንቅስቃሴ አመርቂ አልነበረም፡፡

ቡድኑ በሊጉ ረጅም አመት የመጫወት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ይዞ ብዙም የአጨዋወት እና የውጤት ለውጥ ማምጣት የሚችል አይመስልም፡፡ በአጠቃላይ ዳሽን ቢራ የተጠና ፣ የተደራጀ እና መሰረት ያለው የአጨዋወት ዘይቤ ያስፈልገዋል፡፡

image 3

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *