ሶከር ኢትዮጵያ ከሰዓታት በፊት ባቀረበችው ዘገባ ፈረሰኞቹ አራት ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው መቀላቀላቸውን በመግለጽ የሁለቱን ማንነት ይፋ አድርገን የነበረ ሲሆን ተጨማሪዎቹ ሁለት ተጫዋቾች እነማን እንደሆኑ አሁን ክለቡ አስታውቋል።

በዛሬው ዕለት አራት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ እንደቀላቀለ የገለፅነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሶከር ኢትዮጵያ ይፋ ካደረገቻቸው ኬልቪን ዶሴ እና አልፍሬድ ሜንሳ በተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን በአሁኑ ሰዓት በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል።
አንደኛው ተጫዋች አይቮሪያኑ ካርተር አሂሮ ነው። የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ካርተር በአሴክ ሚሞሳስ እንዲሁም በቤሩትና ኦማን ሊጎች ልምድ ያካበተ ተጨዋች እንደሆነ ተገልጿል።
ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ የኮንጎ ብራዛቪል ተወላጅ የሆነው ክሪስት ቶሉንጋ ነው፡፡ ክሪስት የ20 ዓመት ወጣት የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ሲሆን ለሀገሩ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በክለብ ደረጃ በዲያብሌስ ኖይሪስና በአልጄሪያው ፓራዱ ክለቦች ተጫውቷል፡፡

