በዛሬው የቅዱስ ጊዮርጊስ መግለጫ ምን ተባለ?

በዛሬው የቅዱስ ጊዮርጊስ መግለጫ ምን ተባለ?

በዛሬው ዕለት ቡድኑን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብር ላይ የተነሱ አንኳር ሀሳቦችን እንደሚከተለው ይዘን መጥተናል።

በአስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በፋይናንስ ማጠር ምክንያት ሲንገዳገድ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰሞኑን ያሉበትን ችግሮች መፍትሄ እየሰጠ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዛሬው ዕለትም ቡድኑን የተቀላቀሉ አራት የውጪ ተጫዋቾችን በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ለደጋፊዎች ያስተዋወቀ ሲሆን ከትውውቁ ጎን ለጎን በመድረኩ የተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮችን እንደሚከተለው ለማቅረብ እንሞክራለን።

በቅድሚያ መድረኩን የያዙት የጊዜያዊ ኮሚቴው አባል አቶ ሰለሞን መገርሳ በሽግግር ወቅት የነበረውን ሂደት አስረድተው የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ጀማል አህመድ ክለቡን ለማገዝ ስላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋል። በመቀጠል የሚድሮክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ልዩ ረዳት አቶ ዘላለም ተፈራ ደግሞ ክለቡን ለማገዝ ሚድሮክ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አንስተው በቀጣይ በቤተሰባዊነት ብቻ ሳይሆን ክለቡ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ እስከሰራ ድረስ አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ ነን ብለዋል። በቋሚነትም ክለቡን ለመደገፍ እና አብሮ ለመሆን ሚድሮክ እና ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ጀማል ቁርጠኛ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው ቡድኑ የዘንድሮውን የውድድር ዘመን ሲጀምር 14 ተጫዋቾች ለቀውበት እንደነበረና በነበረው የፋይናንስ ችግር ወሳኝ ተጫዋቾችን አጥቶ በችግር ውስጥ እንደነበሩ አውስተው የፊፋ እገዳው ከተነሳ በኋላ የመጡት ተጫዋቾች ለቡድኑ ትልቅ ጥቅም እንደሚሰጡ እምነት እንዳላቸው አመላክተዋል። አሠልጣኙ በችግሮች ውስጥ ሆነው ቡድኑን ሲያግዙ የነበሩ ወጣት ተጫዋቾቻቸውን፣ በአሁኑ ሰዓት ለቡድኑ ቴክኒካዊ ድጋፍ እያደረገ ያለውን አሠልጣኝ ሚቾ፣ ለጊዜያዊ ኮሚቴውን እንዲሁም ለሚድሮክ ኢንቨስትመንት እና አቶ ጀማልን ምስጋናቸውን ችረዋል።

ታሪካዊውን ክለብ እንዲያውቁ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገናናነት ለተጫዋቾቹ በማስረዳት ንግግራቸውን የጀመሩት አሠልጣኝ ሚቾ ከልጅነታቸው ጀምሮ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን ስሜታዊ ግንኙነት በማስረዳት በስፍራው የታደሙ እንግዶች ፊት ለተጫዋቾቹ አደራ ሰጥተዋል።

አሠልጣኝ ሚቾ አራቱ ተጫዋቾች የመጡበትን ሂደት ሲያስረዱ “በፊፋ ህግ መሰረት 2 የዝውውር መስኮቶች አሉ። በመካከል ደግሞ ነፃ ተጫዋቾችን ማስፈረም የሚቻልበት ህግ አለ። እዚህ ከመጣሁ በኋላ ከ3000 በላይ ነፃ ተጫዋቾችን አይቻለው። ካሉት ውስጥ ይሆናሉ ብዬ የማስባቸውን ለአሠልጣኝ ቡድን አቅርቤያለው። አንድ ላይ ሆነን ተመካክረን ነው አራቱን ተጫዋቾች የመረጥነው።” ካሉ በኋላ “እነዚህን ተጫዋቾች ያመጣነው ቡድኑ ውስጥ ያለውን ፉክክር ከፍ ለማድረግ ነው።” በማለት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

የቡድኑ አሠልጣኝ ፋሲል የሚቾን ሀሳብ ተከትለው “በቂ ጊዜ ባይኖርም አቅማችንን ተጠቅመን ያላቸውን ሁሉ ለመጠቀም እንሞክራለን። በተለይ ከቆሙ ኳሶች ጋር ያለውን አጠቃቀም ለማሳደግ እንዲሁም በማጥቃቱ ረገድ ያጣናቸውን ነገሮች ከእነሱ እናገኛለን ብለን እናስባለን። አራቱንም ካሉን ወጣቶች ጋር አደባልቀን በቀሪ የሊጉ ጨዋታዎች የተሻለ ነገር ለማምጣት እንሞክራለን።” ብለዋል።

በመጨረሻም በአሁኑ ሰዓት ቴክኒካዊ ድጋፍ እያደረጉ እንዳለ የተገለፀው ሰርቢያዊው አሠልጣኝ ሚቾ ከክለቡ ጋር ያላቸው መደበኛ ግንኙነትን በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው ተከታዩን ብለዋል። “ቅዱስ ጊዮርጊስ በደሜ ውስጥ ያለ ነው። በአካል ብርቅም ልቤ እዚህ ነው። ቤቴ እንደተመለስኩ ነው የምቆጥረው። አሁን ለአራት ብሔራዊ ቡድኖች ታጭቻለው። ግን ጊዮርጊስ ውስጤ ነው ያለው ፤ በዚህ የሽግግር ጊዜ ሁላችንም መተጋገስ አለብን። እኔ እዚህ ስመጣ ብቻዬን አይደለም። ያለኝን ኔትወርክ ነው ይዤ የምመጣው። ሁላችንም ተባብረን መስራት አለብን። የመጣሁትም ለዚህ ነው።” በማለት በደፈናው ክለቡን እያገዙ እንዳለ ብቻ በንግግራቸው ጠቁመዋል።