አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ምን አሉ?

አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ምን አሉ?

👉 “…ይሄ ሰዎችን ሊያስደነግጥ ይችላል ነገር ግን ያለንበትን መረዳት ያስፈልጋል።”

👉 “ሰው እንዲያውቅ የምፈልገው የዚህ ቡድን ሌጀንድ ስለሆንኩ አይደለም እዚህ አሰልጣኝ የሆንኩት ፤ በሁሉም ነገር ራሴን አብቅቼ ነው አሰልጣኝ የሆንኩት ፤ በስልጠና ፣ በትምህርት ዝግጅት ፣ በልምድ ራሴን አብቅቼ ነው።”

👉 “አንዱ በተወለድክበት ወይንም አድገህበታል ተብሎ በሚታሰብ ቦታ ስትሠራ ሰዎች ውለታ እየተዋለልህ እንዳለ ያስባሉ”

የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በዛሬው የአዲስ ተጫዋቾች ትውውቅ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ካነሷቸው ነጥቦች ከቡድኑ ጋር በተያያዘ የሰነዘሯቸው ሀሳቦችን እንደሚከተለው አቅርበናል።

“አሁን ካለንበት ደረጃ አንፃር የመጀመሪያው ዕቅዳችን ከአደጋው ስፍራ መራቅ ነው ፤ ይሄ ሰዎችን ሊያስደነግጥ ይችላል ነገር ግን ያለንበትን መረዳት ያስፈልጋል። ሁለተኛው ዕቅዳችን ደግሞ በሰንጠረዡ የተሻለ ስፍራን ይዞ ማጠናቀቅ ነው።

“2ኛ ሆኖ መጨረስ እና 7ኛ ሆኖ ማጠናቀቅ በቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪክ ያው ነው ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚመዘነው በሻምፒዮናነት ነው።

“አንድ በቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳደገ ሰው ጊዮርጊስን ማሰልጠን ህልም ነው ፤ እኔም ህልሜን እየኖርኩ እንደሆነ ይሰማኛል።ሰው እንዲያውቅ የምፈልገው የዚህ ቡድን ሌጀንድ ስለሆንኩ አይደለም እዚህ አሰልጣኝ የሆንኩት በሁሉም ነገር ራሴን አብቅቼ ነው አሰልጣኝ የሆንኩት በስልጠና ፣ በትምህርት ዝግጅት ፣ በልምድ ራሴን አብቅቼ ነው።

“እዚህ ክለብ ለመግባት ምንም ጥረት አላደረኩም ፤ አመራሩ ስላመነብኝ ነው ይህን ቡድን ማሻገር ትችላለህ ብሎ ጠርቶ የሰጠኝ።ይሄ ቡድን ሲጠራኝ ደግሞ ምንም ይሁን ምን ምን ችግር ውስጥ ቢገኝም ወደ ኃላ የምልበት ነገር የለም። በምችለው ነገር ሁሉ ይህን ቡድኑን ለማገዝ እንደ አሰልጣኝ ደግሞ የትኛውንም ፈተና በመወጣት ወደፊት መድረስ ለምፈልግበት ደረጃ ስንቅ እንደሚሆነኝም እንደ አሰልጣኝ አስባለሁ።

“ቡድኑ በዚህ ደረጃ በሁሉም ረገድ ይቸገራል ብዬ አቅጄ አልመጣሁም ተጫዋቾች ለቀዋል የተወሰኑ ልጆችን ከታች እንዲሁም ክለቡ በሚችለው አቅም ከውጭ ተጫዋቾችን አምጥተን ተፎካካሪ እንሆናለን ብዬ አቅጄ ነበር የመጣሁት።

“አንዱ በተወለድክበት ወይንም አድገህበታል ተብሎ በሚታሰብ ቦታ ስትሰራ ሰዎች ውለታ እየተዋለልህ እንዳለ ያስባሉ ፤ ይሄ አንዱ ችግር ነው በእግር ኳስ በተለይ በዚህ ሀገር ያንን በየቀኑ መቋቋም ሊያስቸግር ይችላል ነገርግን የእኔ ህልም ቡድኑ ባለበት ቦታ በማቆየት መልካሙን መጪውን ጊዜ ለማየት መሞከር ነው።

“በዚህ ውስጥ ብዙ ነገሮችን አልፌያለሁ ፤ አንዳንዶቹ ስሜት ይነካሉ ፣ አንዳንዶቹ ያስደስታሉ ፣ አንዳንዶቹ አሰልጣኝ ለምን ሆንኩ ሁሉ ያስብላሉ ነገር ግን ሕይወቴ ነው ሁሉንም ተቋቁሜ ማለፍ ግድ ይለኛል።”

“መድረስ ለማስብበት ቦታ መማርያ ይሆነኛል ብዬ አስባለሁ ፤ ሁሉም ሰው እንዲያውቀው የምፈልገው ራሴን ስላበቃሁ ነው እዚህ ቡድን የመጣሁት እንጂ እዚህ ቡድን ስላደኩኝ ፌቨር ሊደረግልኝ አይደለም።”

አሠልጣኙ ከላይ የተቀመጡትን ሀሳቦች ከተናገሩ በኋላ ስለቀጣይ አመት ቆይታቸው ግን ክለቡ ብቻ መልሱ እንዳለው ተናግረዋል።