በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ከቀይ ቀበሮዎቹ ጋር የሚፋለሙት ወጣት ፈርዖኖች የተመለከቱ መረጃዎች

ሀገራችን ኢትዮጵያ የተደለደለችበት ምድብ አንድ በቀጠናዊ ውድድር ‘UNAF’ በቅርበት የሚተዋወቁ የሰሜን አፍሪካ ኃያላን ሀገራት በመያዙ እንዲሁም አስተናጋጅ ሀገር ሞሮኮ በማካተቱ ምክንያት ከወዲሁ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ምድቦች ሆኗል። በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ከቀይ ቀበሮዎቹ ጋር የምትፋለመውና ከ1997 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ወደ ውድድሩ የምትቀርበው ግብፅ የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
በዋና ብሔራዊ ቡድን ደረጃ የነበራትን የቀደመ ቀጠናዊና አህጉራዊ የበላይነት ለመመለስ ባለፉት ዓመታት በወጣት ተጫዋቾች ልማት በርካታ ስራዎች የሰራችው ግብፅ በሀገር ውስጥ እና በአውሮፓ አካዳሚዎች ባደጉ ዲያስፖራ ተጫዋቾች በተዋቀረ ቡድን ወደ ውድድሩ ትቀርባለች።
ሞሮኮ፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ እና ሊቢያን ባካተተው ምድብ በሰሜን አፍሪካ እግር ኳስ ህብረት ዋንጫ (UNAF) የማጣሪያ ውድድር በስድስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፈችው ግብፅ በማጣሪያ ውድድሩ የገጠማት ፈተና ቀላል የሚባል አልነበረም።
“ወጣት ፈርዖኖች” ቻምፕዮን የሆኑበት የ1997 ውድድር ጨምሮ በመድረኩ ጥሩ ውጤቶች ማስመዝገብ ቢችሉም ግብፅ ካላት የእግር ኳስ ዕድገት አንፃር በዚህ የዕድሜ ደረጃ ያላት ውጤታማት ደረት የሚያስነፋ አይደለም። አሰልጣኝ ሑሴን አብደልለጢፍ ከሀገር ውስጥ አካዳሚዎች እንዲሁም ከአውሮፓ ወጣት ቡድኖች በተውጣጡ ተጫዋቾች በተዋቀረው አዲስ ብሔራዊ ቡድን ሀገሪቱን ከበርካታ ዓመታት በኋላ የዋንጫ ባለ ክብር ለማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች
አሰልጣኝ ሑሴን አብደልለጢፍ ከሁለቱ የሀገሪቱ ሀያላን ክለቦች አል አህሊ እና ዛማሌክ ጨምሮ በአውሮፓ አካዳሚዎች ያደጉ ዲያስፖራ ተጫዋቾች አካተዋል። ከነዚህም ውስጥ አጥቂው መሐመድ ጋማል ፤ አማካዩ አሕመድ ሳፍዋት እንዲሁም ከጣልያኑ ሞንዛ እና ከኔዘርላንዱ ኡትሬክት የተመረጡት አሚር አቡ ኤሌዝ እና ኤሚር ሐሰን ከቡድኑ የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።

