ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና እና ሀዋሳ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሜዳቸው ሀዋሳ ከተማን ያስተናገዱበት ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጀመር በፊት የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች ማኅበር ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ በማለት የሆሳዕና ባህላዊ የአንገት ልብስ እንዲሁም ፎቶግራፍ ለሀዋሳዎች አበርክተዋል።

ሀዲያዎች በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ ከተጠቀሙበት ስብስብ ውስጥ ተከላካዩ በረከት ወልደዮሐንስን በማሳረፍ የአሰላለፍ ለውጥ አድርገው አጥቂው ሙሳ ካማራን ሲያሰልፉ ሀዋሳዎች በጉዳት ያጡት መሳይ ጳውሎስን በተስፋዬ መላኩ እንዲሁም ብሩክ በየነን በእስራኤል እሸቱ በመለወጥ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በአቢዮ ኤርሳሞ ስታድየም የተከናወነው የሁለቱ በድኖች ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር ያልታየበት ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሦስተኛው የሜዳ ክፍል አመዝነው ሲጫወቱ በተቃራኒው ሀዋሳዋች መከላከልን ምርጫቸው አድርገው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ግብ ባልተቆጠረበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሆሳዕናዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ገና በጅምሩ ነበር። በ2ኛው ደቂቃ አብዱልሰመድ አሊ የመታው ኳስ በግቡ ግራ አግዳሚ ሲወጣበት በ15ኛው ደቂቃ ደግሞ ሙሳ ካማራ መሬት ለመሬት አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ቤሊንጋ አድኖበታል። ከዚህ በተጨማሪ አፈወርቅ ኃይሉ ያሻማውን ኳስ በድጋሜ ቤሊንጌ ቀድሞ በመውጣት ያዳነበት ሲሆን በሌላ አጋጣሚም አፈወርቅ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ የወጣበት በመጀመሪያው አጋማሽ የታዩ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

በተቃራኒው ሀዋሳዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ ባያደርጉም በ30ኛው ደቂቃ አዲስዓለም ተስፋዬ ከርቀት በመታው ኳስ የሀዲያዎችን ግብ ክልል ለመፈተሽ የሞከሩበት ብቸኛ ሙከራም ነበር። እጅጉን ተደራጅተው መከላከል ላይ በማተኮር ጨዋታቸውን ያደረጉት ሀዋሳዎች የመጀመሪያውን አጋማሽ ግብ ሳይቆጠርባቸው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በተመሳሳይ እንቅስቃሴ የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛ አጋማሽ ነብሮቹ የግብ ዕድል በመፍጠር በኩል ይበልጥ ተሽለው ቀርበዋል። ሆሳዕናዎች በ50ኛው ደቂቃ ላይ ሙሳ ካማራ ከርቀት በመታው እና ቤሊንጌ ባዳነበት ኳስ የግብ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። የአጥቂዎች ቁጥራቸውን በመጨመር ኢዮኤል ሣሙኤልን ካስገቡም በኋላ ይበልጥ ጫና መፍጠር ችለው ነበር።

በአንፃሩ ተጋጣሚዎቻቸው ሀዋሳዎች የነብሮቹን የአየርም ሆነ የአጭር ቅብብል በሚገባ በመከላከል የተዋጣ ጊዜን ያሳለፉ ሲሆን በተለይም ላውረንስ ላርቴ እና አትራም ኮዋሜ ትልቁን ሚና ይወሰዳሉ። ከዚህም አልፈው በ82ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ ከማዕዘን ያሻምውን እና ሄኖክ አየለ የጨረፈውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው አለልኝ አዘነ ወደ ግብነት ለውጦት ሐይቆቹን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር።

ነገር ግን የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው የተጫወቱት ነብሮቹ በ87ኛው ደቂቃ አብዱልሰመድ ዓሊ የመታው ኳስ ሳጥን ውስጥ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሄኖክ አርፍጮ ወደ ግብነት ለውጦ አቻ መሆን ችለዋል።

ሆሳዕናዎች ከአቻነቱ ግብ በኋላም የአሸናፊነት ዕድል በመሐመድ ናስር ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተው ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ