የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች በሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ እሁድ እለትም ቃሊቲ ክራውን ሆቴል አከባቢ በሚገኘው የመድን ሜዳ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡ ሁለቱ የአማራ ክልል ተወካዮች ወሎ ኮምቦልቻ ሰበታ ከተማን፤ ባህርዳር ከተማ ደግሞ ኢትዮጵያ መድንን ገጥመው ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡
በ7፡00 ሰዓት የተጀመረው እና እጅግ ጥቂት ተመልካች የታደመበት የሰበታ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ጨዋታ በአንፃራዊነት ቀልብን የመግዛት አቅም ነበረው፡፡
ወሎ ኮምቦልቻ
የወሎው ቡድን ኳስን ከተከላካዮች ጀምሮ የመቀባበል ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል የሚደርሱበት መንገድ (Build-up phase) የነበራቸው እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል አይነት ነበር፡፡ ሆኖም በባላጋራ የመጫወቻ ስፍራ ላይ የሚያሳኳቸው ቅብብሎች በላቀ በራሳቸው የሜዳ ክልል ላይ ያደርጓቸው የነበሩ ቅብብሎች የተሻለ ስኬታማ ነበሩ፡፡ በሜዳው የጎንዮሽ ክፍልና ወደ ኃላ የሚዳርጉት ቅብብሎች የበዙ ነበሩ፡፡ በማጥቃት ወረዳው ላይ በሚፈጥሯቸው ደካማ የተናጠል የተጫዋቾች ውሳኔ አሰጣጥ ምክንያት ለጎልነት የቀረቡ በቅብብሎች የተመሰረቱ በርካታ ኳሶች ሲመክኑ ይታያል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ቴክኒካዊ ክህሎትን የታደሉ እንደ እንድሪስ ሰኢድ አይነት ተጫዋች ቢኖሩትም በማጥቃት ወረዳው ላይ የነበራቸው የአጨራረስ ድክመት ከአሰ,ሸናፊነት አርቋቸዋል፡፡
የዕረፍት ሰዓት ታክቲካዊ ውይይቶች
የወሎ ኮምቦልቻው አሰልጣኝ ሻምበል መላኩ አብርሐ በዕረፍት ሰዓት በተረጋጋ መንፈስ ለተጫዋቾቻቸው በመጀመሪያው አጋማሽ የተደረጉ የታክቲክ ስህተቶችን እና አጠቃላይ የቡድኑን ደካማ ጎኖች የሚያስረዱበት መንገድ ትኩረትን የሚስብ ነበር፡፡
በማግኔት የሚታገዝ የተጫዋቾች ቦታ እና በጨዋታው የሚኖራቸውን ሚና የሚሳያ ሰሌዳ (Magnetic Tactic Board) ይዘው ቡድናቸው በመከላከል እና በማጥቃጥ ሒደት ምንአይነት ቅርፅ ሊኖረው እንደሚገባ በግልፅ ሲያስረዱ ታይተዋል፡፡ በግል ተጫዋቾቻቸው በሜዳው ውስጥ ከተጋጣሚ ተጫዋቾች አንፃር የሚዳርጉትን እንቅስቃሴ እና ቦታ አጠባበቅም እንዲሁ ሲገልፁ ተስተውለዋል፡፡
ቡድኑ የኳስ ቅጥጥር የበላይነት ሲኖረው ሊያሳይ የሚገባውን የጨዋታ ሂደት አደረጃጀት፣ በመከላከል ሒደት እንዲኖረው የሚፈልጉት ቅርፅ፣ የMarking System አተገባበር፣ በማጥቃት ሒደት የተጫዋቾቹ የፊት ለፊት እንቅስቃሴ እና የመቀባበያ አማራጭ መስመሮች የሚፈጥሩትበት መንገድ ሲያስተምሩ ዘመናዊነትን የተላበሰ እይታ ነበራቸው፡፡
እዚህ ላይ አንድ መታሰብ ያለበት ጉዳይ እንደነዚህ አይነት ጥልቀት ያላቸው ታክቲካዊ ውይይቶች የሚደረጉባቸው ቦታዎች ሊታሰብቸው ይገባል፡፡ ምክሮቹ ለተጋጣሚ ቡድን እና ለተመልካች አመቺ በሆነ ሥፍራ ላይ መሆኑ አሉታዊ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል፡፡
ከዕረፍት መልስ የወሎ ኮምቦልቻ ተጫዋቾች ሙሉ በሙሉ ባይባልም የአሰልጣኛቸውን ምክሮች የተገበሩ ይመስላሉ፡፡ የጠሩ እና የበዙ ተደጋጋሚ የጎል መኩራዎችን ቢከውኑም የአጨራረስ ድክመታቸውን ባለመቅረፋቸው ያስቆጠሩት የአቻነት ግብ ብቻ ነው፡፡ ተደጋጋሚ ጫና በመፍጠር በመጨረሻዎቹ ዲቂቃዎች እንድሪስ ሰኢድ ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ነጥብ ሊጋሩ ችለዋል፡፡
ሰበታ ከተማ
በመጠኑ የተደራጀ ቡድን ይመስላል፡፡ በተከላካይ መሰመሩ ላይ ያሉት ተጫዋቾች ይበልጥ የተግባቡና የተዋሃዱ ናቸው፡፡ ተመስገን ማሞ ወደኃላ በመሳብ ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን ሲሰጥ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ በተጋጣሚያቸው የተከላካይ አማካዮች እና የማጥቃት አማካዮች መሃል ሰፊ ክፍተት የነበረ በመሆኑ በአራቱ የኮምቦልቻ የማጥቃት ሐላፊነት የሚወጡ ተጫዋቾች ላይ የቁጥር ብልጫን በማስገኘት የተመስገን ወደ ኃላ ማፈግፈግ ተገቢ ነበር፡፡ የሰበታ የማጥቃት አማካዮች (ኤርሚያስ፣ መክብብ እና መንግስቱ) ከዕረፍት በፊት በመሃል ሜዳው ላይ የነበራቸው ብልጫ ይህ የሰፋው የመሃል ሜዳ ጠቅሟቸዋል፡፡ ኤርሚያስ ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ከማስቆጠሩ በፊት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ተጠቃሽ ሙከራ ነበር፡፡
ሰበታ ከተማ የአማካይና አጥቂው ክፍል ላይ በሚገኙ ተጫዋቾች የአካል ብቃት በደንብ መስራት ይገባዋል፡፡ በጨዋታ ሂደት ባሉ ሽግግሮች ላይ ተጫዋቾች ያላቸው ፍጥነት እና ሰፊ የሜዳ ክልል የመሸፈን ድክመት ሊተኮርበት ይገባል፡፡
የሰበታው ቀኝ መስመር ተከላካይ ቴዋድሮስ ወርቁ በጨዋታው ከታዩ ተጫዋቾች ዋነኛው ነው፡፡ 13 ቁጥር ለባሹ ተከላካይ ሚዛናዊ የማጥቃት እና የመከላከል እንቅስቃሴው፣ ጉልበቱ፣ ፍጥነቱ እና ድፍረቱ ዘለቄታዊነት ካከለበት ትልቅ ደረጃ ሊያደርሰው የሚችል ጠንካራ ጎኖቹ ናቸው፡፡