ግብፅ በአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ያላትን የጎላ ብልጫ የማስጠበቅ ዘመቻዋን ነገ ትጀምራለች፡፡ ሃያሎቹ አል አሃሊ እና ዛማሌክ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ሲሳተፉ ፤ ኢኤንፒፒአይ እና የ2014/15 የግብፅ ፕሪምየር ሊግ አስገራሚ ቡድን ምስር አል ማቃሳ በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ ዳግም የግብፅ ክለቦችን የበላይነት ለማስፈን በውድድሮቹ ላይ ይሳተፋሉ፡፡
ምስር አል ማቃሳ በ79 ዓመታት ታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ በአፍሪካ መድረክ ተሳታፊ በሚሆንበት በዚህ የውድድር ዘመን በቅድመ ማጣሪያ ዙር ከሃገራችን ክለብ መከላከያ ጋር በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታል፡፡ በዚህ ፅሁፍ ስለዚህ ክለብ ምስረታ፣ አደረጃጀት እና የአጨዋወት ፍልስፍና ሰፋ ያለ መረጃ እናቀርባለን፡፡
ምስር አል ማቃሳ እ.ኤ.አ. በ1937 የተመሰረተ ሲሆን 100 ኪሎ ሜትሮችን ከካይሮ ርቃ በምትገኘው የፋዩም ከተማ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ ከተመሰረተ ረዘም ያለ ጊዜያትን ያሳለፈ ቢሆንም ወደ ግብፅ ፕሪምየር ሊግ ያደገው በ2009/10 የውድድር ዘመን ነበር፡፡ አል ማቃሳ ከዚህ ቀደም ፈርኦኖቹ እና ሃዊዲ ክለብ በሚል ስም ይታወቅ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የክለቡ ስፖንሰር በሆነው ምስር ፎር ክሊሪንግ ሴትልመንት ኤንድ ሴንትራል ዲፖሲተሪ በተባለ የግብፅ የፋይናንስ ተቋም ስም ይጠራል፡፡ ተቋሙ በአክሲዮን ገበያ ውስጥ ተሳታፊ ሲሆን የካይሮ እና አሌክስአንደሪያ የአክሲዮን ገበያዎች፣ ባንኮች እና የድለላ ተቋማት በተቋሙ ውስጥ አክሲዮን ድርሻ አላቸው፡፡
ክለቡ ዓምና ባልተጠበቀ መልኩ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን በግብፅ ዋንጫ አል አሃሊ እና ዛማሌክ ለፍፃሜ መድረሳቸው እና ሁለቱም የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ተካፋይ መሆናቸው አል ማቃሳን በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ እንዲሳተፍ አስችሎታል፡፡
ስታዲየም
አሠልጣኝ
የቀድሞው የኤስማኤሊ ኮከብ ጋልአል ጫማውን የሰቀለው በ2005 ነበር፡፡ የ2015 የውድድር ዘመን ምስር አል ማቃሳን አራተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ከፍተኛውን ሚና ከተወጣ በኋላ የ2015 የግብፅ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ተብሎ ተመርጧል፡፡
የአጨዋወት ፍልስፍና
የምስር አል ማቃሳ አጨዋወት ከግብፅ እግርኳስ ቅኝት የወጣ አይደለም፡፡ ኳስ መቆጣጠርን መሰረት አድርጎ የሚጫወት ክለብ ሲሆን ከሜዳው ውጪ እንዲሁም ከክለቡ የተሻለ ደረጃ እና መሰረት ካላቸው ክለቦች ጋር ሲጫወት የመሃል ሜዳ ብልጫን ከመውሰድ ይልቅ ጠንካራ መከላከል እና ፈጣን መልሶ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ እግርኳስ ይጫወታል፡፡ ክለቡ እንደሃኒ ሰዒድ የመሳሰሉ ኳስን በእግራቸው ስር ለረጅም ጊዜ ማቆየት የሚችሉ ተጫዋቾች አሉት፡፡
አል ማቃሳ ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት የሚያስችለውን እና ለማጥቃት አመቺ የሆነውን የ4-3-3 አሰላለፍ በብዛት ይጠቀማል፡፡
የክለቡ አሰልጣኝ ኤሃብ ጋልአል ተጫዋቾን አፈራርቆ የመጠቀም ስርዓት አዳብረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የክለቡን ቋሚ 11 ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ክለቡ ከ17 የሚልቁ ተጫዋቾቻቸውን አፈራርቆ መጠቀም የተለመደ ተግባራቸው ሆኗል፡፡
ቁልፍ ተጫዋቾች
ሃኒ ሰዒድ
ሃኒ መሃመድ ሰዒድ ዛካሪያ በሚል ሙሉ ስም የሚታወቀው ተጫዋቹ ከፍተኛ ልምድ ያለው የክለቡ አምበል እና መሪ ነው፡፡ ሰዒድ ለተከላካዮች በሚሰጠው ሽፋን፣ ለአማካዬች በሚያቀብለው የተመጠኑ ኳሶች እና ኳስን ለረጅም ግዜ በመያዝ አቅሙ ተለይቶ ይታወቃል፡፡ ሰዒድ ማሊ ባዘጋጀችው የ2002 የአፍሪካ ዋንጫ ከዶፒንግ ጋር በተያያዘ በካፍ እና ፊፋ የስድስት ወራት እገዳ ተወስኖበት የነበረ ሲሆን የአፍሪካ ዋንጫን ከግብፅ ጋር በ2008 እና 2010 አሸንፏል፡፡
ይህ ለረጅም ግዜ እግርኳስን በግብፅ፣ ቤልጅየም እና በጣልያን የተጫወተው ተጫዋች ለሁለቱ የካይሮ ሃያላን አል አሃሊ እና ዛማሌክ፣ ለጣልያኖቹ ባሪ እና ፍዮረንቲና ተጫውቷል፡፡ ለግብፅ ብሄራዊ ቡድን ለ77 ግዜያት የተጫወተው ሃኒ ሰዒድ ያለጥርጥር የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች ነው፡፡ የመከላከያ የአማካይ ክፍል ተጫዋቾች የሃኒ ሰዒድን በጨዋታው ላይ የሚኖረውን ሚና መገደብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ኦማር ናጅዲ
ኦማር ናጂዲ ለሁለቱ ታላላቅ የሞሮኮ ክለቦች ዋይዳድ እና ራጃ ካዛብላንካ ተጫውቷል፡፡ ፍጥነቱ በሁለቱም ክንፎች አጥቂ ሆኖ መሰለፍ እንዲችል አድርገውታል፡፡ ባለው ፍጥነት ተከላካዮችን መረበሽ የሚችለው ይህ ሞሮኮዊ አጥቂ የሀሰተኛ 9 ቁጥር ሚናን በሚገባ መወጣት እንደሚችል በተደጋጋሚ በውድድር ዘመኑ አስመስክሯል፡፡
ኤል ሳዒድ ሃምዲ
ይህ የቀድሞ የአል አሃሊ አጥቂ የምስር አል ማቃሳን የፊት መስመር በመምራት ይታወቃል፡፡ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ያስቆጠረው ግብ 1 ብቻ ቢሆንም አሁንም ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ የአጥቂ ስፋራ ተጫዋች ነው፡፡ ሃምዲ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ ሰፊ የሆነ ልምድ ያለው ሲሆን በዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይም ከአል አሃሊ ጋር ተሳትፏል፡፡ በ2011 በተደረገው የናይል ተፋሰስ ሃገራት ውድድር ላይ 6 ግብ በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢ ነበር፡፡
ናና ፖኩ
የ2010/11 የውድድር ዘመን ለበርከም አርሰናል እየተጫወተ በ16 ግቦች የጋና ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ነበር፡፡ በእስራኤል ያልተሳካ ቆይታ የነበረው ፖኩ በግብፅ ኤትሃድ አል ሾርታ ጥሩ የሚባል ግዜያት አሳልፏል፡፡ ምስር አል ማቃሳን ከተቀላቀለ በኋላ የተሻለ ግዜ እያሳለፈ ሲሆን በውድድሩ ዘመኑ ስድስት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡ ፖኩ የምስር አል ማቃሳ የወቅቱ ኮከብ ግብ አግቢ ሲሆን በሁለቱም ክንፎች ላይ ተሰልፎ መጫወት ይችላል፡፡ ይህ ምዕራብ አፍሪካዊ አጥቂ እጅግ ፈጣን እና ጉልበተኛ ሲሆን ተከላካዮችን የመረበሽ ችሎታ አለው፡፡ የመከላከያ ተከላካዮች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊከታተሉት የሚገባ ተጫዋች ነው፡፡
ምስር አል ማቃሳ በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ ያለው ጥንካሬ
ምስር አል ማቃሳ በ2014/15 የውድድር ዘመን በሜዳው ጥንካሬውን አሳይቷል፡፡ ቢሆንም በ2015/16 በግብፅ ፕሪምየር ሊግ በሜዳው ካደረጋቸው 10 ጨዋታ ማሸነፍ የቻለው ሶስቱን ብቻ ነው፡፡ በአምስቱ አቻ ሲለያይ ሁለቱ ሽንፈትን ቀምሷል (የተሸነፈው በአል ዳከሂልያ እና የሽመልስ በቀለ ክለብ በሆነው ፔትሮጀት በተመሳሳይ 1-0 በሆነ ውጤት ነው)፡፡ በሚያስገርም መልኩ ምስር አል ማቃሳ ዘንድሮ ከሜዳው ውጪ አንድም ጨዋታ አልተሸነፈም፡፡ ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎች በአምስቱ ድል ሲቀዳጅ በሁለቱ ብቻ አቻ ተለያይቷል፡፡ ከዛማሌክ ጋር 2-2 አቻ የተለያየበት ከሜዳ ውጪ የተደረገ ጨዋታ ክለቡ አሁንም በጠንካራ አቋም ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው፡፡
የዘንድሮ አቋም
በ2015/16 የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ምስር አል ማቃሳ በጥንካሬው ቀጥሏል፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ ከዛማሌክ ጋር በዕኩል 31 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሶስተኛ ነው፡፡ ካደረጋቸው 17 የሊግ ጨዋታዎች በስምንቱ ሲያሸንፍ በሰባቱ አቻ ተለያይቷል፡፡ ክለቡ የተሸነፈው ሁለት ግዜ ብቻ ነው፡፡ የአል ማቃሳ የአጥቂ መስመር በውድድር ዓመቱ 26 ግቦችን አስቆሯል (በሊጉ ከአል አሃሊ ቀጥሎ ብዙ የሊግ ግብ ያገባ ክለብ ነው)፡፡ የተከላካይ መስመሩ 15 ግቦች ተቆጥረውበታል፡፡