በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የግብፁ ክለብ ምስር አል ማቃሳ መከላከያን 3-1 አሸንፏል፡፡ ከጨዋታው በኃላ የመከላከያው አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ እና የማቃሳው አሰልጣኝ ኤሃብ ጋላል ለጋዜጠኞች አሰተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
“ደካማ ጎናቸው አልታየኝም” አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ
ስለጨዋታው
“ጨዋታው ጥሩ አልነበረም፡፡ ተጋጣሚያችን በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ ጥንካሬያቸውን ብናውቅም ጨዋታው እንደተጀመረ ግብ ያስቆጥሩብናል ብለን አልጠበቅንም ነበር፡፡ የምንፈጥራቸው ስህተቶች ናቸው ግብ እንዲቆጠር የሚዳርጉት፡፡ ከዕረፍት መልስ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ውጤቱን ለመቀየር አስቸጋሪ ነበር፡፡
ክፍተት ስለታየበት የተከላካይ መስመር
” አሁንም ባሉን ተጫዋቾች ነው የምንጠቀመው፡፡ ሌላ ምንም አማረጭ የለንም፡፡ በአጠቃላይ በቡድን ደረጃ ከተጋጣሚያችን ጋር ሰፊ ልዩነት አለን፡፡ ”
ስለተጋጣሚያቸው
“ደካማ ጎናቸው አልታየኝም፡፡ እውነት ለመናገር አል ማቃሳ በጣም ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ይህን ከዚህ በፊትም ያየሁት ነገር ነው፡፡ በጋራ በቁጥር በዝተው ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ፡፡ በሊጋቸውም ላይ ጥሩ ሲጫወቱ አይቻለው፡፡ ከኛ ጋር ሲጫወቱ የነሱን ድክመት ማወቅ አልቻልንም፡፡ ”
ስለመልስ ጨዋታው
” በሜዳችን 3-1 ተሸንፈናል፡፡ ከሜዳችን ውጪ ቢያንስ 3-1 ማሸነፍ መቻል አለብን፡፡ ይህንን ማድረግ ከባድ ነው ፣ ቀላል ነው አልልም፡፡ የተወሰኑ ነገሮችን ለማስተካከል እንጥራለን፡፡ በመስመር በኩል የነበረብንን ድክመት ለማሻሻልም እንሞክራለን፡፡ ዕድል ያልጠሰጣቸውን ተጫዋቾች ለመሞከር እንጥራለን፡፡ ”
” ጨዋታው አልተጠናቀቀም” ኤልሃብ ጋልአል
ስለጨዋታው
“ለኔ ጥሩ ውጤት ነው፡፡ ለኛ ይህ የመጀመሪያ የአህጉራዊ ውድድር ጨዋታ ነበር፡፡ ጥሩ ቡድን አሸንፈን መልካም ጅማሮ አድርገናል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ አልቻልንም ነበር፡፡ 2-0 መምራት ከጀመርን ጀምሮም ትንሽ የመዘናጋት ነገር ይታይብን ነበር፡፡
” ዓየር ፀባዩን ለመልመድ አስቸግሮናል፡፡ በተጨማሪም ስምንት እና ዘጠኝ የሚሆኑት ተጫዋቾቻችን ለዚህ ውድድር አዲስ ናቸው፡፡ ተጋጣሚያችንም በሁለተኛው አጋማሽ ተጭኖ መጫወቱ ለኛ ከባድ ነበር፡፡ ”
ስለመልስ ጨዋታ
” ጨዋታውን ማሸነፋችን ሊጠቅመን ይችላል፡፡ ነገር ግን ገና አልተጠናቀቀም፡፡ ለካይሮ ጨዋታ ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን፡፡ ”
ስለተጋጣሚያቸው
” መከላከያ ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ጥሩ ኳስ ይጫወታሉ፡፡ በብዛት ረጃጅም ኳሶችን መጫወትን እንደሚመርጡ ስላወቅን ተዘጋጅተን ነበር፡፡ ቢሆንም ሶስት የጠሩ የግብ ማግባት ዕድሎችን አግኝተው ነበር፡፡ ሁለት ተጫዋቾች (ሙሉዓለም እና ፍሬው)ጥሩ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ቡድኑ 3-0 እየተመራም ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ይህ የመከላከያ ጠንካራ ጎን ነው፡፡”