የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 2-1 ሲዳማ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን 2-1 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

👉 “ከመሪዎቹ በነጥብ ላለመራቅ የሚለው ነገር ተጫዋቾቹ ላይ ጫና ፈጥሮብናል” ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው

“ከመሪዎቹ በነጥብ ላለመራቅ የሚለው ነገር ተጫዋቾቹ ላይ እየፈጠረ ካለው ጫና የተነሳ ልጆቹ ላይ ቶሎ ጎል የመፈለግ ከዛም የተገኘውን ጎል የማስጠበቅ አይነት አዝማሚያ ይታያል። ይህም አዕምራቸውን ስለሚይዘው ከእንቅስቃሴ የመውጣት ነገር አለ። ከዚህ በስተቀር እንቅስቃሴ ረገድ ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው።”

ስለ ዳኝነቱ

“እኔ በግሌ ዳኞችን በሁለት መንገድ ነው የምመለከታቸው። አንደኛውና መሠረታዊው ከዳኞች የሚሰወሩ ነገሮች አሉ። ለዚህም ሲባል ነው ዳኝነት በቴክኖሎጂ እየታገዘ ያለው። ሌላኛው ደግሞ ዳኞቻችን ከተለያዩ ስሌቶች ውስጥ መውጣት አለባቸው ብዬ አስባለሁ። የትም ቦታ ጨዋታዎችን ሲመሩ የጨዋታው ህግ ላይ ማተኮር አለባቸው። ምክንያቱም ዳኞች እኛው የምንኖርበት ያደግንበት ማኅበረሰብ ነፀብራቅ ናቸው።”


👉 “የፍፁም ቅጣት ምቱም ሆነ ለሁለተኛው ጎል ምክንያት የሆነው የማዕዘን ምት በዳኝነት ስህተት የተሰጡብን ናቸው” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ የኳስ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በጨዋታው ደስተኛ ብሆንም በዳኝነቱ ግን አይደለሁም። የተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት ሆነ ለሁለተኛው ጎል ምክንያት የሆነው የማዕዘን ምት ጭምር በዳኝነት ስህተት የተሰጡብን ናቸው። ይህ ደግሞ የተጫዋቾችን ሥነ ልቦና ያወርዳል። በተለይ ከሁለተኛው ጎል በኃላ እነሱ የተሻሉ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ የኛ ልጆች በስነልቦናው ረገድ መውረዳቸው ነው።”

ስለተከሉት አጨዋወት

” ወደ ጨዋታው የመጣነው ያለምንም ስጋት ነበር። እነሱ ኳስን ከኋላ ለመጀመር አስበው በረኛና ተከላካይ ላይ ኳሱን ስለሚቀባበሉ የተጫወቱ ይመስላል እንጂ ምንም አደጋ ሲፈጥሩብን አልነበረም። አደጋ እንደማይፍጥሩ ስለገባን ይህን እንዲያረጉ ፈቅደንላቸው ነበር። ይህም ለእኛ አጨዋወት እንዳንቸገር አድርጎናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ