የአዲስ አበባ ስታዲየም ትችት እያስተናገደ ይገኛል

አንጋፋው እና የወቅቱ የመዲናዋ አንድ ለእናቱ በመሆን እያገለገለ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም በተጫዋቾች እና በአሰልጣኞች ትችት ማስተናገዱን ቀጥሏል።

በቀዳሚ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ተሰርቶ በተለያዩ ወቅቶች በተደረገለት ማሻሻያ የአሁን መልኩን የያዘው አአ ስታዲየም ሀይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ እና በርካታ ስፖርታዊ ውድድሮችን ከ60 ዓመት በላይ ሲያስተናግድ ቆይቶ በቀርቡ ካፍ ባደረገው ግምገማ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስናገድ እንደማይችል መነገሩ የሚታወቅ ነው። አሁን ደግሞ የሜዳው ለጨዋታ አለመመቸቸትን ተከትሎ የውስጥ ውድድሮችን የማዘጋጀት አቅሙ ላይ ጥያቄ እየተነሳበት ይገኛል።

ሜዳው በዋናነት በባለቤትነት የያዘው የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን ቢሆንም የመጫወቻ ሜዳውን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን በመከታተል በተለይ ሜዳውን የመንከባከብ ኃላፊነት በፌዴሬሽኑ ሥር እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም በዘንድሮ ዓመት የሜዳ ገቢያቸውን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በራሳቸው መውሰዳቸውን ተከትሎ ሜዳው እንክብካቤ እየጎደለው ደረቅ እየሆነ በመምጣቱ ለጨዋታ አመቺ አይደለም በሚል በአሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ቅሬታ እያቀረቡበት ይገኛል።

በዚህ ሳምንት ከተሰጡ የአሰልጣኝ አስተያየቶች መካከልም ውበቱ አባተ “ሜዳው ዛሬ እንዳያችሁት ለመጫወት በጣም ከባድ ነበር። በዚህ ሜዳ ላይ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት እጅግ ከባድ ነው። ወደ ግብ ጠባቂ የሚመለሱ ኳሶች እጅግ አስፈሪ ነበሩ፤ ኳሶቹ ፈረስን እንደመያዝ በጣም የከበዱ ነበሩ። ፌደሬሽኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያስብበት ይገባል። የምንጫወትበት ሰዓት በራሱ 9 ሰአት መሆኑ ከባድ ነው። በተጨማሪ ደግሞ የመጫወቻ ሜዳው ምቹ አለመሆኑ ነገሮችን ከባድ ያደርጋቸዋል። ኳስ ለሚያውቅ ሰው በዚህ ሜዳ ላይ ስለኳስ ማውራት በጣም ከባድ ነው። እንደው ቢቻል ከጨዋታ በፊት ሜዳው ውሃ ሊጠጣበት የሚችለው መንገድ ቢመቻች” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ትላንት በደርቢው የማሸነፍያ ጎል ያስቆጠረው ሙሉዓለም መስፍን ስለ ሜዳው አለመመቸት ሲናገር “ስለ አዲስ አበባ ስታዲየም መናገር እፈልጋለው። ቅሬታ ከምታቀርብባቸው የክልል ሜዳዎች የባሰ እየሆነ መጥቷል። ምንም ዓይነት ክትትል እየተደረገበት አይደለም። ሜዳው ደረቅ ድንጋይ እየሆነ ይገኛል። በዚህ ደረቅ ሜዳ ላይ በሦስት ቀን አንዴ እየተጫወትን እየተቀጠቀጠ ለተለያዩ ጉዳቶች እየተዳረግን እንገኛለን። ፌዴሬሽኑ ተመልካች ጥሩ ጨዋታ አይቶ እንዲዝናና ይህን ሜዳ መንከባከብ አለበት ወይም ለአዲስ አበባ ክለቦች ለኢትዮጵያ ቡና እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳውን መስጠት ቢቻል መልካም ነው”።

ሦስት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በሜዳነት እየተጠቀሙበት የሚገኘው ስታዲየም በቀጣይ በምን መልኩ መስተካከል እንዳለበት ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካለት የሚቀርቡ ምላሾችን ይዘን የምንቀርብ ቢሆንም ሜዳውን ለጨዋታዎች ምቹ የማድረግ ተግባር በሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት መከወን ይኖርበታል ጥቆማችን ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ