ከፍተኛ ሊግ ለ | የቴዎድሮስ መንገሻ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ለነቀምቴ ከተማ ወሳኝ ሦስት ነጥቦች አስገኘች

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 8ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታ ሱሉልታ ያያ ቪሌጅ ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከነቀምቴ ከተማ ጋር ያገናኘው ጨዋታ በመጨረሻው ደቂቃ በተቆጠረች ጎል ነቀምቴ ከተማ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል።

ብዙም የጎላ የጎል ሙከራ ያልታየበት እና አዲስ አበባዎች ኳሱን አደራጅተው ለመጫወት የሚያደርጉት ጥረት መልካም የነበረ ቢሆንም ግልፅ አጋጣሚዎች በመፍጠር ረገድ የአጠቃቀም ችግሮች ነበሩባቸው። ቀጥተኛ አጨዋወት የሚከተሉት ነቀምቴዎች የጥንቃቄ አጨዋወት በመከተል አጥቂያቸውን ኢብሳ በፍቃዱን ትኩረት ያደረጉ የረዣዥም ኳሶችን በመጠቀም ጎል ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ጠንካራውን የአዲስ አበባ ተከላካዮችን አልፈው ጎል ለማስቆጠር ተቸግረዋል።

የጨዋታው እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድበትም በሁለቱም በኩል የነበረው የማጥቃት አቅማቸው ደካማ በመሆኑ ምንም የተለየ ነገር ሳያስመለክተን የቀጠለው ጨዋታ አዲስ አበባዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረን ኳስ አጥቂው ዮሴፍ ዳሞዬ ኳሱን በግንባሩ ገጭቶ ጎል ሊያስቆጥር በሚችልበት አቋቋም ላይ ሆኖ ሳለ የነቀምቴ አንበል ደረጄ ፍሬው የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ፍፁም ቅጣት ምት ሰጡ ሲባል ጨዋታው በሁለተኛ ቅጣት ምት እንዲቀጥል ማድረጋቸው አዲስ አበባዎች የዳኛውን ውሳኔ በመቃወም ክስ አስይዘዋል። ይህ ሁኔታ የተመለከቱ በስፍራው የነበሩ የስፖርት ቤተሰቦችን ዳኛው ህጉን የተገበሩበት መንገድ አግራሞትን ጭሯል።

ከእረፍት መልስ በአንፃራዊነት ጨዋታው ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ወደ ጎል የሚደረስበት ቢሆንም ጎል ሳይቆጠርበት እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ 85ኛው ደቂቃ ሊደርስ ችሏል። ከነቀምቴዎች በተሻለ ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወት አዲስ አበባዎች የተሻሉ ቢሆኑም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ኳስና መረብን የሚያገናኝ ወሳኝ አጥቂ ቡድኑ ውስጥ አለመኖሩ የማታ የማታ ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎታል።

በነቀምቴ በኩል ተጫዋቾቹ በየሜዳ ክፍላቸው ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ የነበራቸው ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑ ውጤታማ አደረጋቸው እንጂ ከእረፍት መልስ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኢብሳ በፍቃዱ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት ብቸኛው ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ነበር።

በሚወሰድባቸው ብልጫ ጨዋታውን ተቆጣጥረው አቻ ለመውጣት ጥንቅቃቄን የመረጡት ነቀምቴዎች በ85ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው የቀድሞ የወላይታ ድቻ ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋች ቴዎድሮስ መንገሻ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ተደርቦ እግሩስር ስትገባ ነቀምቴ ከሜዳው ውጭ ሦስት ነጥብ የሚያገኝበትን ወሳኝ ጎል አስቆጥሯል።

ከዚህች ጎል መቆጠር በኃላ አንድ አቻ መሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ አዲስ አበባዎች ከቅጣት ምት የነቀምቴ ተከላካዮች ኳሱን ለማራቅ የሰሩትን ስህተት ተከትሎ በአካባቢው የሚጠቀም ተጫዋች ባለመኖሩ ዕድሉን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ጨዋታውም በነቀምቴ ከተማ 1–0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ