የፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት አናት የሚገኙት ፋሲል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ሲጋሩ ተከታዩ መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ በሰፊ ግብ አሸንፎ ልዩነቱን አጥብቧል። ግርጌ የሚገኘው ሆሳዕና አቻ ሲለያይ ድሬዳዋ ከተማ እና ወልዋሎ አሁንም ተሸንፈዋል። በየሳምንቱ እንደተለመደው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ክለብ ነክ ጉዳዮችን በተከታይ መልኩ አሰናድተናል።

👉 ፋሲል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደተናነቁ ቀጥለዋል

14ኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው ሊጉ በዚህኛው ሳምንት እጅግ ተጠባቂ በነበረውን ፍልሚያ በጎንደር ዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ሊጉን ከአናት ሆነው የሚመሩት ፋሲል ከነማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ጨዋታ 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

1-1 ከተጠናቀቀው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ መልስ የተሻሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ75ኛው ደቂቃ አቤል ያለው ባስቆጠራት ሁለተኛ ግብ በዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ከአፍ እስከ ገደፉ የሞሉት ፋሲላዊያንን ድንጋጤ መክተት ችለው የነበረ ቢሆንም በ83ኛው ደቂቃ በተገኘች የሙጂብ ቃሲም የፍፁም ቅጣት ምት ግብ በሜዳቸው አንድ ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

ጥሩ ፉክክር በተስተናገደበት በዚሁ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ በዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ያላቸው ያለመሸነፍ ጉዞ እጅግ በተሻሻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊነጠቅ የደቂቃዎች እድሜ በቀሩበት ሁኔታ ዘንድሮ በተለያዩ ጨዋታዎች የቡድኑ አዳኝ መሆኑን ያስመሰከረው ሙጂብ ቃሲም ዳግም ከሽንፈት ታድጓቸዋል።

የሊጉን ክብር ለመጎናፀፍ የተሻለ እድል ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ነጥብ ማጋራታቸውን ተከትሎ የነበራቸው ነጥብ ላይ አንድ ጨምረው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም በ27 ነጥብ ሊጉን መምራቱን ሲቀጥል ፋሲል ከተማ ደግሞ ቀአንድ ነጥብ አንሶ በ26 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።


👉 መቐለ 70 እንደርታ ለተከታታይ ሽንፈቶቹ አፀፋ ሰጥቷል

በ14ኛ ሳምንት የመጀመሪያ የጨዋታ ቀን ከሰሞኑ ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገዱት መቐለ 70 እንደርታዎች በዚህኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በትግራይ ዓለምአቀፍ ስታዲየም አስተናግደው የግብ ናዳ በማውረድ ሀዋሳ ከተማን መርታት ችለዋል።

የዐምና የሊጉ አሸናፊዎች መቐለ 70 እንደርታዎች ከሰሞኑ ባስተናገዷቸው ሽንፈቶች በብዙሃኑ ዘንድ በተከታታይ ዋንጫውን ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ስለመሳካቱ ጥርጣሬ ቢያጭርም የትችት ሰይፍ ሲያርፍባቸው የሰነበቱት የቡድኑ ተጫዋቾች በዚህኛው ሳምንት ጠንከር ያለ ምላሽ የሰጡ ይመስላል።

በሚጠበቀው ልክ እስካሁን ቡድኑን እያገለገለ አይገኝም ሲባል የሰነበተው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ሐት-ትሪክ በሰራበት በዚሁ ጨዋታ አለልኝ አዘነን ገና በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለተኛ ቢጫ ያጡትን ሀዋሳ ከተማዎች ቁጥር መጉደልን መቐለዎች በአግባቡ መጠቀም የቻሉ ሲሆን በዚህም 5 ግቦችን አስቆጥረው ማሸነፍ ችለዋል። በዚህም ከአናታቸው የሚገኙት ፋሲል እና ጊዮርጊስ ነጥብ መጋራትን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 25 በማሳደግ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት ነጥብ አንሰው በሦስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅተዋል።


👉 መሻሻሉን በውጤት ያልገለፀው ኢትዮጵያ ቡና

ከሰሞኑ የውጤት ቀውስ ውስጥ ይገኝ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ14ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሰበታን በገጠሙበት ጨዋታ ከሰሞኑ የተሻሻለን እንቅስቃሴ ቢያሳዩም ዕድል ከእነሱ ጋር ባመሆኗ የሦስት ነጥብ ርሃባቸውን ለማስታገስ አሁንም ቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ለመጠበቅ ተገደዋል።

ቡናዎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከሰበታ ያልተደራጀ ጫና (Pressing) ጋር ተዳምሮ ካለፉት ጥቂት ጨዋታዎች በተሻለ ኳስን ከኃላ እየመሰረቱ ሲወጡ እንዲሁም በርከት ያሉ የጠሩ የግብ እድሎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም የተገኙትን አጋጣሚዎች መጠቀም ባለመቻላቸው አንድ ነጥብ ብቻ ይዘው ለመውጣት ተገደዋል።

በጨዋታው ከጉዳት ጋር እየታገለ የተጫወተውን አቡበከር ናስር በፊት አጥቂነት ይዘው የጀመሩት ቡናዎች በዚሁ ስፍራ እንዳለ ደባልቄን ከተጠቀሙባቸው ጨዋታዎች የተለየ መልክ እንዲኖራቸውና የስልነት መልክ እንዲላበሱ አስችሏቸዋል። አቡበከር በጨዋታ ባህሪው ከእንዳለ በተሻለ ፊቱን ወደ ተጋጣሚ ግብ አድርጎ የሚጫወት ተጫዋች በመሆኑ የቡና የመሀል ሜዳ ተሰላፊዎች ተጫዋች የሚደርጓቸውን ሰንጣቂ ኳሶች በመጠቀም ሆነ ቡድኑ በተለይ ተጋጣሚን ለማስከፈት በሚቸገርባቸው የጨዋታ ሂደቶች ይጎድለዋል ተብሎ የሚነሳበትን ተገማች ያልሆነ በሜዳኛው የላይኛው ክፍል የሚደረጉ ሆነ በሳጥን ውስጥ ያለው አካላዊ ተፅዕኖ የቡናን የፊት መስመር የተሻለ መልክ አላብሶት ለማስተዋል ችለናል።

ቡድኑ አሁንም አጋጣሚዎችን ወደ ግብ በመቀየር ረገድ ችግሮች ቢስተዋሉበትም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ግብ ለመድረስ ይከተሉት የነበረው መንገድ ተገማች ለነበረው ቡድናቸው ሌላ የማጥቂያ መንገድ ይዞ መምጣቱ እንቅስቃሴዎችምለደጋፊዎች ተስፋ የሰጠ ሆኗል።


👉 አዳማ በሜዳው የነበረውን ሞገስ መልሶ ያገኘ ይመስላል

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ላይ በሜዳው የነበረውን አስፈሪነት ያጣ ይመስል የነበረው አዳማ ከተማ አሁን ላይ ግን ወደቀደመ ጥንካሬው የተመለሰ ይመስላል። በዚህኛው ሳምንትም በቅርቡ ከዋና አሰልጣኙ ጋር የተለያየው ወልዋሎን ጋብዞ በአማኑኤል ጎበና እና ቡልቻ ሹራ ግቦች 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

በተከታታይ ባደረጋቸው ሦስት የሜዳ ላይ ጨዋታዎች ከተሻሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ድል ማድረግ የቻሉት አዳማ ከተማዎች አሁንም እልባት ባልተገኘለት የደሞዝ ጉዳይ ውስጥ ቢሆኑም ተጫዋቾቹ ያሉባቸውን ጫናዎች ተቋቁመው በተለይ በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ለቡድናቸው ከፍተኛ ግልጋሎት እየሰጡ ይገኛል።


👉 ከስህተቱ የማይማረው ድሬዳዋ ከተማ?

ፕሪምየር ሊጉን ዳግም ከተቀላቀሉበት 2008 ጀምሮ በወራጅ ቀጠናው አካባቢ እንደ ድሬዳዋ ከተማ በተደጋጋሚ ያንዣበበ ቡድን ፈልጎ ማግኘት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። በዘንድሮው የውድድር ዘመንም ምንም እንኳን በሊጉ ሰንጠረዥ የነጥብ መቀራረቦችን ቢኖሩም ከወዲሁ በ14 ነጥብ በወራጅ ቀጠና ውስጥ (በ15ኛ ደረጃ ላይ) ይገኛሉ። ላለፉት ዓመታት ከመውረድ ለጥቂት እየተረፉ የፕሪምየር ሊግ እህል ውሃቸውን እያስቀጠሉ የሚገኙት ድሬዳዎች አሁን በተመሳሳይ የኃልዮሽ መንገድ ጉዟቸውን ቀጥለዋል።

በዚህኛው ሳምንት ሙሉ ክፍለ ጊዜውን ለማለት በሚያስችል ሁኔታ በጎዶሎ በተጫወተው ጅማ አባ ጅፋር የ2ለ1 ሽንፈት ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ መሻሻሎችን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ዘንድሮ ላለፉት ዓመታት እንደ ነገሩ ሲያመልጡት የከረሙት ከሊጉ የመሰናበት እጣ ፈንታ እንደተፈራው መድረሱ አይቀሬ ይመስላል።

ከተጫዋቾች ምልመላ ጀምሮ በርካታ ክፍተቶች የነበረበት ቡድኑን ከወዲሁ ካለበት ስጋት ለመታደግ የጅምላ ሸመታ ውስጥ ለመግባት ስለማሰቡ በስፋት እየተወራ ይገኛል። ይህም ለቡድኑ ይዞት ከሚመጣው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ በማተኮር የቡድኑን ችግር የሚቀርፉና ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ተጫዋቾችን በማዘዋወር ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው እሙን ነው። በተጫዋቾች ጥራት ከሌሎች ቡድኖች ጋር የተራራቀ ደረጃ ላይ የሚገኝ ባለመሆኑም ቡድኑን እንደቡድን የሚያሻሽል ቀጣይ አሰልጣኝ በጥንቃቄ መምረጥም ወሳኝ ነው። በተመሳሳይ ከሜዳ ውጭ ያሉ ጉዳዮችን በመፍታት ከሜዳ የራቀውን ደጋፊ በመመለስ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን መስራት የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ የሚገኙ ይመስላል።

እንደ ቀጠና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመና ትኩረት እየተነፈገው በመጣው የምስራቅ ኢትዮጵያ እግርኳስ አንድ ለእናቱ የሆነው ድሬዳዋ ከተማ ከሊጉ የሚወርድ ከሆነ የሚኖረው ተፅዕኖ ከከተማዋ አልፎ እንደ ቀጠና እጅግ ከፍ ያለ እንደመሆኑ ቡድኑን ማትረፍ ከአመራሮቹ የሚጠበቅ ከባድ የቤት ሥራ ይሆናል።


👉 ሲዳማ ቡና ወሳኝ የሜዳ ውጭ ድሉ እና አንድምታው

ወጣ ገባ የሆነ የውድድር ዘመን እያሳለፉ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በ14ኛ ሳምንት ወደ ወልቂጤ አቅንተው በይገዙ ቦጋለ ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ራሳቸውን የመለሱበትን ድል አሳክተዋል። ብቸኛው ከሜዳ ውጭ ጨዋታን ያሸነፈ የዚህኛው ሳምንት ቡድን የሆኑት ሲዳማዎች የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ መጠነኛ መሻሻልን በጨዋታው ላይ በማሳየት በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከሜዳቸው ውጪ ጎል ሳያስተናግዱ ተመልሰዋል። ይህም አሰልጣኝ ዘርዓይ በቀጣይ ጊዜያት በቡድኑ ላይ ተስፋን እንዲሰንቁ ያደረገ የጨዋታ ሳምንት ነበር።

ምርጥ የአጥቂ ክፍል ጥምረትን ከደካማ የመከላከል አጨዋወት ጋር አጣምሮ የያዘው ቡድኑ በክረምቱ ከለቀቀው ፈቱዲን ጀማል በኋላ የኋላ መስመሩ የሚያፈስ ሆኗል። በተናጠል ከተጫዋቾች ድክመት በተጨማሪ ቡድኑ እንደ ቡድን ያለው የመከላከል አጨዋወት ድክመትም ሳይዘነጋ ጠንካራና የመከላከል አደረጃጀቱ መሪ የሚሆን ተከላካይ የሚፈልግ ይመስላል። በዚህም ቡድኑ በሁለተኛው ዙር የተጫዋቾች እና የአጨዋወት ማሻሻያ ከኋላ ክፍሉ ይጠበቃል።

ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ6 ነጥብ ርቀው በ4ኛ ደረጃ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች የወልቂጤውን ድል እንደመነሻ በመቁጠር የመጀመሪያውን ዙር በድል አድራጊነት ለማጠናቀቅ በማለም በቀጣዩ ሳምንት ሰበታ ከተማን የሚያስተናግዱ ይሆናል።


👉 የሜዳ ውጪ ድል እንደሰማይ የራቀው ባህር ዳር ከተማ

የዘንድሮው ባህር ዳር ከተማ በሜዳው ብዙ ግቦችን የሚያስቆጥር እና በተቃራኒው በርካታ ግቦችን ከማስተናገዱ በዘለለ ከሜዳው ውጪ ያለው ደካማ ክብረወሰንም ሌላኛው መገለጫው እየሆነ መጥቷል።

የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ስብስብ እስካሁን ካደረጋቸው የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች መሰብሰብ የቻለው ሁለት ብቻ ነው። ምንም እንኳን ከሜዳ ውጪ ለማሸነፍ የመቸገር ነገር ለሀገራችን ክለቦች እንግዳ ባይሆንም በሜዳ እና ከሜዳው ውጪ ጨዋታዎች ባለው እጅግ የተራራቀ የአቋም ልዩነት ምክንያት የባህር ዳር ከተማ ጉዳይ የተለየ አትኩሮትን የሚነሻ ይመስላል።

በተጫዋቾች ጉዳት እጅጉን የሳሳው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ የተሻለ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ የሚያልም ከሆነ መሰል ከሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ላይ ያሉ ድክመቶችን ማረም የግድ ይለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ