ለፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ስልጠና ሊሰጥ ነው

ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጀርመኑ ባየር ሙኒክ እግርኳስ ክለብ ጋር በመተባበር ለፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ስልጠና ሊሰጥ ነው።

ለተከታታይ አምስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ስልጠና መሠረታዊ የእግርኳስ አሰለጣጠን ትምህርቶችን በንድፈ ሀሳብ (በቪዲዮ የታገዘ) እና በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተግባር ስልጠና የሚሰጥ ይሆናል። ሰኞ የካቲት 16 ከጠዋት ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታድየም በሚሰጠው በዚህ ስልጠና ላይ የሴት እና የወንድ የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች በሙሉ እንደሚከታተሉ ለማወቅ ችለናል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ኮሚቴ የእግርኳስ ልማት ላይ ትኩረቱን በማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎችን እያዘጋጀ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይም ተከታታይነት ያለው ስልጠናዎችን በሁሉም ውድድሮች ለሚገኙ አሰልጣኞች ትምህርት ለመስጠት ማቀዱን ለማወቅ ችለናል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛው ዙር ሰኞ የሚጠናቀቅ መሆኑን ተከትሎ አሰልጣኞች ይህን ስልጠና ማግኘታቸው የበለጠ ራሳቸውን ብቁ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ