ሴቶች 2ኛ ዲቪዝዮን| ሻሸመኔ ከተማ ተከታዩን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናከረ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን 8ኛው ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ እና ቦሌ ክ/ከተማን አገናኝቶ በሻሸመኔ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የሊጉ መሪን ከተከታዩ ባገናኘው የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ ገና በጅማሬው በሁለቱም በኩልበአጥቂዎቻቸው አማካኝነት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ሆኖም በ6ኛው ደቂቃ የጨዋታው አጠቃላይ ውጤት የሚገልፅ ጎል በእንግዶቹ ሻሸመኔ በኩል ሊመዘገብ ችሏል። ሻሸመኔዎች በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ጎል አምርተው አምሳል ፍስሐ ከሳጥን ውጭ የመታችው ኳስ የግብጠባቂዋ አዛለች ነጋሽ ስህተት ታክሎበት የመጀመርያ ጎል ተቆጥሯል።

በመጀመርያዎቹ ስድስት ደቂቃዎች ሁለት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች እና አንድ ጎል መቆጠሩን ተከትሎ ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር እና ተጨማሪ ጎሎች ይቆጠሩበታል ቢባልም የሆነው ከዚህ በተቃራኒ ነው።

የሊጉ መሪ እንግዶቹ ሻሸመኔዎች ወደ ኃላ አፈግፍገው በዝተው በመከላከል በሚገኙት አጋጣሚሚዎች ወደ ጎል የሚደረግ ጥረት ሲያስመለክቱን በአንፃሩ ቦሌዎች ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ አንስቶ እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ ድረስ ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወት ቢችሉም እድለኛ አልነበሩም በሚባል ሁኔታ የጎል ዕድሎችን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በመጀመርያው አጋማሽም በህዳት ካሱ እና ሜላት ጌታቸው አማካኝነት በፍጥነት ወደ ጨዋታው መመለስ የሚያስችላቸውን አጋጣሚ አልተጠቀሙም።

ከእረፍት መልስ የቦሌዎች ብልጫ ቀጥሎ ቢውልም የሚገኙትን ዕድሎች ወደ ጎልነት የሚቀይር ተጫዋች ጠፍቶ ለመሸነፍ ተገደዋል። በተለይ ህዳት ኳሱ በ60ኛው ደቂቃ ብቻዋን ከግብጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ የመከነበት ኳስ፣ ብዙም ሳይቆይ በተመሳሳይ ሁኔታ ተቀይራ በገባችው ሜሮን አበበ ከግብጠባቂዋ አንድ ለአንድ ተገናኝታ ግቧን በትኩረት እና በጥሩ ብቃት ስትቆጣጠር የዋለችው የሻሸመኔዋ ግብጠበቂ ፅዮን ግርማ አድናባታች። በቀሩትም ደቂቃዎች በሻሸመኔ ጠንካራ መከላከል በቦሌዎች ጎል ለማስቆጠር በሚደረግ ጥረት ጨዋታው ቀጥሎ በመጨረሻም ጨዋታው በእንግዶቹ ሻሸመኔ ከተማ 1-0 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል።

11:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል ተብሎ መርሀግብር ተይዞለት የነበረው የንፋስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ከ ጥሩነሽ ዲባባ ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

error: