ሀዋሳ ከተማ የቀድሞ ተጫዋቹን በዋና አሰልጣኝነት ቀጠረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ የሆነው ሙሉጌታ ምህረት የሀዋሳ ከተማ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተሹሟል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ለ17 አመታት ያህል በተጫዋችነት አሳልፎ ነበር ከአራት ዓመታት በፊት ከእግር ኳስ በክብር የተሸኘው። የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደደቢት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ሙሉጌታ ምህረት የአሳዳጊ ክለቡ እና ለረጅም ጊዜ በአምበልነት የመራው ሀዋሳ ከተማ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ዛሬ አመሻሽ በይፋ ተቀጥሯል፡፡

እግር ኳስን ካቆመ በኋላ በወሰደው የአሰልጣኝነት ስልጠና ቢ ላይሰንስ ደረጃ በሀዋሳ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ረዳት በመሆን ከ2009 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት በረዳትነት ያገለገለው ሙሉጌታ ከ2011 ጀምሮ የአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል ሆኖ እየሰራ መቆየቱ ይታወቃል።

ሙሉጌታ ምህረት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ከክለቡ ጋር የሚያቆየውን ውል ተፈራርሟል።

© ሶከር ኢትዮጵያ