በፖለቲካውና በሚድያው ዘርፍ ላይ ንቁ ተሳትፎ ያለው የእግርኳስ ተጫዋች

ከአስር ዓመታት በፊት መቐለ ባሎኒ ሜዳ የተገኘው የወቅቱ የኢቲቪ የስፖርት ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር በጣም ቀጭን እና ያጠለቀው ማልያ የሰፋው ባለተሰጥኦ ተጫዋችን ተመልክቶ ቀጣይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተስፋ ነው ብሎ ከተናገረ በኋላ የብዙዎች ትኩረት ስቦ ነበር። 

አሁን በፕሪምየር ሊጉ ለስሑል ሽረ እየተጫወተ የሚገኘው ይህ ተጫዋች በሙሉ ስሙ ኃይለአብ ኃይለሥላሴ የሚባል ሆኖ Haileab Fidel በሚል መጠርያ በማኅበራዊ ሚድያውና በትግርኛ ቋንቋ በሚታተሙ የኅትመት ውጤቶች በፖለቲካ፣ ማኅበራዊ እና እግርኳሱ ላይ ያተኮሩ ፅሁፎች በመፃፍ ይታወቃል።

የእግር ኳስ ሕይወቱን በመቐለ 70 እንደርታ ጀምሮ ለደደቢት እና ወልዋሎ የተጫወተው ይህ አማካይ በአንድ ወቅት በተለይም የፖለቲካ ጉዳዮችን በድፍረት እየዳሰሰች አነጋጋሪ እና ተወዳጅ በነበረችው “ሰርጌን መፅሔት” በዋና አዘጋጅነት እና በምክትል ዋና አዘጋጅነት የሰራ ሲሆን በመቐለ ጥሩ የንባብ ባህል ለመፍጠር የሞከረው “የፊደል ሠራዊት የወጣቶች ቤተ መፃሕፍት” በማቋቋም ትልቅ ድርሻ ከነበራቸው መሐል አንዱ እንደነበረም ይነገርለታል።

ከሌሎች ተጫዋቾች በተለየ መልኩ ስፖርት ላይ ላሉ ግለሰቦች የማይነኩ የሚባሉ ዘርፎች ላይ የሚሳተፈው እና በታሪክ ከመቐለ ዩኒቨርስቲ የመጀመርያ ዲግሪ ያለው ኃይለአብ በተለይም በከባድ የጉልበት ጉዳት ምክንያት ለዓመታት ከሜዳ በራቀባቸው አስከፊ ግዜያት በሰርጌን መፅሔት አይረሴ ሥራዎች በመስራት የትግራይ ክልል እግርኳስ አፍቃሪውንና ወዳጆቹን አስከፊውን ግዜ በበጎው መልኩ እንዲያዩት አድርጓል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ ራሱን ለህዝብ እያስተዋወቀ ያለውና ከወዲሁ በትግራይ ወጣቶች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ብቅ ያለው፤ ብሎም በቀጣዩ ምርጫ አዲሱ የህወሓት ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው “ሣልሳይ ወያነ ትግራይ” የተባለ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆኑን በግልፅ ያስታወቀ ሲሆን በቀጣዩ ምርጫ  ይወዳደር ይሆን? የሚለውን መጠበቅ አጓጊ ያደርገዋል።

ፊቱን በጉልህ በሸፈነው ጺሙ ተለይቶ የሚታወቀው ኃይለአብ ብዙዎች ከሱ ጋር የተጫወቱ ተጫዋቾችና አንጋፋ የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ስለ ኳስ ችሎታው በጥሩ ጎኑ የሚያወሩለት ቢሆንም የአካል ብቃትና የጉዳት ተጋላጭነት ጥያቄዎች ሁሌም ያነሱበታል። በመቐለ የቀድሞ ቆይታው ከነጉዳቱ የማደንዘዣ መርፌ እየተወጋ በመጫወቱ እና የሀገሪቱ ወቅታዊ የእግርኳስ ሁኔታና አሰራር የችሎታውን ያህል እንዳይጫወት እንዳገደውም ይነገራል።

እግር ኳስ በጀመረባቸው የታዳጊ ዓመታት ክልሉን በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች የወከለ እና ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ግን በጉዳትና ከሜዳ ውጭ ባለው የህይወት ዘዬ ምክንያት እንደታሰበው ያልደመቀው አማካዩ በተለይም በ2000ዎቹ አጋማሽ  ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ያሳለፋቸው ጊዜያት በክለቡ አንጋፋ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። በዚህ ዓመት ለስሑል ሽረ እየተጫወተ የሚገኘው አማካዩ በተለይም ተቀይሮ እየገባ የሚፈጥራቸው ለውጦች በቡድኑ ደጋፊዎች ተወዳጅ አድርጎታል።

በቀጣይ እንደተጠበቀው ስላልደመቀው የእግር ኳስ ሕይወቱ፣ ስለ ሰርጌን መፅሄት ቆይታው፣ ስለ ፖለቲካዊና እግር ኳሳዊ እምነቱ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክተን ከተጫዋቹ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘንላቹ እንቀርባለን።

(ተጫዋቹ በአሁኑ ወቅት በግል ጉዳዮች ምክንያት ሽረን በስምምነት ለቆ ከዚህ ቀደም በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለተጫወተበት ደደቢት ለመጫወት ተስማምተዋል የሚል መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ)

© ሶከር ኢትዮጵያ