የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ተራዘሙ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ መሆኑ በታወጀው የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ምክንያት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገራቸውን ካፍ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በማጣርያው መጋቢት 18 እና 21 ከኒጀር ጋር በሜዳዋ እና ከሜዳዋ ውጪ ጨዋታ እንድታደርግ መርሐ ግብር ወጥቶላት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በካፍ ውሳኔ መሠረት ጨዋታዎቹ የማይደረግ ይሆናል። ካፍ ጨዋታዎቹን ከማራዘሙ መቼ ሊደረጉ እንደሚችሉ በቀር ያለው ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በማጣርያው ምክንያት ለ3 ሳምንታት እንደሚቋረጥ መገለፁ የሚታወስ ሲሆን የካፍ ውሳኔን ተከትሎ የሊጉ ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው የሚጠበቅ ጉዳይ ቢሆንም ዛሬ በኢትዮጵያ አንድ ጃፓናዊ ግለሰብ በቫይረሱ መያዙ መገለፁን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚደረጉ ውድድሮች ቀጣይ እጣ ፈንታም መቋረጥ እንደሚሆን ይገመታል።

ዐለም አቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ በተመሳሳይ ከትላንት በስቲያ አዲስ አበባ ላይ ሊደረግ የነበረውን የፊፋ ኮንግረስ ወደ መስከረም 2013 ማሸጋገሩ ይታወሳል።

©ሶከር ኢትዮጵያ