ሪፖርት | አሰልቺው ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል

ከዛሬ የ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል ወላይታ ሶዶ ላይ የተደረገው የወላይታ ድቻ እና የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቋል።

ወላይታ ድቻ በ16ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና ከተሸነፈበት አሰላለፍ ላይ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ አዲስ ፈራሚዎቹ አበባው ቡታቆ እና አማኑኤል ተሾመን እንዲሁም ጉዳት ላይ የነበረው ደጉ ደበበን በማሰለፍ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን እንግዳው ቡድን ወልዋሎ በአንፃሩ በሜዳው ከሰበታ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ውስጥ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ሄኖክ መርሹ እና ዐወል አብደላን በመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ አካቷል።

ከሙሉ ዘጠና ደቂቃው የተሻለ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች የተሻሉ ነበሩ። የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በማድረግም ቀዳሚ የነበሩት ድቻዎች ሲሆኑ በ9ኛው ደቂቃ አበባው ቡታቆ ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ አንተነህ ጉግሳ በግንባሩ ገጭቶት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሞከሩት ባለሜዳዎቹ በፈጠሩት ዕድል በ13ኛው ደቂቃ እድሪስ ሰይድ እና ባዬ ገዛኸኝ በጥሩ አጨዋወት ተቀባብለው ያመጡትን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ቢሞክርም ምቱ ጠንካራ ባለመሆኑ በግብ ጠባቂው በቀላሉ ተይዞበታ። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ እድሪስ ሰዒድ ከመስመር ላይ ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው አብዱልአዚዝ በግሩም ብቃት አወጣው እንጂ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር።

እንግዶቹ ወልዋሎዎች ረጃጅም ኳሶችን በመጣል አደጋ ለመፍጠር ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቀር ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉትም 22ኛ ደቂቃ ላይ በራምኬል ሎክ አማካኝነት ከቅጣት ምት ቢሆንም ግብ ጠባቂው መክብብ በቀላሉ ይዞታል። በጭማሪ ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ አንተነህ ጉግሳ በግንባር ሲገጭ የወልዋሎ ተከላካዮች አውጥተውበታል። በዚህ አጋጣሚ ‘የወልዋሎ ተጫዋች ኳስ በእጅ ነክቷል’ በማለት የድቻ ተጫዋቾች ዳኛውን ቢከቡትም ፌደራል ዳኛ ሀብታሙ መንግስቴ ጨዋታው እንዲቀጥል አዘዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም በዚሁ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽም ብዙ ሙከራ ያልተደረገበት ነበር። በአንፃሩ የተጫዋቾች ግጭት እና ጥፋቶች እንዲሁም የወልዋሎ ተጫዋቾች ሰዓት የማባከን ሂደት የታየበት ነበር። በ53ኛ ደቂቃ ከአማኑኤል ተሾመ በረዥሙ የተሻገረለትን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ከርቀት ሞክሮ የወልዋሎ ተከላካዮች ተደርበውበት ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል። ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሻሽለው የገቡት እንግዶቹ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲያደርጉ የነበረው ጥረትም ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል። 87ኛው ደቂቃ አንተነህ ጉግሳ ለቡድን አጋሩ ሲያቀብል ኳስ ለወልዋሎው ያሬድ ብርሃኑ ደርሳው ከመሐል ሜዳ ገፍቶ ይዞ በመግባት ቢሞክርም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበት ጨዋታው ያለምንም ግብ ተጠናቋል። የጨዋታው ማጠናቀቂያ ፊሽካ ሲሰማ የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች የተጨመረው ደቂቃ በቂ አይደለም በማለት የዳኛውን ውሳኔ ተቃውመዋል።

የአቻ ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በ22 ነጥቦች 11ኛ ወልዋሎ ደግሞ በ18 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ