የሲዳማ ቡና የቡድን አባላት አሁንም በሽረ ይገኛሉ

በሽረ እንዳሥላሴ ከተማ በተነሳው ከፍተኛ አቧራማ ንፋስ የተነሳ የሲዳማ ቡና የቡድን አባላት ወደ አዲስ አበባ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ እክል ፈጥሮባቸዋል።

ትላንት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ17ኛው ሳምንት መርሐግብር ወደ ሽረ አምርተው 2ለ1 ተሸንፈው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ዛሬ ከከተማዋ ለመውጣት ቢያስቡም ከተማ ውስጥ ባለው ከፍተኛ የአቧራ አውሎ ንፋስ አሁንም በከተማው ላይ ይገኛሉ፡፡ ትላንት ረፋድ ላይ በሽረ ከተማ በተነሳው ከፍተኛ የአቧራ አውሎ ንፋስ የተነሳ ከተማዋ ገና በጊዜ ጨላልማ የታየች ሲሆን የስሑል ሽረ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታም በዚህ ከባድ የአየር ፀባይ ታጅቦ በስሑል ሽረ 2ለ1 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በዕለቱ ጨዋታ ላይ የሁለቱም ክለብ ተጫዋቾች ለመጫወት ቀርቶ ለመተንፈስ ሲቸገሩ ሶከር ኢትዮጵያ ሁነቱን ተከታትላለች፡፡

የሲዳማ ቡና የቡድን አባላት ዛሬ 3:00 ላይ ከተማዋን ለቀው ለመውጣት ቢያስቡም ዛሬም ሁኔታው በመቀጠሉና በረራ ለማድረግ ምቹ ባለመሆኑ የተሰረዘ ሲሆን ዛሬ በዛው እንደሚያድሩ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ምናልባትም ይህ ጉም መሰል አቧራማ የአየር ፀባይ ለውጥን ካሳየ ነገ ረፋድ ከሽረ ተነስተው አዲስ አበባ እንደሚገቡ የሚጠበቅ ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን በጉዟቸው ላይ ሌላ ተጨማሪ ጊዜያትን ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ