ሲዳማ ቡና ናይጄሪያዊውን ተከላካይ ለማስፈረም ተስማማ

ከአንድ ሳምንት በፊት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በስምምነት የተለያየው ናይጄሪያዊው ተከላካይ ላውረንስ ኤድዋርድ የሁለተኛው ዙር የሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ፈራሚ ለመሆን ተቃርቧል፡፡

የቀድሞው የካርባያ፣ አልሲናት እና የቱኒዚያው ኢትዋል-ደሳሀል ተጫዋች ቀጣይ ማረፊያው ሲዳማ ቡና ሊሆን ከጫፍ ደርሷል፡፡ በማጥቃቱ ረገድ በሊጉ ጠንካራ የሚባለው ሲዳማ ቡና ተጫዋቹን በጥቂት ቀናት ውስጥ በእጁ በማስገባት የነበረበትን ከፍተኛ የመከላከል ችግር ለመቅረፍ አልሞ ዝውውሩን ሊፈፅም እንደቻለ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በክረምቱ የኢራቁን ክለብ አልካርባላን በመልቀቅ መቐለ 70 እንደርታን የተቀላቀለው ግዙፉ ናይጄሪያዊ የመሐል እና የግራ መስመር ተከላካይ ላውረንስ ኢድዋርድ አግቦር በመቐለ ከመጀመሪያው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች በዘጠኙ ላይ ተሰልፎ መጫወቱ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ለሁለት የውጪ ሀገር የተከላካይ እና የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች የሙከራ ዕድልን ሰጥቶ የነበረው ሲዳማ ተጨማሪ ተጫዋች እንደማያስፈርም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

©ሶከር ኢትዮጵያ