የፕሪምየር ሊጉ ዕጣ ፋንታ ምክረ ሀሳብ ተጠየቀበት

የ18ኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊግ ጨዎታዎች መጋቢት 12 እና 13 እንዲደረግ አወዳዳሪው አካል ቢወሰንም በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ የቀን ለውጥ ሊደርግበት ይችላል።

ዛሬ ጠዋት አወዳዳሪው አካል (የፕሪምየር ሊግ ሼር ካምፓኒ) የውድድሩን ቀጣይ እጣ ፋንታ ለመወሰን ይረዳው ዘንድ ወደ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ደብዳቤ መላኩ የታወቀ ሲሆን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ቀጣይ ጨዋታዎችን በምን መልኩ ማካሄድ እንደሚገባው አቅጣጫ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮርና ቫይረስ በኢትዮጵያ ባሳለፍነው ዓርብ በአንድ ጃፓናዊ ላይ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ በትናንትናው ዕለት ቁጥሩ ወደ አራት ከፍ ባለበት በዚህ ወቅት የፕሪምየር ሊጉ እና ሌሎች ከፍተኛ የሰዎች ቁጥርን በአንድ ላይ የሚያሰባስቡ ክንውኖችን ማካሄድ ይበልጥ አደገኛ እንደሆነ ይታመናል።

ከፕሪምየር ሊጉ ጋር በተያያዘ ዜና የቀጣይ ሳምንት ጨዋታዎች ከቫይረሱ በተጨማሪ ሌላ ስጋት ተጨምሮባቸዋል። በሰሜናዊሀገሪቱ ክፍል የተነሳው ከፍተኛ ነፋስ የአየር በረራዎችን በማስተጓጎሉ በትግራይ እና አማራ ክልል የሚገኙ ክለቦችን እና በዚያ ለጨዋታ የተገኙ/ መጓዝ የነበረባቸው ቡድኖችን እንቅስቃሴ ገድቧል። ይህ የአየር ሁኔታ በቀጣይ ቀናት ካልተስተካከለም ችግሩ ተፅዕኖ የፈጠረባቸው ቡድኖች ጨዋታዎች ላይ የመርሐ ግብር ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ