የቀድሞ እና የአሁን የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋችች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚፈጠረው ማኅበራዊ ቸረግር ለማቃለል የሚያግዝ ቁሳቁስ የቀድሞ እና የአሁኖቹ ኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ማሰባሰብ ጀምረዋል።

ባሳለፍነው ቀን የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ አባላት እና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማኀበራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ በማለት እያንዳንዳቸው በግል 300 ሳሙና በመለገስ የጀመሩት በጎ ተግባር ተጠናክሮ እየቀጠለ ይገኛል። የዚህ አካል የሆነ እንቅስቃሴም ዛሬ ከሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም የቀድሞ እና የአሁኖቹ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ለአቅመ ደካሞች የሚውል ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ለማኅበሩ አስረክበዋል።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው በዚህ በጎ ተግባር ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ ዕድሉ ደረጄ፣ አብዱራህማን ሙባረክ፣ ኤልያስ ማሞ፣ አቡበከር ናስር፣ መስዑድ መሐመድ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ኤፍሬም ወንድወሰን፣ ጀማል ጣሳው፣ አህመድ ረሺድ እና ሌሎችም አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

ይህ መልካም ተግባር ሰኞ ሲቀጥል የቀድሞ እና የአሁኖቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በአዳነ ግርማ መሪነት መሰል ድጋፎቾች በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚሰበሰብ ለማወቅ ችለናል።

ከዚህ በተጨማሪ ይህን በጎ ተግባር ለማገዝ የሚፈልጉ ሌሎች የማኅበሩ አባላት እና የስፖርት ቤተሰቦች ማኅበሩ ባዘጋጀው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት መለገስ የሚችሉ መሆኑን ማኅበሩ አስታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ