ለኮሮና ቅድመ መከላከል እየተደረጉ ያሉ ድጋፎችን የተመለከቱ አጫጭር መረጃዎች…

በእግርኳሱ ዙሪያ ያሉ አካላት ለኮሮና ቫይረስ ቅድመ መከላከል እያደረጉ ያሉትን መረጃዎች በአጫጭሩ እንዲህ አቅርበናቸዋል፡፡

-የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተደረገ የሚደረገውን ዘመቻ የመደገፍ ሥራውን አጠናክሯል፡፡ የባንክ አካውንት በመክፈት በሀገሪቱ የሚገኙ ተጫዋቾች ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ሲሆን በዚህም በጎ ምግባር በርካታ ተጫዋቾች ገንዘብ ወደ አካውንቱ በማስገባት ተሳትፎን እያደረጉ ይገኛሉ። በነገው ዕለትም የተሰበሰበውን ለሚመለከተው አካል የሚያስረክቡ ይሆናል፡፡

-እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋቾች ማኅበር ሁሉ ሁለት የመከላከያ ተጫዋቾች ማለትም ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ እና ተከላካዩ ምንተስኖት ከበደ በራሳቸው ስም በተከፈተ የባንክ አካውንት እንዲሁም ደግሞ የቴሌግራም ግሩፕንም ጭምር ከፍተው ተጫዋቾችን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀስቀስ ተሳታፊ እያደረጉ ሲሆን ተጫዋቾችም ወደ ተዘጋጀላቸው የባንክ አካውንት ከአምስት ሺህ ብር ጀምሮ አስገብተዋል። ይህንንም የተሰበሰበውን ገንዘብ በዚህ አንድ ቀን ውስጥ እንደሚያስረክቡ ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

-የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ አሰልጣኞች ማኅበር ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ እንዲውል የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ማኅበሩ ባደረገው ስብሰባ ከሀያ ሺህ ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስረክቧል፡፡

-የመዲናይቱ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በከተማው ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቦታዎች ተጫዋቾችንም ሆነ ባለሀብቶችን በማስተባበር እጅግ አስገራሚ መልካም ተግባራትን እየፈፀሙ ይገኛል፡፡ በከተማው ውስጥ የሚኖሩ አቅመ ደካማ እና በአልጋ ላይ ላሉ ታማሚዎች የገንዘብ እንዲሁም የምግብ እህል በመሰብሰብ በስጦታ መልክ እየሰጡ ሲሆን በተለይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የክለቡን ተጫዋች አህመድ ረሺድን ከፊት አድርገው በርካታ ሰብዓዊ የሆኑ ስራዎችን እየሰሩ ለማህበረሰቡ ደራሽነታቸውን አሳይተዋል፡፡ የረጅም ዓመት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ የሆኑት አቶ ጀማል አህመድም ይህ መልካም እንቅስቃሴ ለመደገፍ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የስምንት ሚሊዮን ብር ድጋፍን ከሰሞኑ አድርገዋል፡፡

-የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የኮሮና ቫይረስን ለመግታት የድርሻችንን እንወጣ በማለት አላማውን ተቀላቅለውታል፡፡ ክለቡ ከዚህ ቀደም በተለያየ መልኩ ድጋፎችን ያደረገ ሲሆን አሁን ደግሞ የደጋፊ ማህየኅበሩ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራን ጀምሯል፡፡ ሁሉንም አካላት ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ ባለ 20 እና 30 ብር ትኬቶችን በማዘጋጀት ትኬቱም ተሽጦ ለጎንደር ከተማ አስተዳደር ለማስረከብ በዚህ ሳምንት የትኬት ሽያጩን ማከናወን ጀምሯል፡፡

-የወልቂጤ ከተማ ክለብ ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ቡድኑ አጠቃላይ አባላት ጀምሮ በቅርቡ የገንዘብ ድጋፍን ያደረጉ ሲሆን አሁን ደግሞ በወልቂጤ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የክለቡ ደጋፊዎች የቁሳቁስ ፡ የእህል እና ገንዘብ ማሰባሰብ ስራንም ማከናወን ጀምረዋል፡፡

-በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ የክለብ እና የፕሮጀክት አሰልጣኞች በከተማው በመዘዋወር የኮሮና ቫይረስን ከሀገራችን ለማጥፋት የድርሻቸውን ለመወጣት ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ አሰልጣኞቹ ከተለያዩ አካላት ገንዘብ በመሰብሰብ ከራሳቸውም ኪስ በማውጣት አቅመ ደካማ ለሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚሆን እህል እና የንፅህና መጠበቂያን በመግዛት ለማስረከብ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በትላንትናው ዕለት የወልቀ ከተማው ተጫዋች አዳነ ግርማ ፡ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አስቻለው ታመነ እና ጋዲሳ መብራቴ የሀዋሳ ከተማው አጥቂ እስራኤል እሸቱ እንዲሁም ደግሞ የደቡብ ፓሊስ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሀዋሳ ከተማ በመዟዟር የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራን ሲሰሩ የታየ ሲሆን እጅ በማስታጠብ ለህዝቡም ግንዛቤ ሲያስጨብጡ ውለዋል፡፡

-አምስት ተጫዋቾች በሰፈራቸው ለእጅ መታጠቢያ የሚያገለግል ታንከር ገዝተው ለአካባቢያቸው ግልጋሎት ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡ በአዲስ አበባ ተክለሀይማኖት አካባቢ ይህን ለአካባቢው ነዋሪ ያበረከቱት ዐወት ገብረሚካኤል፣ ዋለልኝ ገብሬ፣ ካርሎስ ዳምጠው፣ አፈወርቅ ኃይሉ እና ስንታየው ሰለሞን ናቸው፡፡

-የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ነው፡፡ አዲስ አበባ ጃንሜዳ በተለምዶ ኮርያ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የባህርዳር ከተማው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እንዲሁም አማካዩ ሚኪያስ ግርማ፣ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ እና ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በጋራ በመሆን በሰፈራቸው ባነሮችን በማሰራት ህብረተሰቡ የቁሳቁስ እና የገንዘብ ስጦታን እንዲያበረክት ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ከትላንት ጀምሮ ይህ የማስፈፀም ስራቸውን ጀምረዋል፡፡

-የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሉሲዎቹ አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ በግል ተነሳሽነቷ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ጥረት ማድረግ ጀምራለች። አሰልጣኟ የባንክ አካውንት በመክፈት ሁሉም በሀገሪቷ የሚገኙ አሰልጣኞች በአካውንቱ ገንዘብ በማስገባት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ እያደረገች ሲሆን በቅርቡም የተሰበሰበውን ገንዘብ በማጠናቀቅ እንደምታስረክብ ሰምተናል።

-የኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋቾች ማኅበር ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ተጫዋቾች የገንዘብ ድጋፍን በማኅበሩ በኩል ፈፅመዋል፡፡ ከክለቡ ተጫዋቾች የተሰበሰበ ከ21 ሺህ ብር በላይ ነው የለገሱት፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ