የጅማ አባጅፋሩ አጥቂ መልካም ተግባር …

የጅማ አባጅፋሩ አጥቂ አምረላ ደልታታ ለአንድ ወር ያህል በትውልድ ከተማው ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ እንዲውል ከጎደኞቹ ጋር በመሆን ያደረገውን የማሰባሰብ ስራ አገባዷል፡፡

በዘንድሮው የውድድር አመት አዳማ ከተማን በመልቀቅ ወደ ጅማ አባጅፋር አምርቶ እየተጫወተ የሚገኘው አምረላ ደልታታ ተወልዶ ባደገበት ስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ ዓለምገበያ ከተማ ላይ ያለፉትን አንድ ወራት በግሉ ሀሳብ ጠንሳሽነት ሁለት የስልጤ ወራቤ ተጫዋቾችን በመጨመር በከተማው እና በወረዳው ባሉ 34 ቀበሌያት ላይ ለአቅመ ደካማ እና ራሳቸውን መደጎም ላቃታቸው ግለሰቦች ሲያሰባስብ የነበረውን የገንዘብ እና የእህል ማሰባሰብ ስራን አጠናቋል፡፡

ተጫዋቹ ሀሳቡን በማንሳት ጓደኞቹንም የዚህ መልካም አላማ አጋዥ በማድረግ በጋራ ሆኖ በወረዳው ባሉ ሁሉም ቀበሌያት ከግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ጀምሮ ወደ ተለያዩ የገቢ ማሰባሰብ ስራ በመግባት በተለይ በአካባቢው የገበያ ቀንን በመጠበቅ እና ከከተማው ማህበረሰብ ገንዘብ እና የእህል ጥራጥሬን በመሰብሰብ ለተቸገሩ ወገኖች እንዲሆን አድርጓል፡፡ በጥሬ ገንዘብ ወደ ሁለት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሺህ ብር የሚጠጋ እንዲሁም ደግሞ ቀሪው ብር በእህል መልክ በጠቅላላው ወደ አራት መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ ግምት ያለውን በጥሬ እና በእህል መልክ ለወረዳው አስተዳደር ለመልካም አላማ እንዲውል አበርክቷል፡፡ ተጫዋቹ አሁን ሲያደርግ የነበረውን የአንድ ወር በጎ ምግባርን ለጊዜው ቢያጠናቅቅም አሁንም ይህ በሽታ ከሀገራችን እስኪጠፋ ከማኅበረሰቡ ጎን እንደማይለይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ