በዳሶ ሆራ የት ይገኛል ?

በመከላከያ እና ሙገር በቆየባቸው ዓመታቶች በጠንካራ ተጫዋችነቱ የሚታወቀው ግዙፉ አጥቂ በዳሶ ሆራ የት ይገኛል?

በባቱ ከተማ (ዝዋይ) ተወልዶ ያደገው በዳሶ በሻሸመኔ ከተማ፣ በኢትዮጵያ መድን በኃላም በሙገር ሲሚንቶ ተጫውቶ አሳልፏል። ሙገር ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ ከ2003 ጀምሮ ስኬታማ ቆይታ ወዳደረገበት መከላከያ በማቅናት መጫወት ከመቻሉ ባሻገር የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ማንሳቱ ይታወቃል። በእንግሊዛዊው ኤፊ ኦኑራ እና ቤልጅየማዊው ቶም ሴይንትፌት የአሰልጣኝነት ዘመንም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት ችሏል። ከመከላከያ ጋር ከተለያየ በኃላ ወደ አዳማ ከተማ በማቅናት በሴካፋ የክለቦች ዋንጫ ላይ መሳተፍ ችሎ የነበረ ቢሆንም ከጉዳት ጋር ተያይዞ በአዳማ የታሰበውን አገልግሎት ሳይሰጥ በመቅረቱ ተለያይቷል። ከዚህ በኃላ ለሙገር ከፍተኛ ሊግ፣ ለሰ/ሸ/ደብረ ብርሀን ደግሞ ብሔራዊ ሊግ ከተጫወተ በኋላ ያለፉትን ሁለት ከእይታ እርቆ ይገኛል። ይህ ግዙፍ አጥቄ የት ይገኛል በማለት ፈልገን አግኝተን አናግረነዋል።

” በመጀመርያ የት ይገኛል ብላችሁ አስባችሁ ስለጠየቃችሁኝ አመሰግናለው። እግርኳስ ምንያህል ከሰዎች ጋር መግባባት እንደሚያስፈልግ ያወኩት አሁን ነው። ቀድሞ ስራችን ጠንክረን መስራት ላይ ብቻ የምናተኩር በመሆኑ ሌላ ምንም ግንኙነት አልነበረንም። ከመከላከያ ከወጣው በኃላ የጉዳት ሁኔታ እና የተለያዩ ምክንያቶች የእግርኳስ ህይወቴ እንዳሰብኩት አልሄደልኝም። አሁን በግሌ ልምምድ እየሰራሁ እገኛለው እግርኳስ ግን አላቆምኩም ። እዚሁ አዲስ አበባ ከባሌቤቴና ከወንድ እና ከሴት ልጆቼ ጋር አብሬ የግል ሥራ እየሰራው እየኖርኩ እገኛለው። አንዳንዴ እግርኳስ ውለታ አያውቅም። እስቲ ነገሮች ይስተካከሉና ዳግመኛ ወደምወደው እግርኳስ እመለሳለሁ”።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ