የልጅነት ህልሙን ዕውን ያደረገው ቢንያም አሰፋ…

ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ጥሩ አጥቂዎች አንዱ ነው። ከተለመዱት የፊት አጥቂዎች በተለየ ባለተስጥኦ መሆኑ እና የግራ እግሩ ጠንካራ ምት መለያው ነው። በኒያላ፣ በወንጂ ስኳር፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በሰበታ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (በሦስት ጊዜያት)፣ ጅማ አባ ቡና እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫውቶ አሳልፏል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አራት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ከማንሳቱ ባሻገር በ1998 የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። በኢትዮጵያ ታዳጊ ቡድን፣ ኦሊምፒክ እና በዋናው ብሔራዊ ቡድን መጫወት ችሏል። በተለያዩ ዓመታት የኮከብ ጎል አግቢነት ፉክክር ውስጥ መግባት የቻለው ቢንያም በአጠቃላይ በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ልናወራ በቀጠሮ መለያየታችን ይታወሳል። እነሆ ከእድገቱ እስከ እግርኳስ ያቆመበት ጊዜ ድረስ ያለውን የእግርኳስ ህይወቱን በዚህ መልኩ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ

ትውልድ እና ዕድገትህ አጠቃላይ የቤተሰብ ህይወትህን በመጠየቅ ልጀምር ?

የተወለድኩት አዲስ አበባ አራት ኪሎ ቅድስተ ማርያም አካባቢ ነው። በዚህ ሠፈር እስከ ስምንት ዓመቴ ድረስ ኖሬያለሁ። ሆኖም ብዙም በዚህ አካባቢ ሳንቆይ ቤተሰቦቼ የቤት ለውጥ አድርገው ወደ ሀያ ሁለት አካባቢ ልናመራ ችለናል። ለቤተሰቤ ሁለተኛ ልጅ ነኝ፤ አንድ ታላቅ ወንድም አንድ ታናሽ እህት አለችኝ። ከቤተሰቤ መሐል እግርኳስን ተጫውቶ ያለፈ የለም፤ እኔ ብቻ ነኝ ።

ከቤተሰብ ተጫውቶ ያለፈ ከሌለ እግርኳስ ተጫዋች እንድትሆን መነሻ የሆነ ምክንያት ምንድን ነበር ?

አራት ኪሎ እያለሁ አንድ ጎረቤታችን እግርኳስ ይጫወት ነበር። እርሱ ተጫውቶ ሲመጣ ትጥቁን እየተቀበልኩ አጥባለው፣ ምግብ ሲመገብ አብሬው እበላለው። ከዛን ጀምሮ ይመስለኛል የኳስ ፍቅር በውስጤ ያደረው። አራት ኪሎ የነበረኝን ፍላጎት ይዤ ነው ወደ ሀያ ሁለት አዲስ ሰፈራችን የመጣሁት። እዚህም ከመጣው በኃላ ሰፈሩ እግርኳስ ለመጫወት በጣም አመቺ ነበር። ብዙ የሚጫወቱ በእኔ እድሜ ያሉ ህፃናት እና በርከት ያሉ ሜዳዎች የነበሩ መሆናቸው እግርኳስን መጫወት ጀመርኩ። ትምህርት ቤትም በተመሳሳይ እጫወት ነበር። ፍቅሩ እያደረብኝ ሲመጣ ከቤተሰብ በኩል ደግሞ ጫና ነበር። ትምህርቴ ላይ ትኩረት እንዳደርግ ግፊቶች ነበሩ። እኔ ግን ከትምህርቱ ይልቅ ወደ እግርኳሱ አድልቼ ትምህርት ቤት በማንኛውም ሰዓት በሚገኙ እረፍቶች ሁሉ ኳስን መጫወት አዘወትር ነበር። በጣም የሚገርመው ኳስ ተጫውቼ ወደ ክፍል ስገባ ላብ በላብ ሆኜ ስለመገባ አስተማሪዎቼ በጣም ይናደዱ ነበር። ‘እንተን እንዲህ ሆነህ እየመጣህ አንተን ማስተማር አንችልም፤ ኳስ እንዳትጫወት’ ይሉኝ ነበር። እንዲያውም ትዝ ይለኛል ከእህቴ እና ከእናቴ ጋር ሆነን በአዲስ አበባ ስታዲየም ስናልፍ በሩን አጥሩን እያየሁኝ እዚህ ሜዳ ላይ አንድ ቀን ተጫውቼ ብሞት አይቆጨኝም ብዬ የተናገርኩትን አሁንም ድረስ እህቴ እያነሳችው ስታውሰኝ በጣም ነው የሚገርመኝ። በአጠቃላይ የነበረኝ ፍላጎት ፍቅሩ ኳስ ተጫዋች ለመሆን ምክንያት ሆኖኛል።

ይህ ፍቅር ታዲያ እውን የመሆን መሠረቱ በየትኛው ክለብ በመጫወት ጀመረ ?

ያለው ባለሁበት አካባቢ ቅ/ገብርኤል ሆስፒታል እና ኢንጂን ዲዛይን የሚባሉ የተቋቋሙ ክለቦች ነበሩ። ትልቅ ባይባሉም እዚህ ነው መጫወት የጀመርኩት። መኳንንት ሰፈፈ የኢንጅን ዲዛይን አሰልጣኝ ነበር። እርሱ እያሰራኝ መጫወት የጀመርኩ ጊዜ ነው ትክክለኛ የእግርኳስ ህይወቴ መሠረት የተጣለው እና ደረጃዬን ከፍ ማድረግ የጀመርኩት። ከዚህ ክለብ መነሻነት ነው ወደ ትልቅ ክለቦች መሻገር የቻልኩት።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ጋር በሁለት አጋጣሚዎች በተለያዩ ክለቦች የመሰልጠን አጋጣሚ አግኝተሀል…

ከኢንጂል ዲዛይን በኃላ ወደ ኒያላ ነው ያመራሁት። በጊዜው ገና ልጅ ስለነበርኩ ካስፈረሙኝ በኃላ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እኔን ወደ ዝግጅት ይዞ ለመሄድ በጣም ተቸግሮ ነበር። ምክንያቱም ይህ ህፃን ነው እንዴት ከእኛ ጋራ መጫወት ይችላል፤ አቅም የለውም፤ ልጅ ነው በማለት የክለቡ አመራሮች አሰልጣኝ አብርሀም ላይ ጫና አሳድረውበታል። ዝግጅት የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶ እኔ ሻንጣዬን ይዤ የመጣሁ ቀን አሰልጣኝ አብርሀም የተለያዩ ችግሮች ስለተፈጠሩ አብረኸን አትሄድም፤ ከዝግጅት ስንመለስ ግን አብረህን ትቀላቀላለህ ብሎኝ ተመልሻለው። ይህ ጊዜ በጣም ያዘንኩበት፣ የተከፋሁበት ነበር። ልጅ ሆነህ በክለብ የመጫወት ፍላጎት አድሮብህ ሲመልሱ የሚሰማህን ስሜት አስበው፤ በቃ ኳስ ላልጫወት ነው ብዬ በጣም ነው የደነገጥኩት። ከዝግጅት እንደተመለሱ አሰልጣኝ አብርሀምን አናገርኩት፤ ያው እርሱ ለዋናው ቡድን አስቦኝ ነበር ያመጣኝ። የአመራሮቹ ጫና ስላለ ፍቃደኛ ከሆንክ እኔ ትልቅ ደረጃ አደርስሀለው። ከታች ካለው ቢ ቡድን ጋር ተቀላቀል እና የተወሰነ ጊዜ ስራ ከታች የምናሳድጋቸው ተጫዋቾች አሉ። የዛን ጊዜ አቅምህን አይተው እራሳቸው ይወስናሉ አለኝ። እኔም በጣም ደስ አለኝ። ለዋናው ቡድን ብፈርምም ለቢ ቡድን መጫወት ችያለው። ከታችኛው ቡድን ጋር ለሳምንት ከሰራው በኃላ የወዳጅነት ጨዋታ ከታዳጊ ብሔራዊ ቡድን እና ከእርሻ ሰብል ቢ ቡድን ስንጫወት ጎሎችን አስቆጠርኩ። በዚህም ኮሚቴዎቹ በጣም ተገርመው ወደ ዋናው ቡድን እንድመለስ አደረጉኝ። ኒያላ በዛኑ አመት ቻምፒዮን ሆኖ እኔም በውድድሩ በአጠቃላይ ሰባት ጎሎችን አስቆጥሬ ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደግ ቻልን። ፕሪምየር ሊግ ከገባን በኋላ ውድድሩ በጣም ነው የከበደን፣ እንደ ብሔራዊ ሊጉ አልሆነልንም፤ ጫናም ነበረው። እኔም የውድድሩ ግማሽ ላይ ጉዳት አጋጥሞኝ ውድድሩን ሳልጨርስ ቀረሁ። ቡድኑ እንደምንም እየተንገዳገደ ሳይወርድ ቀረ። የዓመቱ መጨረሻ ላይም ከቡድኑ ከተቀነሱ ሦስት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆንኩ።

አንተ ብቻ ሳትሆን አሰልጣኝ አብርሀም ከኒያላ ተሰናብቷል። በጣም የሚገርመው በቀጣይ ዓመት ከአሰልጣኝ አብርሀም ጋር በሌላ ክለብ ዳግም ተገናኝታችኋል። ምን ይሆን ከአሰልጣኝ አብርሀም ጋር አብሮ የመስራት ግጥጥሞሻቹ ?

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የእኔ አጨዋወት እና ኳሊቲ በጣም ይመቸዋል። ብዙ የእግርኳስ እውቀት የሰጠኝ አሰልጣኝ ነው። ከጉዳቴ ነፃ መሆኔን ከጠየቀኝ በኃላ ለወንጂ ስኳር እንድጫወት አድርጎኛል። ሆኖም ወንጂ ስኳር ብሔራዊ ሊግ እያለ የተጫወትኩት ከአምስት ጨዋታ አይበልጥም ነበር። ምክንያቱም የታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ ረጅም ጊዜ አብረን ተሰባስበን የቆየንበት በጣም ጥሩ ቆይታ ያደረገኩበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። በዚህም ምክንያት ለወንጂ ብዙ መጫወት አልቻልኩም። በወቅቱ ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን የጠሩኝ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ጉልላት ፍርዴ ነበሩ። በጣም የሚገርም ስብስብ ነበር። ሁሌም ሳስበው በጣም የሚገርመኝ ቡድን ነበር። የመጀመርያው ይመስለኛል ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ፤ ከዛ በኋላ ያለፈ ቡድን የለም። በወቅቱም አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ይናገር ነበር። ይህ ከ17 ዓመት በታች ቡድን የመጨረሻው ትውልድ ነው ይል ነበር።

እስቲ ይህ የወቅቱን ቡድን ትንሽ አስታውሰኝ ?

ይህ ታዳጊ ቡድን ረጅም ጊዜ አብሮ የቆየ የሚገርሙ ምርጥ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች ነበሩ እንደነ ታፈሰ ተስፋዬ፣ ሀብቶም ብርሀኔ፣ ደምስ ኑር፣ ታምራት አበበ፣ ሚካኤል ደስታ፣ ኤልያስ ሌሎችም ልጆች ነበሩበት። ስዋዚላንድ ላይ የተዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ የቻለ ቡድን ነው። እዛም ሄደን ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። በዚህ ቡድን ውስጥ በማጣርያውም በአፍሪካ ዋንጫም ጎሎችን ማስቆጠር ችያለው።

መቼም ይህ የታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ቆይታ ብዙ ነገሮችን በእግርኳስ ህይወትህ ላይ ለውጥ አምጥቷል ብዬ አስባለው። በመቀጠል ወደ ወንጂ ስኳር ተመልሰህ የነበረህንም ቆይታ አጫውተኝ

ምንም ጥያቄ የለውም። እኔ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበርነውን ልጆች የእግርኳስ ህይወታችንን ቀይሮታል። ከብሔራዊ ቡድን መልስ ወደ ክለቤ ወንጂ ስኳር ተመልሼ መጫወት ችያለው። በጣም የሚገርመው ወንጂ ስኳር ብሔራዊ ሊግ ወደ መጨረሻው ጨዋታ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ጫፍ ላይ ደርሶ በነበረው ጨዋታ ላይ መጫወት ችያለው። ቡድኑ የውድድሩ ቻምፒዮን መሆን ቻለ። የወቅቱ የቡድኑ አጥቂ የነበረው ኤልመዲን መሐመድ የውድድሩ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆነ። በቀጣይ ዓመት ወንጂ ፕሪምየር ሊግ ከገባ በኋላ መጫወት ችያለው። እራሴን ያሳየሁበት ጥሩ የውድድር ዓመት አሳልፌያለሁ። የውድድሩም ኮከብ ጎል አስቆጣሪነትን ከፍቃዱ በላይ፣ መሳይ ተፈሪ፣ ታፈሰ ተስፋዬ እና እኔ አራታችን ሆነን በ12 ጎል ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆነን ማጠናቀቅ ችለናል።

ወንጂ እውቅና ያገኘሁበት ቡድን ነው። በአብርሀም መብራቱ እየተመራ ጥሩ ቡድንም ነበረው… አሁን ቡድኑ ታችኛው ዲቪዝዮን ሲዳክር ስታየው ምን ይሰማሃል…?

አዎ ወንጂ ስኳር የልጅነት ክለቤ ነው። ጥሩ ትዝታ አለኝ። ከአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ፣ ኤልመዲን መሐመድ ጋር ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍነው። ህዝቡም በጣም እግርኳስ የሚወድ ነው። ይህ ቡድን እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ በጣም ነው የሚያሳዝነው። የእኛ ሀገር እግርኳስ አንዳንዴ የሚያሳዝኑ ክስተቶችን ያሳይሀል። በቀርቡ የነበርኩበት ንግድ ባንክ እንኳን ስንት ታሪክ ሰርቶ ብዙ ልጆችን ለብሔራዊ ቡድን አፍርቶ የነበረ ክለብ በማይሆን መልኩ ነው ፈርሶ ያለው። አንዳንዴ ሳስበው በጣም ነው የሚያሳዝነኝ

ከወንጂ ቀጥሎ በእግርኳሱ ነጥረህ ወደ ወጣህበት እና ብዙ ስኬት ወዳጣጣምክበት ቅዱስ ጊዮርጊስ አምርተሀል። እስቲ ሰፋ አድርገን ቅዱስ ጊዮርጊስ የነበረህን ቆይታ እናውራ ?

የእግርኳስ ህይወቴ ጥሩ ጊዚያት ያሳለፍኩበት ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቆየሁበት አምስት ዓመታት ውስጥ ነው። ብዙ ዋንጫዎችን፣ ብዙ ስኬቶችን አግኝቻለው ። በተለያዩ አሰልጣኞች ብሰለጥንም አብዛኛውን ጊዜ ያሰለጠነኝ ሚቾ ነው። ሚቾ በጣም ትልቅ እና እግርኳስ ምን እንደሆነ እንዲገባኝ ያደረገ አሰልጣኝ ነው። የክለቡም አመራሮች ለኢትዮጵያ እግርኳስ ትልቅ ስራ የሰሩ ግለሰቦች ያሉበት ነው። በቅዱስ ጊዮርጊስ በቆየሁበት አምስት ዓመታት በ1998 የአመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብያለው። አምስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችያለው። በሴካፋ የክለቦች ዋንጫ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ሜዳልያ አግኝቻለው።

በአምስት ዓመታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታህ ብዙ ስኬቶችን እንዳገኘህ ይታወቃል። ሆኖም አንዳንድ ነገሮችን ማሳካት አልቻልክም ይባላል። ለምሳሌ በ1998 ኮከብ ተጫዋች የተባልክበትን ምርጡን አቋምህን በቀጣይ ዓመታት መድገም አልቻልክም። ለምን?

አዎ መድገም ያልቻልኩበት ምክንያት በመሐል የውጭ ሀገር የእግርኳስ ዕድል አግኝቼ ወደ የመን ሄጄ ነበር። እዛም ብዙም የተሳካ ነገር ሳይኖር ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ተመልሼ መጥቻለው። ከየመን ስመለስ እዚህ ቡድኖች ዝግጅት ጨርሰው ወደ ውድድር ገብተው ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተስማምቼ መቀጠል ከጀመርኩ በኃላ ወደ ነበርኩበት አቋም ለመመለስ ትንሽ ጊዜ ወስዶብኛል። እንደሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ ነው። በአጋጣሚዎች በጉዳት፣ በተለያዩ ምክንያቶች ቦታህን ካጣህ ተመልሰህ ለማግኘት ረጅም ጊዜ ነው የሚወስድብህ። እኔም በመሐል ጉዳት እየተደራረበ አስቸግሮኝ ነበር። በዚህ ምክንያት ውድድሩን ያሳለፉኩት ደካማ ሆኜ ነበር። በቀጣይም ያሉትን ዓመታትም ወጥ የሆነ አቋም አሳይቼ መቀጠል አልቻልኩም። ብልጭ ድርግም የማለት ነገር ነበር። በመሐልም ከክለቡ ጋር በአንዳድን ነገሮች መስማማት ስላልተቻለ ልንለያይ ችለናል።

ሌላው ማንሳት የፈለግኩት በዚሁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታህ ከኢትዮጵያ ውጭ ወጥቶ የመጫወት ዕድሎች አግኝተህ አልተጠቀምክም። ከአንተ ጋር ይጫወት የነበረው ፍቅሩ ሲጠቀም አንተ ግን ለምን?

በወሬ ደረጃ እኔም እሰማለው እንጂ በቀጥታ እኔ ጋር መጥቶ የውጪ እድል መጥቶልሀል፤ ትሞክራለህ ወይ? ብሎ ያናገረኝ አካልም ሆነ ሰው የለም። በጭምጭምታ ደረጃ ሚቾ ወደ ውጭ ወጥተህ እንድትጫወት እያመቻቸልህ ነው ሲሉ እሰማለሁ። ሆኖም በቀጥታ የመጣ ነገር የለም። አጋጣሚ ኖሮ የምሞክረው ዕድል ቢኖር ደሰተኛ ሆኜ ራሴን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ እፈልግ ስለነበር እጠቀምበት ነበር።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተሳካ አምስት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ሰበታ ከተማ አምርተህ መጫወት ችለሀል። ቀጥሎም ኢትዮጵያ ቡና የማመራህበትን አጋጣሚ አስታውሰኝ

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከተለያየሁ በኃላ ሰበታ ከተማ ነው የገባሁት። ሰበታ በነበረኝ ቆይታ ጊዮርጊስ ቤት የነበረኝን አቅም፣ ልምድ ይዤው ስለነበረ ሰበታ ላለመውረድ እየተጫወተ እኔ የኮከብ ጎል አግቢነቱን ከነ ጌታነህ ከበደ ጋር እፎካከር ነበር። አንዳንዴ ተጫዋች ሆነህ ከክለብህ ጋር ችግሮች ሲኖሩ ሜዳ ላይ ተፅእኖ ይኖረዋል። ከእነዚህ ነገሮች ነፃ ስትሆን ደግሞ በተሻለ መልኩ ጥሩ መንቀሳቀስ ትችላለህ። በሰበታ ቆይታዬ የተሻለውን ቢንያምን ማየት ችያለው። ኢትዮጵያ ቡናም በቆየሁበት ሁለት ዓመታት ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለው። ቡድኑ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ባነሳበት ማግስት በመሆኑ ክለቡን የተቀላቀልኩት የተወሰነ አለመረጋጋት ነበር። 2003 ሻምፒዮን ከሆነው ቡድን ስምንት ተጫዋቾች ተቀንሰው ሮቤል ግርማ፣ አስናቀ ሞገስ እና እኔ ነበርን መጨመር የቻልነው። በወቅቱ ብዙ ነገሩ የተጎዳ ቲም ነበር። ይልቁንም እንዳይወርድ ሁሉ ተሰግቶ የነበረበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። ሆኖም በሚገር ሁኔታ ሁለተኛ ሆኖ የጨረሰበት ዕድል ተፈጥሯል። ሁለተኛ ዓመት ቆይታዬም ጥሩ ነበር። የመጀመርያው ዙር ላይ ከፍተኛ ጎል አግቢነት እፎካከር ሁሉ ነበር። የክለቡ አመራሮች ተጨማሪ ተጫዋቾችን በማምጣት ቡድኑን ለማጠናከር የገቡትን ቃል አለመጠበቃቸው ሳይበቃ በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ግልጋሎት እየሰጡ ያሉትን የማባረር እንቅስቃሴ ሲጀምሩ የቡድኑ ጥንካሬ በአንዴ እየወረደ መምጣት ጀምሯል። የክለብህ ሁኔታ እየተጎዳ ወደ አለመረጋጋት ውስጥ ሲገባ የአንተም እንቅስቃሴ እየወረደ አይምሮህ እየተጎዳ ይመጣል። ወደ አምስት ስድስት ጨዋታዎች ላይ ሳላገባ የነበረኝን የኮከብ ጎል አስቆጣሪነት ክብርን ሳላሳካ ቆይቻለሁ።

ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለኢትዮጵያ ቡና ተጫውተሃል… ከሁለቱ የበለጠ ጥሩ ትዝታ ያለህ በየትኛው ክለብ ነው?

ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ የሚባሉ ሁለቱ ክለቦች ናቸው። እኔም በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ በሁለቱም ክለብ ተጫውቼ አሳልፌያለው በዚህም በጣም ዕድለኛ ከሆንኩባቸው እና ደሰ ከሚሉኝ ነገሮች አንዱ ነው። ሁሌም በየሄድክበት ክለብ የየራሱ የሆነ ትዝታ አለው። ከጊዮርጊስ ጋር አምስት ዓመት ስቆይ ዋንጫዎች፣ ኢንተርናሽናል ውድድሮች ብዙ ስኬቶች ስላገኘሁ ብዙ ትዝታ አለኝ። እንዲሁም ከቡና ጋር ቢሆን የነበረኝ ቆይታ የደጋፊው ድባብ መቼም የምትረሳው አይደለም። በየሄድክበት ቦታ፣ ወደ ሜዳ ለጨዋታ ስትገባ የሚዘምሩት ዝማሬዎች ልትረሳው የማትችለው ትዝታ አለው። በአጠቃላይ ሁለቱም ጋር ቆንጆ ትዝታ አለኝ።

ከኢትዮጵያ ቡና ከወጣህ በኃላ ያሉት ቀሪ የእግርኳስ ህይወትህ ብዙም የተረጋጋ አልነበረም። ወደ አራት ቡድኖች ቀያይረህ ነው እግርኳስን ወደ ማቆም ደረጃ የደረስከው እንዴት ነው የመጨረሻዎቹ ክለቦች ቆይታህ?

አዎ ብዙ ምክንያቶች ቢኖረውም ከኢትዮጵያ ቡና ቆይታዬ በኋላ ተመልሼ ለንግድ ባንክ፣ ጅማ አባ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ መጫወት ችያለው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያለው ይህ ቡድን እንዳይወርድ የምንችለውን ሁሉ ብናደርግም ሊሳካ አልቻለም። በእግርኳስ ህይወቴ ያዘንኩበት ጊዜ ሆኖ አልፏል። ከዚህ በኃላ ከጉዳትም ከሌሎችም ምክንያቶች ጋር ተያይዞ ብዙም አስደሳች ግዜ አላሳለፍኩም በመጨረሻም ኢትዮ ኤሌክትሪክ እያለው እግርኳስን ለማቆም ተገድጃለው።

በተደጋጋሚ ክለቦች መቀያየርህ በእግርኳስ እድገትህ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ምንያህል ነው?

ብዙ ክለብ ተዟዙሮ መጫወቱ ችግር አለው ብዬ አላስብም። አንድ ክለብ ላይ ተረጋግተህ መጫወት ያልቻልከው ለምድነው ካልከኝ የክለቦቹ ችግር ነው የምልህ። እኔ በጣም የሚገርመኝ እና የሚያሳዝነኝ ነገር ይሄ ነው። ቡድን ከሰሩ በኃላ ያ ቡድን ጥሩ ሆኖ ተፎካክሮ እየሄደ ባለበት ሰዓት ሊጉ አልቆ በቀጣይ በጎደሉት ነገሮች ላይ ማስተካከል ሲገባ የሚያፈርሱት ነገር ነው ክለብ እንድቀያይር ሲያደርገኝ የቆየው።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ መታረም መስተካከል አለብ የምትለው ነገር አለ በዚሁ የምታነሳው ሀሳብ ካለህ ?

የእኛ ሀገር እግርኳስ እየተጓዘበት ያለው መንገድ ጥሩ ነው የሚባል አይደለም። በጣም የተበላሸ አቅጣጫውን የሳተ ነው። እግርኳሱ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ ባለበት ወቅት አሰልጣኞች፣ ኮሚቴዎች፣ ጋዜጠኞች ጭምር ብዙ የተበላሸ የተጨማለቀ ነገር ነው ያለው። ለእኛ ሀገር እግርኳስ የባሰ ገደል የሚከት ነው። አቅም ያለውን ተጫዋች ከመጠቀም ይልቅ እነርሱን ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን ነገር ነው እየተከተሉ ያሉት። ይህ ነገር ደስ አይልም። ፌዴሬሽኑም፣ የተጫዋቾች ማኀበርም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተረባርበው እና ራሳቸውን አጠናክረው እነዚህ አላስፈላጊ ነገሮች የሚቆሙበትን መንገድ ቢፈጥሩ መልካም ነው።

አሁን በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለህ ?

በእግርኳስ ተጫዋችነት በቆየሁባቸው 15 ዓመታት እጅግ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ የሚባሉት ሁለቱ ትልልቅ ቡድኖች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና መጫወቴ በጣም ዕድለኛ እና ሁሌም ሳስበው የሚያስደስተኝ ነው። አሁንም ቢሆን የመጫወት አቅሙ፣ ልምዱ ነበረኝ። ሆኖም የኢትዮጵያ እግርኳስ እንዲህ ነው ብለህ የማትገልፀው በርካታ ውስብስብ ችግሮች እና እግርኳሱን ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚቀይሩ በርካታ ነገሮች መኖራቸው እግርኳስን ለማቆም (ጫማ ለመስቀል) አንዱ ምክንያት ሆኖኛል። ወደፊት በስፖርቱ የሚኖረኝን ተሳትፎን አሁን ላይ ሆኜ መናገር ባልችልም ወደፊት የምናየው ይሆናል። አሁን ከኢትዮጵያ ውጭ በሀገረ በአሜሪካ ከባለቤቴ እና ከወንድ ልጄ አማን ቢንያም ጋር እየኖርኩ እገኛለው።

ወደ መጨረሻዎቼ ጥያቄዎች ልምጣ.. እግርኳስን በክለብ መጫወት ስትጀምር የመጀመርያ ጎልህ እና እግርኳስ ስታቆም የመጨረሻ ጎልህን አስታውሰኝ? ከዚህ በተጨማሪ ጠንካራ የግራ እግር ምቶችህና የቆሙ ኳሶች አጠቃቀምህ ከምን ያገኘህው ነው ?

የመጀመርያ ጎሌ ከኒያላ ጋር ብሔራዊ ሊግ እያለን ወላይታ ሶዶ እነርሱ ሜዳ ላይ ሄደን ይመስለኛል ጎል ያስቆጠርኩት። የመጨረሻ ጎሌ ከጅማ እንደተመለስኩ ንግድ ባንክ ላለመውረድ በሚጫወትበት ወቅት ሁለት ጎሎችን ኢትዮጵያ ቡና ላይ በማስቆጠር ነው የጎል አካውንቴን የዘጋሁት። ጠንክሮ ከመስራት የመጣ ይመስለኛል የጠንካራ ምቶቼ መገኛ።

በተጫዋችነት ዘመንህ በጣም የምታደንቃቸው ተጫዋቾችን ንገረኝ

በተጫዋችነት ዘመኔ ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር ተጫውቼ አልፌያለው። ሆኖም እኔ በልዩ ሁኔታ የማያቸው ሙሉዓለም ረጋሳ፣ አሸናፊ ግርማ፣ ዳዊት መብራቱ (ገዳዳው) ናቸው። ሌሎች ተጫዋቾችም ቢኖሩ እነርሱ የተለዩ ተጫዋቾች ናቸው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ