የኢትዮጵያ ቡና የራሱን የልምምድ ሜዳ ዝግጁ አደረገ

በተለያዩ ቦታዎች ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ልምምድ ይሰራ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና የራሱ የልምምድ ሜዳ አዘጋጅቶ ማጠናቀቁ ታውቋል።

ለቡ (ጀሞ) በሚገኘው ክለቡ ለስታዲየም ግንባታ እንዲውል በተፈቀደለት ይዞታ ላይ ከወራት በፊት አቅዶ ወደ ሥራ ገብቶ የነበረው። ይልቁንም ያለፉትን ሦስት ወራት በተደረገው ከፍተኛ ጥረት በአሁኑ ሰዓት ቦታውን በጊዛዊነት ክለቡ ልምምድ እንዲሰራበት መጠናቀቁን ለማወቅ ችለናል። ምን አልባትም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ውድድሮች መሰረዛቸውን ተከትሎ እንጂ ክለቡ በቀጣይ ልምምድ ለመስራት ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማቆም ራሱ ባዘጋጀው ቦታ ልምምድ እንደሚሰራ ታውቋል። ያለፉትን ዓመታት የራሱ የልምምድ ሜዳ ባለመኖሩ ምክንያት ለልምምድ ሜዳ ኪራይ በቀን ከሁለት ሺህ ብር በላይ ያወጣ የነበረ ሲሆን ይህ የልምምድ ቦታው መዘጋጀቱ ክለቡን ያወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ እንደሚቀንስ ታውቋል። ለጊዜው ለልምምድ ሜዳነት ይሰራ እንጂ በቀጣይ ኢትዮጵያ ቡና በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በዚህ ሜዳ ለማድረግ ከወዲሁ ከፍተኛ ሥራ ይሰራል ተብሏል። ይህም ብቻ ሳይሆን የክለቡን ገቢ ለማሳደግ ሌሎች ክለቦች ልምምድ እንዲሰሩ እና የሚጫወቱበት ሜዳ እንዲሆን ጭምር ለማከራየት መታቀዱን ሰምተናል።

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ሊያስገነባው አዲስ ስታዲየም ከከተማ አስተዳደሩ የተሰጠውን 7,723 ካሬ ሜትር ስፉት ያለው ቦታን ለማስጀመር አንዳንድ በአካባቢው ቀድመው የተገነቡ ህንፃዎች የፈጠሩትን ተግዳሮት ቀጣይ በምን መልኩ ማስተካከል ይገባል በማለት በትናትነው ዕለት የመስክ ምልከታ ተደርጓል። በመስክ ምልከታው ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አረጋይን ጨምሮ የንፋስ ስልክ ክ/ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የክፍለ ከተማው የመሬት ልማት ኃላፊ እና የወረዳው አመራሮች የኢትዮጵያቡና ስፖርት ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ፣ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እንዲሁም የደጋፊ ማኅበሩ አመራሮች ተገኝተዋል። በቦታው በተደረገው ምልከታ የሰታድየም ግንባታወን ለመጀመር በቦታው ላይ ያለየትን ችግሮች ለመቅረፍ ሰፊ ውይይት እንደተደረገ ሰምተናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ