የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ስለ ሊጉ መሠረዝ ይናገራል

የ2012 ውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሙሉ ለሙሉ ከመሠረዙ አስቀድሞ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን የፋሲል ከነማው አጥቂ ሙጂብ ቃሲም በ14 ጎሎች እየመራ እንደነበረ ይታወቃል። ሆኖም አወዳዳሪው አካል የኮረና ወረርሽኝ ምክንያት የ2012 የሊግ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ውጤቶቹ በመሠረዛቸው የኮከብ ጎል አስቆጣሪዎችም ውጤት ሊሰረዝ ችሏል። ይህን አስመልክቶ የተሰማውን ስሜት እንዲገልፅልን የጎል ሰንጠረዡን እየመራ ከነበረው ሙጂብ ቃሲም ጋር አጭር ቆይታ አድርገን የሚከተለውን ብሎናል።

“እንደማንኛውም ተጫዋች ትልቅ ክብሮችን ለማግኘት ጠንክረህ ትስራለህ። እኔም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ለመጨረስ ጠንክሬ እየሰራሁ ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን ዓምና የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ጫፍ ደርሰን በመጨረሻ ጨዋታ ያጣነውን ዋንጫ ከፋሲል ከነማ ጋር ዘንድሮ ለማሳካት እንደ ቡድን አቅደን እየሰራን ነበር። ያው ይህ አስከፊ በሽታ መጥቶ ያሰብነውን ነገር እንዳናሳካ እንቅፋት ሆኖብናል። ይህ ችግር እኔ ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ እኔ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ለመሆን ለሚፎካከሩትም ጭምር የተወሰነ ውሳኔ ነው። ከተከላካይ ስፍራ ተጫዋችነት ወደ አጥቂነት ከተመለስኩ በኃላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ጥሩ የጎል አስቆጣሪነት ሪከርድ አለኝ። ከፈጣሪ ጋር በቀጣይ የተሻለ ነገር ለመስራት አስባለው። ዘንድሮ ቢሳካልኝ ደስ ይለኝ ነበር። ፈጣሪ የፈቀደው ነው የሚሆነው”።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ