“በአሰልጣኝነት ዘመኔ ተስፋዬ ኡርጌቾን የሚያህል ተጫዋች አላየሁም” አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ

የቀድሞው ድንቅ የአማካይ ሥፍራ ተጫዋቹ ተስፋዬ ኡርጌቾ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ተከትሎ በቅዱስ ጊዮርጊስ ያሰለጠኑት አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ስለ ተጫዋቹ ይናገራሉ።

ተስፋዬ ኡርጌቾ ተወልዶ ያደገው በወንጂ ከተማ ሲሆን ትልቅ ተጫዋች ሆኖ በወጣበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ1984-90 ድረስ ተጫውቶ አሳልፏል። አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ቡድኑን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማሰልጠን በተረከበበት በ1986 ላይ ይህ ድንቅ አማካይ አቅምኑ አውጥቶ እንዲጫወት በማድረግ እድል ሰጥተውታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ86–88 ድረስ ለተከታታይ ሦስት ዓመት የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ሲሆንም የተስፋዬ ኡርጌቾ ሚና ከፍተኛ ነበር። የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ ተስፋዬ ኡርጌቾ በአንድ ወቅት ለሚዲያ ሲናገር “ትልቅ ተጫዋች እንድሆን አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ትልቁን ውለታ ውሎልኛል።” በማለት መናገሩም ይታወሳል። ይህን ተከትለን የቀድሞውን አንጋፋ አሰልጣኝ ጋሽ አሥራትስ ስለ ተስፋዬ ኡርጌቾ ግለ ባህሪ እና የተጫዋችነት ዘመን ምን ይላሉ ብለን ጠይቀነው ይህን ብለውናል።

” እጅግ በጣም ያልጠበኩት አስደንጋጭ ዜና ነው የነገርከኝ፤ አስቀድሞ አልሰማሁም ነበር። (ከተወሰኑ ሶኮንዶች ዝምታ ከተዋጡ በኋላ በሀዘን ስሜት…) ተስፋዬ በጣም ልዩ ተጫዋች ነው። ጥሩ ሥነ ምግባር የነበረው ታዘዥ፣ ታታሪ ነው። ለተሰማራበት ሙያ እስከ መጨረሻው ድረስ መሰዋዕትነት የሚከፍል ተጫዋች ነው። እንደ አሰልጣኝ ያወጣህውን የልምምድ ፕሮግራም በሙሉ ጨርሶ የሚወጣ፣ ያልገባውን የሚጠይቅ፣ ሁሌም ራሱን ለማሻሻል ከፍተኛ ደረጃ ለመድረስ የሚጥር ተጫዋች ነበር። ተስፋዬ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ተጫዋች ነው። ሜዳ ላይ ሁሉን ነገር ማድረግ የሚችል አማካይ፣ አጥቂ መሆን የሚችል፣ ሲፈልግም ወደ ኃላ መጥቶ የሚጫወት ጉልበት፣ ፍጥነት እና ድፍረት የነበረው ሁለገብ ተጫዋች ነው። እንደሱ ዓይነት ተጫዋች በዚህ ዘመን አለ ብዬ ለመናገር አልደፍርም። ተስፋዬን የሚተካ ተጫዋች በእርሱ ቦታ አልተፈጠረም ማለት ይቻላል። በእኔ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝነት ዘመን የእኔ ቁልፍ ተጫዋች የነበረው ተስፋዬ ነው። ቀድሞ ጎል የሚገባብን ከሆነ ተስፋዬ ሜዳ ውስጥ ካለ በርግጠኝነት ጎል አግብተን እንደምናሸንፍ እናውቅ ነበር። በአጠቃላይ በእኔ የአሰልጣኝነት ዘመን ካየኋቸው ተጫዋቾች ተስፋዬን የመሠለ ምርጥ አማካይ ተጫዋች አላየሁም ቢባል ማጋነን አይሆንም። በጣም ነው የሚያሳዝነው፤ ብዙ ሳይሰራ ሳንጠቀምበት ነው ያጣነው። ነፍስ ይማር፤ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመድ እና ለስፖርት ቤተሰቡም መፅናናትን እመኛለሁ።”

በዛሬው ዕለት የዚህን ድንቅ ተጫዋች የህይወት ታሪክ የያዙ የተለያዩ ዘገባችን በተለያዩ አምዶች ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልፃለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ