ስለ ሳምሶን ሙሉጌታ “ፍሌክስ” ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

“ሳሚ ልስልሱ አንጀት አርሱ” እያሉ ደጋፊዎች የዘመሩለትና ቅዱስ ጊዮርጊስን ለረዥም ዓመታት በተከላካይነት ያገለገለው ሳምሶን ሙልጌታ “ፍሌክስ” ማነው?

አስራ አራት ዓመታት ያለማቋረጥ ቅዱስ ጊዮርጊስን በታማኝነት አገልግሏል። ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ገነት ሆቴል አካባቢ ነው። ከ1991-92 (ግማሽ) ድረስ በታዲጊ ቡድን ቆይታ ካደገ በኃላ እስከ 2004 ድረስ በፈረሰኞቹ ቤት አይረሴ ቆይቷል አድርጓል። አልሸነፍ ባይነት እና ታታሪነት መለያዎቹ የሆኑት ሳምሶን ከ2001 ጀምሮ ክለቡን እስከለቀቀበት ጊዜ ድረስ ቡድኑን በአንበልነት መምራት ችሏል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ምልክት ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ጠንካራ ተከላካይ ለአስራ አራት ዓመታት በቆየበት የስኬት ጉዞው ዘጠኝ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ጨምሮ የአሸናፊ አሸናፊ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በህብረ ዝማሬ “ሳሚ ልስልሱ አንጀት አርሱ” እያሉ የሚዘምሩለት ይህ ሁለገብ ተከላካይ በ2004 ነበር ከአሳዳጊ ክለቡ ጋር ተለያይቶ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ መድን እንዲሁም አምና እግርኳስ እስካቆመበት ጊዜ ድረስ ለደቡብ ፖሊስ የተጫወተው። ከመስመር የሚጣሉ ኳሶችን በፍጥነት የማቋረጥ አቅሙ ድንቅ እንደሆነ የሚመሰከርለት ይህ ምርጥ ተከላካይ በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ለረዥም ዓመት በኦሊምፒክ እና በዋናው ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ሀገሩን አገልግሏል። የ1997 በኢትዮጵያ የተዘጋጀውን የሴካፋ ዋንጫን ባነሳው ስብስብ ውስጥም ነበር። በዋንጫ ከታጀበ የእግርኳስ ህይወቱ በመቀጠል በአሁኑ ወቅት ያለውን ከፍተኛ ልምድ ለታዳጊ ተጫዋቾች ለማካፈል ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ ተቀላቅሏል። በዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከቦች አምዳችን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ይህን ተናግሯል።

” ከልጅነት እስከ ዕውቀት ድረስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ በከፍተኛ ታማኝነት ያለኝን ነገር ሰጥቼ ተጫውቻለው። እጅግ በርካታ በዋንጫ የታጀቡ ስኬቶችን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አሳክቻለው። በዚህ ታላቅ ቡድን ውስጥ መጫወት፣ ረዥም ዓመት መቆየት፣ በርካታ ድሎችን ማጣጣም፣ አንበል ሆኖ መጫወት እና የታሪኩ ተካፋይ በመሆኔ በጣም እድለኝ ነኝ። በተለይ የ1995 እና አንድም ጨዋታ ሳንሸነፍ የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ያነሳንበት የ2000 ስብስብ ውስጥ በመኖሬ እጅግ በጣም ትልቅ ክብር ይሰማኛል። በእግርኳስ ህይወቴ አላሳካሁትም ብዬ የምቆጨው በሁለት ነገር ነው። አንደኛው ሀገሬን በአፍሪካ ዋንጫ እንድትሳተፍ አለማድረጌ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ የክለቦች መድረክ ረዥም ዕቀት አለመሄዱ ይቆጨኛል። በተለይ የ1998 ቡድን ረዥም ርቀት መሄድ የሚችል ስብስብ ነበር። ሆኖም በጋናው ኸርትስ ኦፍ ኦክን ክለብ በተሰራብን ከፍተኛ በደል ይህ ህልማችን ሳይሳካ መቅረቱ ይቆጨኛል።

” ፍሌክስ የሚለውን ቅፅል ስሜን ያወጡኝ ቴዎድሮስ በቀለ (ቦካንዴ) እና ዘውዴ መኮንን ናቸው። ወቅቱ 1993 ነበር። እኔ በጣም ልጅ ነኝ ከእነርሱ ጋር የመቀራረብ አብሮ የመስራት እድሉ ነበረኝ፣ በጣምም ያበረታቱኝ ነበር። አንድ ተጫዋች ቀድሞ በዚህ ስም ይጠራበት ነበር። ሆኖም ኳስ ይዞ ለመዞር ሲቸገር ይህችን ለጎመን ፍሌክስ ብንሰጣት ታዞረዋለች እያሉ፣ ያሉትም ሳደርግ ፍሌክስ የሚለውን መጠርያ ለእኔ አወጡልኝ። ቀድሞ ይህ ስም የወጣለት ተጫዋችም እንኳ ሳይቀር በዚህ ስም መጥራት ሲጀምር በዛው ስሜ ሆኖ ቀርቷል። በአሁን ሰዓት ከዋና ስሜ በላይ ሰው ሁሉ የሚያውቀኝ ፍሌክስ በሚለው መጠርያ ሆኗል።

” አሁን እግርኳስ አቁሚያለው ወደ አሰልጣኝነቱ ገብቻለው። በተጫዋችነት ያገኘሁትን ትልቅ ስኬት በአሰልጣኝነቱም የማሳካት ትልቅ ዓላማ እና እቅድ አለኝ። እድለኛ ሆኜ በተጫዋችነት ዘመኔ በታላላቅ አሰልጣኞች የመሰልጠን አጋጣሚ አግኝቻለው። መንግስቱ ወርቁ፣ አስራት ኃይሌ፣ ሥዩም አባተ፣ ሚቾ እና ሌሎችም… ከእነዚህ አሰልጣኞች የምታገኘው ልምድ ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ልምዴን ለታዳጊዎች ለማካፈል በእራሴ ትልቅ እምነት አለኝ። ዘንድሮ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ለማሰልጠን መንገድ ላይ ነው ያለሁት። ቅዱስ ጊዮርጊስም ለእኔ ይህን ሲሰጠኝ ትክክለኛ ተተኪ ታዳጊዎችን ማፍራት የምፈልገው። ቢያንስ በዓመት አንድ ሁለት ልጅ ለዋናው ቡድን የሚያድግበትን ነገር ነው እያቀድኩ ያለሁት። በዚህ ሂደት ውስጥ የኮረና ወረርሽኝ በመምጣቱ ሳይሳካ ቀርቷል። በቀጣይ ዓመት ውድድር ወደ ማሰልጠኑ እመለሳለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ