ማናዬ ፋንቱ የት ይገኛል?

በአንድ ወቅት በሊጉ ከሚገኙ ጥሩ አጥቂዎች አንዱ የነበረው ማናዬ ፋንቱ የት ይገኛል ?

በትልቅ ደረጃ በደቡብ ፖሊስ መጫወት ጀምሮ በኋላም ለመከላከያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ የተጫወተው ይህ አጥቂ በ2010 መጨረሻ ከወልዋሎ ጋር ከተለያየ በኋላ ላለፈው አንድ ዓመት ከስድስት ወር ከእግር ኳሱ ርቆ ይገኛል።

በበርካታ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማልያ ለብሶ የተጫወተው እና በደቡብ አፍሪካው የቻን ውድድር ተሳታፊ ከነበረው ስብስብ አባል የነበረው ማናዬ አሁን ስላለበት ሁኔታ እና ከእግር ኳሱ የጠፋበት ምክንያት እንዲህ ያስረዳል።

” ከእግር ኳሱ የራቅኩበት ምክንያት የነገሮች አለመመቻቸት ነው። ከእግር ኳሱ በራቅኩባቸው ጊዜያት እንደማንኛውም ተጫዋች ወደ እግር ኳሱ ለመመለስ በመንቀሳቀስ ላይ ነበርኩ። ነገር ግን በአንዳንድ ምክንያት አልተሳካልኝም። ከወራት በፊት ግን ወደ ከፍተኛ ሊጉ ሻሸመኔ ከተማ ፈርሜ ለወራት ከቡድኑ ጋር በዝግጅት ቆይቻለው። በኮሮና ምክንያት እስከተቋረጠበት ግዜ ከሻሸመኔ ጋር ነበርኩ። በቀጣይ ግዜያትም በትልቅ ደረጃ ለመጫወት የሚያስችል አቅም አለኝ ፤ ጠንክሬ እየሰራሁ ነው ጠንክረህ ከሰራህ የሚከብድ ነገር የለም።” ብሏል።

እግር ኳሱ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከተቋረጠ በኃላ በግሉ ልምምዶች በመስራት እንደሚገኝ የገለፀው አጥቂው አብዛኛው ጊዜውን ከልጁ ጋር ማሳለፍ እንደሚያስደተው ይናገራል። “በዚ ሰዓት ጊዜዬን በቤት ውስጥ እያሳለፍኩ እገኛለው። ጥንቃቄ እያደረግኩ ነው። በግልም ስፖርት እየሰራሁ ነው። አብዛኛው ጊዜዬን ከልጄ ጋር ነው የማሳልፈው፤ በዛም ደስተኛ ነኝ።” ብሏል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ