የቶሎሳ ሜዳ ህልውና አበቃለት ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለምልክት ከቀሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ክፍት ሜዳዎች መካከል አንዱ የነበረው የቶሎሳ ሜዳ ከአንድ ሳምንት በፊት ባልታወቁ ሰዎች ታርሷል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ከክለቦች ጀርባ የስፖርቱ መሰረት የነበሩ የአዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ቤት እና የቀበሌ ውድድሮች አሁን ላይ መመናመናቸው ይታወቃል። ከዛም አልፎ በየአካባቢው የሚገኙ ሜዳዎችም በልማት ምክንያት ለተለያዩ አገልግሎቶች እየዋሉ አሁን ላይ ከተማዋ ለእግር ኳስ ያላት አበርክቶት እጅግ ተቀዛቅዟል። ይህ ጉዳይ በተለያየ ጊዜያት ሲነሳ ቢታይም የቀሩትን ማዳዎች ለማቆየት የሚደረገውን ጥረት በተደራጀ መልኩ የሚከታተለው ባለመኖሩ ቀስ በቀስ የከተማዋ ሜዳዎች እየተሰዉ ይገኛሉ። ባሳለፍነው ሳምንትም ቀጣዩ የዚህ ጉዳይ ሰለባ ‘ቶሎሳ ሜዳ’ ሆኗል።

በተለምዶው ኃይሌ ጋርመንት ተብሎ በሚጠራው የሠፈራ ብረት ጫፍ አካባቢ ይገኝ የነበረው የቶሎሳ ሜዳ ከ1998 ጅምሮ በአካባቢው ለሚገኙ ታዳጊዎች እና ወጣቶች እስካሁን የዘለቀ ብቸኛው የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ሆኖ ቆይቷል። በዚህም የአካባቢው 11 ፕሮጀክቶች ውስጥ የታቀፉ 420 ታዳጊዎች በሳምንት ሦስት ቀናት በሰዓት ተከፋፍለው ልምምድ ይሰሩበት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም አምስት የጤና ቡድኖች ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን ከ10-17 የዕድሜ እርከን ውስጥ የሚገኙ 32 ቡድኖች የሚካፈሉበት ውድድርም በየዓመቱ ይዘጋጅበታል።

በዚህ መጠን ከሳምንት እስከሳምንት ያለእረፍት ያገለግል የነበረው የዚህ ሜዳ ህልውና ከአንድ ዓመት በፊት ነበር መናጋት የጀመረው። በወቅቱ ችካል ተቸክሎበት ቦታው ለልማት ሊውል ሲል የሜዳው ተጠቃሚ የሆኑ ፕሮጀክቶች እና የአካባቢው ማህበረሰብ ከወረዳው እና ከክፍለ ከተማው የወጣቶች እና ስፖርት ፅ/ቤቶች ጋር በመሆን ባደረጉት ርብርብ የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት በቦታው ተገኝቶ የሜዳውን ጥቅም በመመልከት እና ውሳኔውን በማስተካከል ቦታው በስፖርት ማዘውተሪያነቱ እንዲቀጥል አድርጓል።

ሆኖም በያዝነው ዓመት ግንቦት ወር አካባቢ የአካባቢው ገበሬዎች ቦታውን ለእርሻ ለማዋል እንቅስቃሴ መጀመራቸው በመሰማቱ በድጋሜ ስጋት የገባቸው የአካባቢው የሜዳ ተጠቃሚዎች 1400 የሚሆን ፊርማ በማሰባሰብ ወደ ወረዳቸው ወጣቶች እና ስፖርት ፅ/ቤት አቤት ብለዋል። ስለጉዳዩ ማብራሪያ የሰጡን የሰፈራ ስታር ፕሮጀክት ባለቤት አቶ ሙራድ አህመድ ጉዳዩ የሚመለከተው የክፍለ ከተማው መሬት ማኔጅመንትም ቦታው በመሬት ባንክ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን እና መንግስት እስኪፈልገው እና ተተኪ ቦታ እስኪሰጥ ድረስ በስፖርት ማዘውተሪያነቱ እንደሚቀጥል የቃል ማረጋጋጫ እንደተሰጣቸው ገልፀውልናል። የህን በቂ ሆኖ ስላላገኙትም ባሳለፍነው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ለአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ደብዳቤ በማስገባት ምላሽ እየጠበቁ ባለበት ሰዓት ቦታው የኛ ነው የሚሉ የተደራጁ ሰዎች መጥተው በትራክተር አርሰውታል።

የወጣቶቹ ብቸኛ የስፖርት ማዘውተሪያ የነበረው ሜዳ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ተተኪ ቦታ ታስቦላቸው ወይስ እንዲሁ እንደሆን የታረሰው በቀጣይ ከክፍለ ከተማው ምላሽ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ