አስተያየት | የቡድን ሥራ-ጠል ነን?

ትብብር የማይታይበት የሥልጠናችን ከባቢ

በሃገራችን እግርኳስ ከታዳጊዎች ሥልጠና ጀምሮ ከፍ እስካለው እርከን ድረስ በአብዛኛው አብሮ የመስራት፣ እውቀትና ሃላፊነትን የመጋራት፣ እውቅናን የመቸርና የመሞጋገስ ልማድ የለንም፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ “አንተ ከእኔ ትሻላለህ፤ አንቺ የተሻለ ተሞክሮ አለሽ፡፡” የመባባል ባህሉማ ጭራሽም የእኛ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው እግርኳስ በርካታ ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ የስፖርት ዘርፍ ነው፡፡ በአግባቡ መሸፈን ያለባቸው የቴክኒክ፣ ታክቲክ፣ አካል ብቃት፣ ሥነ-ልቦና፣ ሥነ-ምግብ፣ ህዝብ ግንኙነት፣ ህክምና እና ሌሎችም ስራዎች አሉ፡፡ ይህን በይዘቱ ሰፋ ያለ የሥራ መሥክ በጥቂት ባለሙያዎች ብቻ ለመሸፈን መሞከር እጅግ አዳጋች ይሆናል፡፡ በየቀኑ የሚተገበሩ ልምምዶችና በጨዋታ ላይ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡የእግርኳስ ዘመናዊነት በፍጥነት እያደገ ይገኛል፡፡ በሜዳ ላይ የተለያዩ የአጨዋወት ዘዴዎች እንዲሁም የስልጠና ስልቶች በመፈጠራቸው በዘርፉ የበቁ በርካታ አሰልጣኞች እንዲኖሩን ያስገድዳል ፡፡ እኛ ደግሞ በቁጥርም በጥራትም ያሉን አሰልጣኞች ብዙ አይደሉም፡፡ ይህን ክፍተት ለመሸፈን የሚያስችል በቂ የአሰልጣኞች መጠን በየክለቡ ባይኖርም ያሉትም ግን በጋራ ሲሰሩ አይታይም ፡፡ በነገራችን ላይ አብሮ የመስራቱ ችግር ታች ድረስ ወርዶ በፕሮጀክቶች ደረጃም በጋራ የመስራት ባህል እንዲጠፋ አድርጓል፡፡በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የሚሰሩ የፕሮጀክት አሰልጣኞች በጋራ የመስራትም ሆነ እውቀትን የመጋራት ፍላጎት አይታይባቸውም፡፡

በእግርኳስ አጨዋወት ሥልትና የስልጠና አሰጣጥ ዘዴ የማይቋረጥ የእድገት ዑደት ይታያል፡፡ ስልጠና እያንዳንዱን ተጫዋችና አሰልጣኝ ለጨዋታ ዝግጁ ያደርጋል፡፡ ጨዋታ ደግሞ መልሶ በስልጠና ልናሻሽል የሚገቡ ችግሮችን ወይም ልናዳብር የሚያስፈልጉን አዎንታዊ ጎኖችን ያሳየናል፡፡ ድክመቶቻችን እንደ ቡድን የቴክኒክ፣ የታክቲክ፣ የአካል ብቃት እና የሥነ-ልቦና ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተናጠል የተጫዋቾች ብቃት መዋዠቅ አልያም በሜዳ ላይ በሚገኙ የተለያዩ መጫወቻ ክፍሎች (Departments) – ለምሳሌ፡- የተከላካይ፣ አማካይ ወይም አጥቂ ክፍሉ ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ ስለዚህም ሜዳ ላይ በጨዋታ ከታዩት ችግሮች በመነሳት ስልጠናዎች በግል፣ በየመጫወቻ ክፍሎች (Departments) እና በቡድን ይዘጋጃሉ፡፡ ታዲያ እነዚህን ስልጠናዎች በአግባቡ ለመስጠትና እና ለቀጣይ ጨዋታ ለመዘጋጀት በጋራ መስራት የማያጠያይቅ ሐቅ ነው፡፡

ሁሉንም ማለቴ ባይሆንም እኔ ባየኋቸው አንዳንድ የከፍተኛ ሊግ፣ የአንደኛ ሊግ፣ የአዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዚዮን፣ አንደኛ ዲቪዚዮን እንዲሁም ከሃያና ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድኖች ውስጥ አብዛኞቹ ስራዎች የሚሰሩት በአንድ አሰልጣኝ ነው፡፡ በዋና አሰልጣኙ ብቻ፡፡ በእርግጥ ቡድኖቹ ምክትል አሰልጣኝ ቢኖራቸውም ሚናቸው ግን ቁጭ ብሎ ከማየት ወይም የአካል ብቃት ልምምድ መሥሪያ መሳሪያዎች እንዲዘጋጂ ከማድረግ የዘለለ አይደለም፡፡

የአሰልጣኝ ቡድን አባላቶች ለችግሮቻችን መፍትሄዎችን በጋራ ለማበጀት አልታተርንም፡፡ ጨዋታዎችን በአጽንኦት በመመልከት ከእያንዳንዱ ጨዋታ በኋላ ቡድናችን ያሳየውን ጠንካራ እና ደካማ ጎን በዝርዝር የመለየት ሥራ አለመድንም፡፡ ምክክርና ውይይት የማድረግ ዘላቂ ሥልት አልቀየስንም፡፡ በጨዋታዎች ወቅት በግልጽ የታዩ የሜዳ ላይ ችግሮች ለተገቢው ባለቤት በማከፋፈል የቡድን፣ የግለሰብ ወይም የዲፓርትመንት ስለመሆናቸው በአሳማኝ ማስረጃ ለማስረዳት ጥረት አላሳየንም፡፡ ውጤታማ ለመሆን ያበቁን ወይም ከስኬት ያራቁን ብለን የምንጠቅሳቸው ምክንያቶች የታክቲክ፣ የአካል ብቃት፣ የሥነልቦና፣ ቡድን የማስተዳደር ወይም የሌሎች ነገሮች ጉዳይ መሆኑን በጥልቀትና በስፋት አላብራራንም፡፡ በአጠቃላይ በአንድነት የመወያየትና የመማማር መሠረት አልያዝንም፤ ባሕሉን አላዳበርንም፡፡ በእግርኳሳችን በሳምንት በአማካኝ ከሦስት ቀን ያልበለጠ የልምምድ ፕሮግርም ብቻ መዘውተሩ ታክሎበት ይብዛም ይነስም ያለንን እውቀት ለመጋራት እድሉን አላመቻቸንም፡፡ አሰልጣኞች በጋራ መስራት ካልቻልን በየሳምንቱ ደካማ ቡድን ይዞ ከመቅረብ የተሻለ አማራጭ የለንም፡፡

ዘመናዊ እግርኳስን በጥልቀት ያለመረዳት ችግር ማለትም ስፖርቱ ሰፊ ስራ እንደሚፈልግ አለመገንዘባችን ብዙ አጉድሎብናል፡፡ በተጫዋቾች የእድሜ እርከንና አስፈላጊነት ተመሥርቶ ዓመታዊ እቅዶችን የማዘጋጀት፣ ሳምንታዊና የየዕለቱን የልምምድ ፕሮግራሞች የማሰናዳት እውቀት እንዳናዳብር አድርጎናል፡፡ በቡድን ሥራ ያለማመናችን የተለያዩ የልምምድ አይነቶችን እንዳንተገብርና ለተለያዩ ባለሙያዎች በየደረጃው ሃላፊነት እንዳናጋራ ቀፍድዶ ይዞናል፡፡ 

መቼም በሃገራችን እግርኳስ በስልጠናው አካባቢ የሚታዩ ኋላ-ቀር አስተሳሰቦች ብዙ ናቸው፡፡ አንድን ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የሚይዙ ባለሙያዎች በራስ መተማመን ይጎድላቸዋል፡፡ ” ጥሩ አቅም ላለው ምክትል ወይም ረዳት አሰልጣኝ የተለያዩ ሥራዎችን እንዲሰራ ኃላፊነት ብሰጠው ኋላ ላይ መልሶ እኔኑ ያሳጣኝል፡፡” ብለው ያስባሉ፡፡ በአራዶቹ ቋንቋ “ያስጠቁረኛል!” መሆኑ ነው፡፡ ይህን አመለካከት ይዞ፣ አብረው የሚሰሩ ባልደረቦችን አስተያየት ከመስማት ይልቅ “እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው፡፡” የሚል ከመጠን ያለፈ ትምክህት ተሸክሞ እንዴት እግርኳሳዊ እድገት ይመጣል? በሌላ በኩል ምክትል አሰልጣኞችም ጋር እንዲሁ ችግሮች ይታያሉ፡፡ አንዳንዶቹ እድሉን ሲያገኙ ስራን ከመስራት ይልቅ አሉባልታን በመንዛትና ዋናውን አሰልጣኝ ሰላማዊ የሥራ ድባብ በመንሳት ላይ ያተኩሩና ወርቃማ አጋጣሚያቸውን ያመክኑታል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ሙያዊ እድገታቸውን ወደ ጎን በመተው ባሉበት ሲረግጡ ይታያሉ፡፡ እነዚህኞቹ ለሌሎች አርአያ ከመሆን ይልቅ ሳያውቁት ሙያው የተናቀና ተራ የሆነ ያህል እንዲታይ ያደርጋሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት በሃገራችን አንዳንድ አሰልጣኞች በንፅፅር ጥሩ ቡድን የሠሩ ቢሆንም ይህ ግን በአብዛኛው በአሰልጣኙ የግል ጥረት እና በተጫዋቾች ህብረት የመጣ እንጂ በአሰልጣኞች ቡድን የጋራ ስራ ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ መመስከር አይቻልም፡፡ ይህ አካሄዳችን ለተጫዋቾች ምሳሌ የማይሆን ከመሆኑ የተነሳ ለበርካታ ቡድኖች ህብረት ማጣትና አለመስማማት መንስዔ ሆኖ ቆይቷል፡፡

አሰልጣኞች በጋራ ያለመስራት ችግራችን ጉዳቱ የሚታየው ውጤት ላይ ብቻ ሳይሆን የእውቀት ሽግግርም እንዳይኖር ማድረጉን ልንረዳ ይገባል፡፡በዚህ ዘመን በአውሮፓ የምንመለከታቸው ታላላቅ አሰልጣኞች በአንድ ወቅት ተጫዋች ወይም ምክትል አሰልጣኝ ሆነው ከሰሩባቸው አሰልጣኞች ስር ብዙ ተምረው የተሻለ ደረጃ ደርሰዋል፤ ታላላቅ አሰልጣኝ ለመሆንም በቅተዋል፡፡ የሃገራችንን እግርኳስ አሰልጣኞች የእርስ በእርስ ግንኙነት ስንመለከት ግን አብረው ከሰሩባቸው አሰልጣኞች በመማር የተሻለ አዲስ ነገር ይዘው ከመምጣት ይልቅ እርስ በእርስ ሲናቆሩና ሲተማሙ ማየት ልማዳችን ሆኗል፡፡

በእግርኳስ እወቀት በተለያየ መንገድ ሊገኝ ይችላል፡፡ እየሰሩ በተግባር የሚገኝ እወቀት ግን ከሁልም ይልቃል፡፡ ስለዚህ በጋራ መስራታችን ውጤታማ ቡድን ብቻ ሳይሆን ውጤታማና የተሻሉ አሰልጣኞች እንድንፈጥር እንደሚያደርገን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ሌሎችን መስማትና ከሌሎች ለመማር በመዘጋጀት ስራዎቻችንን የጋራ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በልምድና በትምህርት ያካበትናቸውን እውቀቶች እርስ በእርሳችን እየተለዋወጥን በህብረት የመስራት ባሕልን ለማሳደግ መትጋት ይኖርብናል፡፡


ስለ ፀሐፊው

የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ