ስለ በለጠ ወዳጆ ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

በዘመናዊ እግርኳስ ግብጠባቂ እንደ አንድ ተጫዋች ኳስን አደራጅቶ መጫወት ባልታሰበበት ዘመን ኳስን በእጁ ባይቆጣጠር የሚመርጠውና በእግሩ የመጫወት አቅሙ ከፍተኛ እንደሆነ የሚመሰከርለት የዘጠናዎቹ ምርጥ ግብጠባቂ በለጠ ወዳጆ (አሞራው) ማነው?

በደርግ ዘመን በነበረው የብሔራዊ ውትድርና ግዳጅ ተመልምሎ ወደ ጦላይ መግባቱ ጠንካራ ግብጠባቂ እንዲሆን እንደረዳው የሚታመነው በለጠ ትውልድ እና እድገቱ አዳማ ከተማ ነው። በወታደር ማሰልጠኛ በነበረው ቆይታ እግርኳስ በመጫወት የጀመረው በለጠ ግብጠባቂ መሆንን ቀስ በስ ጀምሮት በኋላ የሙሉ ጊዜ ግብጠባቂ ሆኗል። በወታደር ቤት እያለ በተለያዩ የውስጥ ውድድሮች አድርጎ ምርጥ አስራ አንድ ተመርጦ የምዕራብ ዕዝን በመወከል ለጦርኃይሎች ውድድር አዲስ አበባ ሲመጣ ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ በ1979 ለምድር ጦር ተመርጦ ዳግመኛ ወደ ጦላይ ሳይመለስ እዚሁ አዲስ አበባ ለመቆየት ችሏል።

” ስርዓቱን ጠብቆ ኳስ ይጀምራል፣ የተከላካዮችን በራስ መተማመን ይጨምራል፣ ተጠንቅቆና አስቦ ይጫወታል” ሲሉ አብረውት የተጫወቱ ሁሉ ይመሰክሩለታል። ሙሉዓለም ረጋሳ ስለ በለጠ ሲመሰክር “በለጠ ግብጠባቂ ቢሆንም አማካይ በለው። ኳስን አቁሞ በደንብ መጫወት የሚችል እና በጣም ንቁ የሆነ ግብጠባቂ ነው። ያለው አቅም ከግብጠባቂ ባሻገር በእግሩ የሚጫወት በመሆኑ እርሱን ምርጥ ግብጠባቂ ነው” በማለት መናገሩ ይታወሳል።

በለጠ ከመንግስት ለውጥ በኃላ ከምድር ጦር በመውጣት ለአግሮ፣ መብራት ኃይል፣ ሙገር፣ ቡና፣ ሰሚት፣ መድን በመጨረሻም ለትራንስ ተጫውቷል። ከ1985-91 ድረስ ለስድስት ተከታታይ ዓመታት ለመብራት ኃይል ሲጫወት የ1990 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ዋንጫን ማንሳት ችሏል። በወቅቱ የኮከብ ግብጠባቂ ሽልማት የለም እንጂ ኮከብ ተብሎ መሸለም የሚገባው ነበር።

በወቅቱ በአብዛኛው ማለት ይቻላል ከክልል የሚመጡ ግብጠባቂዎች ለብሔራዊ ቡድን ምርጫ ይመረጡ ነበር። የወዳጅነት ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ተዘጋጅቶ ከክልል የሚመጡት ግብጠባቂዎች ቡድኑን እስኪቀላቀሉ ድረስ ጊዜው ስለሚያጥር በቅርብ ከአዲስ አበባ ማንን እንምረጥ ብለው ለመጀመርያ ጊዜ በአጋጣሚ በዋናው ብሔራዊ ቡድን በ1984 የተጠራው በለጠ እስከ ዘጠናዎቹ አጋማሽ ድረስ ሀገሩን አገልግሏል።

ጓንቱን ከሰቀለ በኃላ በግብጠባቂነቱ ዘመኑ ያገኘውን ከፍተኛ ልምድ ለማካፈል የግብጠባቂዎች አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ የሚገኘው በለጠ አስራ ሦስት ዓመታት በቆየው የአሰልጣኝነት ዘመኑ በመከላከያ፣ ሰበታ፣ ወልዲያ፣ ኢትዮጵያ መድን እና በአሁኑ ወቅት ወልቂጤ ከተማን እያገለገለ ይገኛል። በታንዛንያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የቅርብ ትውስታ በሆነው ለፍፃሜ ደርሶ በነበረው ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የግብጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን ሰርቷል። የዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከብ በለጠ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ሀሳቡን ሰጥቶን እኛም እንዲህ አቅርበነዋል።

” ድንቅ ግብጠባቂዎች አቋማቸው ተቀራራቢ የሆኑ ለብሔራዊ ቡድን እንኳን ግብጠባቂ ለመምረጥ በሚያስቸገርበት ዘመን ከአንድ ክለብ ሁለት ግብጠባቂ ሳይቀር የሚመረጥበት ተካበ ዘውዴ፣ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ፣ ቅጣው ሙሉ፣ አሊ ረዲ፣ ብዙወርቅ ከሌቻ፣ ይልማ ከበደ (ጃሬ) አንዱን ከአንዱ የማትለይበት እጅግ የተዋጣላቸው ግብጠባቂዎች ባሉበት ዘመን የተገኘሁ መሆኔ በራሱ ሁሌም እጅግ በጣም ያስደስተኛል። ከምድር ጦር ጀምሮ ለመጨረሻ ጊዜ እስከተጫወትኩበት ትራንስ ድረስ ስኬታማ ጊዜ ነበረኝ። ከኤልፓ ጋር በዘጠና ያነሳሁት ዋንጫ ልዩ ትውስታ ቢኖረውም ስኬት የሚለካው በዋንጫ ብቻ አይደለም። በብዙ ነገር ልትገልፀው ትችላለህ፣ ዋንጫ በማግኘት ፣ ልጆችን አብቅተህ ለብሔራዊ ቡድን በማስመረጥ በተለያየ መልኩ ስኬታማ ትሆናለህ። እኔ ባለሁበት ቦታ በተጫወትኳቸው ክለቦች ሁሉ እና አሁን እያሰለጠንኩበት ባለው ደረጃ ስኬታማ ነኝ።

“በግብጠባቂነት ዘመኔ በተለያዮ ክለቦች ስጫወት አንድ ቀን ተጠባባቂ ሆኜ አላውቅም። በግሌ እንደፈለኩ ሆኜ ነው ለረዥም ዓመት የተጫወትኩት። ለምን አንዴ ተዘናግተህ ቦታ የምትለቅ ከሆነ በወቅቱ ከነበሩት ጠንካራ ግብጠባቂዎች አንፃር ቦታህን እንደማታገኘው ስለምታውቅ ልምምድህን በተለየ ሁኔታ ነው የምትሰራው። ስለዚህ በክለብ ደረጃ የምፈልገውን ያህል ተጫውቻለው። በብሔራዊ ቡድን የተሻለ ደረጃ ደርሻለው። ሆኖም ሴካፋ ዋንጫ ሲያነሱ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ሀገሬን አለማስገባቴን ሳስብ ውስጤ ሁሌም በጣም ይቆጨኛል። እኔ ያላሳካሁትን አሁን የማሰለጥናቸው ልጆች ይሄን እንዲያሳኩ ሁሌም ይሄን ነው የምነግራቸው።

” አንዳንዴ ተፈጥሮ የሚሰጥህ ነገር አለ። ከዛ ውጭ ግብጠባቂ መቻልህ ብቻ ግብጠባቂ ሊያደርግህ አይችልም። ልትሆን ትችላለህ ግን ሙሉ ላያደርግህ ይችላል። ምን ለማለት ፈልጌ ነው፤ በእግርህ የምትጫወት እና ግብጠባቂ ሆነህ ሁለቱን ስታጣምር ነገሮች ይቀሉልሀል። ግብጠባቂ በእጁ ብቻ ሳይሆን በእግሩ መጫወት አለበት። ምክንያቱም የተቃራኒ ቡድን እንቅስቃሴ ለማቆም በአዕምሮህ መቅደም አለብህ፣ አብረውህ ቅርብ ላሉት ተከላካዮች በእግርህ በመጫወት ምቾት፣ በራስ መተማመን መፍጠር ይገባሀል። እኔ አስራ ስድስት ከሀምሳ ውስጥ በእግሬ አልጫወትም ከዛ ውጭ ነው የምጫወተው። ግብጠባቂ ሆነህ በእግርህ መጫወትህ አስተሳሰብህን፣ አዕምሮህን ከፍ ያደርገዋል። ያኛው ተጫዋች ቀድሞ የሚያስበውን አጨዋወት አንተ ቀድመህው እንድታስበው ያደርግሀል። ነፍሱን ይማረው ጋሽ ሀጎስ ምን ይላል “አጥቂ ሆኖ ይጫወት የነበረን ተጫዋች፣ እድሜው ሲገፋ ወደ ኃላ ካመጣኸው ኃይለኛ ተከላካይ ነው የሚሆነው።” ይላሉ እኔም መጀመርያ ተጫዋች ነበርኩ። ግብጠባቂ ስሆን በእግሬ መጫወት ያልተቸገርኩት ለዛ ይመስለኛል።

” በዚህ ዘመን የሚገኙ ግብጠባቂዎችን ከእኛ ዘመን ጋር አላወዳድርም። በእኛ ዘመን የነበሩ ግብጠባቂዎች እስካሁን ድረስ በሙያ ውስጥ አሉ። ለምሳሌ በለጠ ወዳጆ ብትል አለሁ፤ ቅጣው ሙሉ፣ ፀጋአብ አሁን ድረስ በሙያ ውስጥ አለን። ይልማ ከበደ (ጃሬ)፣ አሊ ረዲ፣ ፈቱሼ እስከ ቅርብ ድረስ በሙያው ነበሩ። በእኛ ዘመን አንድ ግብጠባቂ ዓመቱን ሙሉ የመጫወት አቅም አለው። ደሳለኝን እኔን ብትወስደን ከዓመት እስከ ዓመት ሙሉን ጨዋታ እንጫወታለን። ይህ ምን ያሳያል አቅምህን ያሳያል። ወደ ዚህ ዘመን ስመጣ ሁለት ነገሮች ላይ ክፍተት አለ። አንደኛ አሰልጣኞች ላይ ክፍተት አለ፣ ሁለተኛ ግብጠባቂዎቹ ላይ ነው። አሰልጣኞች ለግብ ጠባቂዎች መስጠት የሚገባውን ነገር መስጠት አለባቸው። ምን ለማለት ፈልጌ ነው ግብጠባቂውን መርጠህ ያመጣህው አንተ ነህ፤ ልጁ ሜዳ ውስጥ ገብቶ ሲሳሳት እጅህን ልትጠቁምበት አይገባም። ቀድሞ መገኘት ያለበት አሰልጣኙ ነው። እርሱ ለሰራው ስህተት እና ጥፋት ተጠያቂው አንተ ነህ። ስህተት በአንድ ጨዋታ ሲመለከት በቀጣይ ጨዋታ ከጨዋታ ውጭ አድርጎ ልጁ ራሱን እንዳያሻሽል እድል ሳይሰጠው ያጠፋዋል። ሌላው ራሳቸው ግብጠባቂዎቹ ናቸው። በአንድ ወቅት በግብጠባቂ ዙርያ አንድ ጥናት አጠናሁ። አንድም ኢትዮጵያዊ ግብጠባቂ ዓመቱን ሙሉ የሚጨርስ የለም። ሮበርት ኦዶንካራ አምስት ዓመት ኮከብ ተብሎ ሲሸለም አንዱ የኮከብ ምርጫ መስፈርቱ ብዙ መጫወት ነው። ኦዶንካራ ዓመቱን ሙሉ ይጫወታል ሌላ ክለብ ብትሄድ ግን ይህንን ማየት አትችልም ዛሬ የገባ ግብጠባቂ ነገ ይቀየራል ይህ ደግሞ የልጆቹን አቅም ያወርደዋል።

” ይህ እንዳለ ሆኖ የእኛ ግብጠባቂዎች የስራ ፍላጎታቸው የወረደ፣ ሰነፎች ናቸው። ጠንክረው አይሰሩም። በአንድ ጨዋታ ጥሩ አቋማቸው ተኮፍሰው ይጠፋሉ። ብሔራዊ ቡድን ተመልከት ሲሳይ ባንጫ መጣ ኮከብ ተባለ ጠፋ፣ ጀማል ጣሳው መጣ ይታያል ይጠፋል። አቤል ማሞ መጣ እርሱም ይጠፋል። ብሔራዊ ቡድኑን ያላየ ግብጠባቂ አለ? ስለዚህ የግብ ጠባቂዎቻችን ዕድሉን ሲያገኙ ከመጠቀም ይልቅ የመስራት አቅማቸው የወረደ ነው። ምንም የሚመጣ ነገር የለም ከዚህ ክለብ ብወጣ እዛኛው ክለብ እሄዳለው እያልክ እንደፈለክ ትሆናለህ፣ ትሸከረከራለህ፤ ያ ይመስለኛል በኛ ዘመን እንደነበሩት ጥሩ ግብጠባቂዎች በዚህ ዘመን ብዙ ማፍራት ያልተቻለው።

” በግብጠባቂ ዘመኔ እንደ ሙሉጌታ ከበደ ያስቸገረኝ አጥቂ የለም። እርሱ አዕምሮው ፈጣን ግብጠባቂዎች ከሚያስቡት በላይ ቀድሞ የሚያስብ አስቸጋሪ አጥቂ ነው። ሳጥን ውስጥ ሹት ይመታል ብለህ ስትጠብቀው ቺፕ ያደርግብኃል። በጣም ልዩ ተስጦኦ ያለው አጥቂ ነበር።

” አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ይዞት ለመጣው ፍልስፍና ትመቻለህ (ታስፈልጋለህ) ተብዬ ክለቡ አምኖበት በ1995 ቡና ገባው። ዝግጅት ጨርሰን ወደ ውድድር ስንመጣ የመጀመርያው ጨዋታ አስታውሳለው የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በደርሶ ምልስ 6–0 ተሸነፍን። በወቅቱ ብዙ ጎል መግባቱ ብዙ ተቃውሞ ተነስቶብኛል፤ ግን ጎል መግባቱ መታሰብ የለበትም ነበር። እኔ ወጥቼ በእግሬ መጫወቴ እኔ የምፈልገው እና አሰልጣኝ ካሳዬ ከሚፈልገው ፍልስፍና ጋር የሚሄድም ስለሆነ ጎሌን ለቅቄ ወጥቼ መጫወቴን፣ ጎል የሚገባ እየመሰላቸው ከጭንቀት ከፍርሀት የተነሳ ተቃውሞ ሲበዛብኝ ለአንድ ሚዲያ ቀርቤ “እኔ ጎል ለመጠበቅ ሳይሆን የመጣሁት ጎል ለማስቆጠር ነው ጎል ጠበቃ ሁለተኛ ደረጃ ስራዬ ነው።” አልኩ። በዚህ አባባል ብዙዎች ተገረሙ። ይህን ያልኩት በወቅቱ የነበረውን ጫና ተቃውሞ ለመቀነስ የሰጠቡት ሀሳብ ነው። ቀጥታ ሄጄ እኮ ጎል የማገባ ሆኜ ሳይሆን በእንቅስቃሴ ለጎሉ መቆጠር መንስኤ ትሆናለህ ለማለት ነው። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ቡና ግብጠባቂዎች ላይም በእግራቸው ሲጫወቱ የተለያዩ ጫናዎችን እመለከታለው ጊዜ ካለመስጠት፣ ትዕግስት ካለማድረግ የተነሳ የሚመጣ ነው።

“በቤተሰብ ህይወቴ በጣም እጅግ ከምለው በላይ ደስተኛ ነኝ። ባለ ትዳር የወንድ እና ሴት ልጆች አባት ነኝ። ሴቷ ቤተል በለጠ 18 ዓመቷ ነው። ወንዱ ምህረትአብ በለጠ የ17 ዓመቱ ነው። ወንዱ ልጄ ምንም አይነት የስፖርት ፍላጎት የለውም ትምህርት ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ