አስተያየት | በእግርኳሳችን ትኩረት የተነፈገው ሥልጠና

እግርኳስ በከፍተኛ ፍጥነት የሚከወን፣ የእንቅስቃሴው ጥድፈት ለብዙ ስህተት የሚዳርግ፣ በጨዋታ ወቅት ደግሞ ተገቢውን እርማት ለመውሰድ ፋታ የማይሰጥ የስፖርት ዘርፍ ነው፡፡ ጨዋታ እየተካሄደ ሳለ የምትከሰት አንዲት ትኩረት የማጣት አጋጣሚ፣ በአሉታዊ ሁኔታ ውጤት ሊያስቀይር የሚችል የተሳሳተ የኳስ ቅብብል ሒደት፣ የመከላከል ስህትት እንዲፈጸም የሚያስገድዱ የተጋጣሚ ቡድን ጫናዎች እና ሌሎችም የሜዳ ላይ ውሳኔዎች ቅጽበታዊ በመሆናቸው የወዲያው እርምት ጊዜ አይኖራቸውም፡፡ እንደ እነዚህ ያሉት የሜዳ ላይ ዱብ-ዕዳዎች የአንድ ቡድን ስኬት ላይ ብቻ ሳይሆን የተጫዋቾች ዘላቂ የግል ብቃት ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳርፋሉ፡፡

እግርኳስ ከራስ ወገን ተጫዋቾች፣ ከአሰልጣኞች፣ ከተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች፣ ከደጋፊዎች፣ ከሚዲያ አካላት፣ ከተለያዩ የውድድር አመራሮች፣ ከክለብ አስተዳደሮችና ከስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች ትልቅ ጫና ይገጥመዋል፡፡ ስለዚህም ተጫዋቾች እነዚህን ጫናዎች እንዲቋቋሙ የሚያስችሉ የስነ-ልቦና በተለይም የአእምሮ ጥንካሬ ዝግጅቶችን ማድረግ ግድ ይላቸዋል፡፡

እንደሚታወቀው እግርኳስ አራት የሥልጠና ክፍሎች አሉት፡፡ ቴክኒክ፣ ታክቲክ፣ አካል ብቃት እና ስነ-ልቦና፡፡ እነዚህ የእግርኳስ መሰረታውያን እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ በመሆናቸው አንደኛውን ያለ ሌላኛው ተግባራዊ ለማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ተጫዋቾች በአንዱ ደካማ ሆነው በሌሎቹ ጥሩ ቢሆኑ እንኳ ሜዳ ላይ ሙሉ ብቃታቸውን ለማሳየትና ውጤታማ ለመሆን ይቸገራሉ፡፡

በሃገራችን እግርኳስ ጥራትና ዘመናዊ ይዘቱ ለየቅል ቢሆንም በሦስቱ የሥልጠና ዘርፎች ማለትም በአካል ብቃት፣ ታክቲክና ቴክኒክ ዙሪያ በክለቦችም ይሁን በብሄራዊ ቡድኖች ደረጃ ልምምዱ ይሰጣል፡፡ በስነ-ልቦና-በተለይም በአእምሮ ጥንካሬ- ላይ መደበኛ ስልጠና ሲሰጥ እምብዛም አይስተዋልም፡፡ ለዚህ የሚረዳ ተገቢ የተጫዋቾች አያያዝም አይታይም፡፡ የተጫዋቾችን አእምሮ የሚያበቃ ስልጠና በአግባቡ አለመሰጠቱ ተጫዋቾቻችን- በራስ መተማመን እንዳይኖራቸው፣ ተቃራኒ ቡድንን የመጋፈጥ ፍርሃትን እንዳያስወግዱ፣ በጨዋታ ወቅት ስህተት ከሰሩ በኋላ የመረጋጋት አቅም እንዳያዳብሩ፣ የተነሳሽነት ስሜታቸው እንዳያድግ እና የመሳሰሉትን ችግሮች በመቅረፍ የተሻሉ ተጫዋቾች እንዳይሆኑ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡

ተጫዋቾቻችን እና አሰልጣኞቻችን ፍጥነትን፣ አካላዊ ጥንካሬን እንዲሁም ክህሎትን ለማሳደግ የተለያዩ የልምምድ መርኃግብሮችን ነድፈው ለውጥ ለማምጣት ይታትራሉ፡፡ በሥነ-ልቦና እና የአእምሮ ጥንካሬ ላይ የሚሰጡት ትኩረት ግን እጅግ አናሳ ነው፡፡ በእግርኳሳችን ከባቢ ከአሰልጣኞች ቡድን አባላት ውስጥ በስነ-ልቦናው ዘርፍ የበቁ ባለሞያዎችን የማካተት ልምዱ የለም፡፡ይሁን እንጂ አሰልጣኞችም ብንሆን በዚህ ርዕሰ-ጉዳይ ዙሪያ በጥልቀት አንብበን የምናሰለጥናቸውን ተጫዋቾች በአካላዊም ሆነ አዕምሯዊ ጥንካሬ የላቀ ደረጃ እንዲደርሱ የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኒኮች አልፈጠርንም፤ ነባሮቹንም አላሻሻልንም፡፡

በታዳጊዎች የሥልጠና ማዕከላት ደግሞ በቂ የምግብ አቅርቦት ያለማግኘት፣ የተሟላ የትጥቅ ቁሳቁሶች ያለመኖር፣ የጉርምስና ተፅእኖ፣ ከቤተሰብ ጋር ያለመስማማት፣ ከትምህርት ቤት ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የሥልጠና ሰዓት ያለመመቸትና ሌሎችም ተግዳሮቶች ጎልተው ይታያሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ጉድለቶች በተለይ ታዳጊ ተጫዋቾችን ለከፋ የስነ-ልቦና ውድቀቶች ይዳርጋሉ፡፡ ከአሰልጣኞቻቸው በቂ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆኑ ይሰማኛል፡፡ አልፎ አልፎ እኛ የምናሰለጥናቸው ታዳጊ ተጫዋቾች ከእግርኳሱ ውጪ ወደፊት ትልቅ ቦታ ደርሰው በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ የሚሰማሩ፣ ቤተሰብ የሚመሰርቱና የሚያስተዳድሩ ሲያልፍም ትልልቅ ተቋማትን እና ሃገርንም ሊመሩ የሚችሉ ዜጎች መሆናቸውን እንዘነጋለን፡፡ የግል አልያም ቤተሰባዊ ችግሮቻቸውን ተረድተን መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ በማግለል፣ ቅጣት በመጣልና በመገሰጽ ታዳጊዎቹን መግራቱ ይቀለናል፡፡ ይህ አካሄዳችን ሁሌም ትክክለኛው አያያዝ እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ እንዲያውም በወጣቶቹ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር በስፓርቱና በቀጣይ የህይወት መስመራቸው ተስፋ እንዳይኖራቸውና እምቅ አቅማቸውን በአግባቡ እንዳይጠሙ ያደርጋል፡፡ የሥነ-ልቦና ሥልጠና ማግኘቱና በዚያ ዙሪያ መማሩ የሚጠቅመው እነዚህን መሰል ችግሮች በአግባቡ እንዲፈቱ ማስቻሉ ይመስለኛል፡፡

የሥነ-ልቦና ቅድመ ዝግጅት አለመልመዳችን ከላይ በተጠቀሱት ማህበረሰባዊና ሌሎች እግርኳሳዊ ምክንያቶች የአእምሮ ጥንካሬ የሌላቸው፣ በራሳቸው የማይተማመኑ፣ መረጋጋት የሚሳናቸው፣ ከጨዋታ በፊት በፍርሃት የሚረበሹ ተጫዋቾችን በማፍራት ውጤታማ እንዳንሆን አድርጎናል፡፡ ስለዚህም በተለያዩ ደረጃዎች የምንገኝ አሰልጣኞች-ተጫዋቾቻችን ከፊታቸው የሚደቀኑ ተግዳሮቶችን በቀላሉ እንዲያልፉ የሚያግዙ ልምምዶችን በሜዳ ላይ ከማዘጋጀት ባሻገር ከተጫዋቾች ጋር ተገቢ የሥራ ቅርርብ ወይም ሙያዊ መስተጋብር ለመፍጠር መጣር ይኖርብናል፡፡ ሙያዊም ሆነ ማህበራዊ ችግሮቻቸውን መቅረፍ ከአቅማችን በላይ ቢሆንብን እንኳ ለማዳመጥ ጊዜ መስጠት፣ ወደ ትክክለኛው አካል መላክና ሌሎችም እገዛዎችን ማድረግ አያዳግተንም፡፡ በሥልጠናችን ዓለም ለተጫዋቾቻችን ግልጽ አቋም ልናሳያቸው እንጣር፡፡ በሜዳ ላይ የመጀመሪያ ተሰላፊ ሲሆኑም ሆነ ተጠባባቂ ሲደረጉ ለውሳኔያችን ተገቢነት በቂ ምክንያት እንስጣቸው፡፡ በጨዋታ ወቅት በብቃት መዋዠቅ ሳቢያ ተቀይረው ሲወጡ እና በጉዳት ላይ ሲገኙም ከጎናቸው ሆነን ቤተሰባዊ ትስስር እንደመሰረትን እናመላክታቸው፡፡ ይህ ግንኙነት የሙያ ሥነ-ምግባር ገደቡን ሳያልፍ መከናወን ይኖርበታል፡፡ በመልካም ሙያዊ ግንኙነት ላይ ከተመሰረተ የአሰልጣኝ-ተጫዋቾች ቅርርብ አትራፊዎቹ መላው የእግርኳሱ ከባቢ ነውና ይህን የሥነ-ልቦና የሥልጠና ሒደት ትኩረት እናድርግበት፡፡ እጅግ በጣም ባለ ክህሎት ነገርግን በቀላሉ ተሰባሪ የሆነ የአዕምሮ ደረጃ ያላቸው ተጫዋቾች ካሉን ተጠንቅቀንና በተገቢው የአዕምሮ ሥልጠና ገርተን በተፈጥሮ የታደሉትን አቅም ሁሉ አውጥተው ራሳቸውንና ቡድናቸውን እንዲጠቅሙ ለማድረግ ቀድመን እንገኝ፡፡

 


ስለ ፀሐፊው

የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: