የቀድሞው ናይጄሪያዊ አጥቂ ለሀገራችን ተጫዋቾች ምክር እና መልዕክቱን ያስተላልፋል

የቀድሞው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዳንኤል አሞካቺ ለሀገራችን ተጫዋቾች በአሰልጣኞቻቸው አማካኝነት ምክር እና መልዕክት ከቀናት በኋላ እንደሚያስተላልፍ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ አማካኝነት አሰልጣኞችን ከአሰልጣኞች እያገናኘ የሚገኘው የቪዲዮ ውይይትን ተከትሎ ከትላንት በስቲያ በስብሰባው ለመካፈል በቴክኒክ ችግር ምክንያት በውይይቱ መገኘት ያልቻለው የ47 አመቱ የቀድሞው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዳንኤል አሞካቺ ከአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው ሲሆን የሀገራችን ተጫዋቾች ኮሮና እያሳደረ ካለው ተፅዕኖ አንፃር በምን መልኩ ራሳቸውን ማዘጋጀት እና ማብቃት አለባቸው በሚሉ ጉዳዮች ላይ ለመላው የሀገራችን እግር ኳስ ተጫዋቾች በአሰልጣኞቻቸው አማካኝነት ምክር እና መልዕክትን እንደሚያስተላልፍ ተገልጿል። ይህ አንጋፋ አጥቂ ከራሱ ልምድ እና ተሞክሮ በመነሳት የሀገራችን እግር ኳስ ተጫዋቾች ራሳቸውን ማሳደግ የሚችሉበትን መንገድ እንዴት መፍጠር እንደሚችሉም ጭምር በገለፃው እንደሚካተት ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ኳስን ከሀገሩ ናይጄሪያ ክለቦች የጀመረው እና ለእንግሊዙ ኤቨርተን፣ ለቤልጂየሙ ክለብ ብሩዥ እና ለአሜሪካው ኮሎራዶ ራፒድስ መጫወት የቻለው አጥቂ እግር ኳስን ካቆመ በኋላ በናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን በረዳት አሰልጣኝነትም አገልግሏል፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫም አሰልጣኝ አብርም መብራቱ በነበሩበት የካፍ ቴክኒካል ስተዲስ ግሩፕ ውስጥ አባል እንደነበር ይታወሳል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ