ፕሪሚየር ሊግ ፡ ሀዲያ ሆሳዕናን ያሸነፈው አዳማ ከተማ የሊጉን መሪነት ተረከበ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ አንድ ጨዋታ ተካሂዶ አዳማ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-0 በማሸነፍ የሊጉን መሪነት ነገ ጨዋታውን ከሚያደርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተረክቧል፡፡

አዳማ ከተማ ግብ ለማግኘት የፈጀበት 7 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ ቤኒናዊው አጥቂ አቢኮዬ ሻኪሩ ከሱሌማን መሀመድ የተሸገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አዳማ ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኋላ የአዳማ ተጫዋቾች አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን በመክበብ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ አሰልጣኝ አሸናፊ ከጥቂት ደጋፊዎች ማስፈራርያ እየደረሰባቸው እንደሆነ በመግለፅ ክለቡን ሊለቁ ከጫፍ ደርሰው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በኳስ ቁጥጥር እና ጫና ፈጥሮ በመጫወት ከእንግዳው ቡድን ብልጫ የነበረው አዳማ ከተማ በ74ኛው ደቂቃ የ1-0 መሪነቱን ወደ አስተማማኝነት የቀየረበትን ግብ በ74ኛው ደቂቃ በአንጋፋው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ አማካኝነት አስቆጥሯል፡፡ ታፈሰ የሊጉን 8ኛ ግብ እንዲያስቆጥር ተቀይሮ የገባው ሚካኤል ጆርጅ አስተዋጽኦ የላቀ ነበር፡፡

ውጤቱ አዳማ ከተማ 23 ነጥብ ሰብስቦ ነገ ጨዋታውን ከንግድ ባንክ ጋር ከሚያደርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1 ነጥብ በመብለጥ የሊጉ መሪ እንዲሆን ሲያስችለው ሀዲያ ሆሳዕናን ደግሞ የሊጉን ግርጌ ይዞ እንዲቀጥል አስገድዶታል፡፡

የሊጉ 10ኛ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ በ9፡00 መከላከያ ከወላይታ ድቻ ፣ በ11፡30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

የሊጉ ሰንጠረዥ

standing

የከፍተኛ ግብ አግቢዎች ደረጃ

top scorers

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *