“አሁንም ድሮም ለሚባክነው ትውልድ ተጠያቂዎቹ አሰልጣኞች ናቸው” ዐቢይ ሐይማኖት (አስቴር)

የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የባንኮች ተከላካይ ዐቢይ ሐይማኖት በኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት እና ውድቀት ዙርያ ከሚኖርበት አሜሪካ ይህን አጋርቶናል።

ከ1985-1993 ድረስ ለዘጠኝ ዓመት ለባንኮች በተጫዋችነት አሳልፏል። በተጨማሪም ለቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ለሜታ አቦ እና ኒያላ የተጫወተው ይህ የቀድሞ ጠንካራ ተከላካይ ዐቢይ ሐይማኖት ከሀገሩ ከወጣ ረጅም ዓመት የሆነው ሲሆን ኑሮውን በአሜሪካ ካደረገ ቆይቷል። በዘጠናዎቹ ኮከብ አምዳችን ለማቅረብ ፈልገን ባዋራነው ወቅት ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት እና ውድቀት በቁጭት ይህን ነግሮናል።

“የኢትዮጵያ እግርኳስን በተመለከተ ውጤት አልባ ጉዞ እያደረግን ነው። ይሄም በጣም የሚያሳዝን ጉዳይ ነው። ለምን ቢባል ውጤት ማምጣት ያቃተን ውጤት የሚያመጣ አጨዋወት (እንቅስቃሴ) ስለሌለን ነው። እንቅስቃሴ ደግሞ በስልጠና ይታገዛል። ስልጠናው ደግሞ አሰልጣኙ ጋር ነው ያለው። ስለዚህ አሰልጣኞቻችን ይሄን መረዳት አለባቸው። ውጤት እንዴት እንደሚመጣ መስራት ካልቻሉ አሁንም ውጤት አልባ ነው የምንሆነው። ባለሙያው ባለሙያ ነኝ ብሎ ያልፋል ግን ውጤት የለም። ከዚህ በፊት የነበሩ አሰልጣኞች በዚህ ሁኔታ አለፉ፤ አሁንስ ያሉትስ ? በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ያለው በአሰልጣኝ እጅ ላይ ነው። የአሰልጣኝ አመለካከቶች ናቸው እግርኳስን ማሳደግም መጣልም የሚችሉት። ሆን ብለው አይጥሉም፤ ሆኖም አለማወቅ ይጥላል።

” እኛ ሀገር ትልቁ ክፍተት ችግሩን ምን እንደሆነ መረዳት አለመቻላችን ነው። ውጤት የጠፋበትን ምክንያት ምድነው ብሎ በዝርዝር አስቀምጦ መፍትሔ መፈለግ ባለመቻላችን ነው እዚህ ደረጃ የደረስነው። እንደ ባለሙያ የተጣመመውን ማቃናት ካቃተህ ትልቅ ጥያቄ ነው የሚያስነሳው። አሰልጣኞች ይህ መረዳት አለባቸው። የትውልድ ብክነት በግልፅ የሚታይ ነገር ነው። ትውልዱ መጥቀም በሚችልበት ጊዜ መጥቀም ሳይችል ቀርተው ሲያልፍ ስታይ፣ በዚህ ውስጥ ትውልዱ እየባከነ መሆኑን ያሳያል። ይህ ደግሞ የተደረገው ለረዥም ዓመታት ያለማቋረጥ ነው። ተጫዋቾች ባላቸው አቅም እና ችሎታ ውጤታማ ሳይሆኑ ሲቀር አሰልጣኞች ተጠያቂ ነው የሚሆኑት። ምክንያቱም ጥያቄ የሚነሳው ስልጠናው ላይ ስለሆነ አሰልጣኞች ተጠያቂ ይሆናሉ። ስለዚህ ለትውልዱ ብክነት ተጠያቂ ነው የሚሆኑት።

” በእግርኳስ ጨዋታ የተለያዩ መለካከቶች (ፍልስፍናዎች) ይኖራሉ። በምንም ምክንያት ያለፉት ረጅም ዓመታት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ውድቀት ወደድንም ጠላንም ተጠያቂው አሰልጣኝ ነው። እግርኳሱ ያለው በአሰልጣኙ እጅ ላይ ነው። ማንም ላይ ልናሳብብ አንችልም። አሰልጣኙ አመለካከቱን እያስተካከለ፣ ስህተቶቹን እያስተካከለ እርምት ማድረግ ካልቻለ አሁንም ለሚባክነው ትውልድ አሰልጣኝ ተጠያቂ ነው የሚሆኑት። ይሄ እኛ ሀገር በትኩረት የታየ አይመስለኝም። ወጣቶች ተጫውተው ሀገራቸውን መጥቀም ሲችሉ እንዲሁ የሚባክንቱ በአሰልጣኝ ችግር ነው። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች መታየት አለባቸው። ቁጭ ብሎ ሰከን ባለ አዕምሮ መነጋገር ያስፈልጋል። በዓለም ላይ እንደ እግርኳስ ቀላል ነገር የለም፤ የሚታይ ነገር ነው። የምታየውን ነገር ማረም ካልቻልክ ደካማነትህን መጠራጠር መቻል አለብህ። ደካማ ነኝ ብለህ ማመን አለብህ። ዘጠና ደቂቃ ሙሉ ስህተትህን እያየህ ማረም ካልቻልክ በእርግጥ ደካማነትህን ነው የሚያሳየው። አሰልጣኞች ለትውልዱ ማዘን አለባቸው። ውጤት ሊያመጣ የሚያስችል ስራ መስራት አለባቸው።”

*የፊታችን አርብ የዚህን የዘጠናዎቹ ድንቅ ተከላካይ የእግርኳስ ህይወት አስመልክቶ ያዘጋጀነውን መሰናዶ የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እያሳወቅን ዐብይ ወደፊት በኢትዮጵያ እግርኳስ ማደግ ዙርያ የሚያስባቸውን ዕቅዶች አናግረን ይዘን እንመለሳለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ