“የዘመኑ ከዋክብት ገጽ” ከከነዓን ማርክነህ ጋር..

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካሉት ድንቅ አማካዮች አንዱ ነው። ጥሩ የኳስ ክህሎት፣ ግዙፍ ተክለ ሰውነት እና ቀልጣፋ የሆነው ይህ አማካይ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በሊጉ በትልቅ ደረጃ ከሚጠቀሱት አማካዮች አንዱ ለመሆን በቅቷል። የእግርኳስ ሕይወቱን በአዳማ ከተማ ተስፋ ቡድን ጀምሮ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ከተማ የተጫወተው ከነዓን ከ2010 ጀምሮ ወደ አሳዳጊ ክለቡ አዳማ ከተማ ተመልሶ በመጫወት ላይ ይገኛል። በሁለት አጋጣሚዎችም የውጭ ዕድሎች አግኝቶ በአንዳንድ ጉዳዮች ዝውውሩ ከሽፎበታል።

ለወጣት እና ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ከነዓን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን መሰለፍ የጀመረ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያት ከክለብ አልፎ የብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች የሚሆንበት ዕድልም እንዳለ ይገመታል። ከዚህ አማካይ ጋር ያደረግነውን አዝናኝ ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ጊዜውን የሚያሳልፍበት …

ጊዜዬን በቤት ውስጥ ነው የማሳልፈው። በግል እንቅስቃሴዎች በመስራት እና ከቤተሰቦቼ ጋር ጥሩ ግዜ በማሳለፍ እገኛለው። በሳምንት ለአራት ቀናት በቤት ውስጥ የሚሰሩ ስፖርቶች እሰራለሁ።

እግር ኳስ ተጫዋች ባይሆን …

እግር ተጫዋች ባልሆን አናጢነት ላይ የምሰማራ ይመስለኛል። ያደግኩበት ሰፈር በአናጢነት የተሰማሩ ብዙ ናቸው፤ ገና ታዳጊ እያለሁም ሞካክሬ ነበር። ኳስ እየተጫወትኩ በጎን ለማስኬድ ሞክሬ ነበር።

የማይረሳው ጎል እና አመቻችቶ ያቀበለው..

የማልረሳት ጎል ሽረ ላይ ያስቆጠርኳት ግብ ነች። አዳማ የተካሄደ ጨዋታ ነበር ግቧ በአሪፍ መንገድ ነበር ያገባኋት። የማልረሳው ያቀበልኩት ኳስ ደግሞ ከመከላከያ ስንጫወት ሁለት ለግብ የሆኑ ኳሶች አቀብዬ ነበር። ለበረከት ደስታ እና ለዳዋ ሆቴሳ። ሁለቱም ኳሶች አልረሳቸውም።

በተቃራኒ ሲገጥመው የሚያስቸግረው

በተጋጠሚ ስገጥመው ያን ያህል ያስቸገረኝ ተጫዋች የለም። የአጥቂ አማካይ ስለሆንኩ በደምብ ወደ ተከላካዮች የመጠጋት ዕድል አገኛለው። እስካሁን በጣም ያስቸገረኝ ይህ ነው ባልልም የፈተነኝ ግን አስቻለው ታመነ ነው።

ከማን ጋር ቢጣመር …

በአማካይ ቦታ ላይ ከኤፍሬም ዘካርያስ እና ብሩክ ቃልቦሬ ጋር ብጣመር ደስ ይለኛል። ከነሱ ጋር ስጫወት ምቾት ይሰማኛል በሜዳ ላይ ከሚረዱኝ ሰዎች መሀከል ናቸው። የአዳማ ቆይታችን ብዙ ጊዜ የቆየ ነበር። ጥምረቱም በጣም አሪፍ ነበር።

ለመጀመርያ ጊዜ በአካል ሲያገኘው ስሜታዊ ያደረገው ተጫዋች

ጊዜው ትንሽ ቆየት ስላለ በትክክል አላስታውሰውም። በአዲስ አበባ ከተማ እያለው ነው ለመጀመርያ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ የተጫወትኩት፤ ያኔ ሳልሀዲን ሰዒድን በጣም ስለማደንቀው እሱን ለመጀመርያ ጊዜ ሳየው ስሜታዊ ሆኜ ነበር።

ከኳስ ውጭ የሚያዝናናው ..

ከኳስ ውጭ አብዛኛው ጊዜዬን በእንቅልፍ ነው ማሳልፈው። መፅሐፍ ማብበብም ደስ ይለኛል።

በእግር ኳስ የቅርብ ጓደኛው..

በእግር ኳስ ውስጥ የቅርብ ጓደኛ የለኝም፤ ማለቴ ይህን ያህል የቅርብ አማካርዬ ምናምን የሆነ ተጫዋች የለም። ግን በሜዳ ላይ በጣም የምግባባቸው ዳዋ ሆቴሳ፣ ሚካኤል ጆርጅ እና ብሩክ ቃልቦሬ ናቸው። ሜዳ ውስጥ እንዲህ ብናደርግ ምናምን ብዬ የምቀርባቸው እነሱ ናቸው።

የማይረሳው አጋጣሚ ..

በ2010 በመጨረሻ ሳምንታት ዋንጫ ያጣንበት ጊዜን አልረሳውም። በዋንጫ ፉክክሩ መዝለቅ የምንችልበት አጋጣሚ እያለ በአንዳንድ ነገሮች ወደ ኃላ ቀርተን ዋንጫ ያጣንበት ጊዜ ነበር።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ