የዳኞች ገፅ | የጥንካሬ ተምሳሌቱ ቦጋለ አበራ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከጀመረበት ከ1990 ጀምሮ እስካሁን ለሃያ ሁለት ዓመታት በማጫወት በጥንካሬ መዝለቅ የቻለው የቀድሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቦጋለ አበራ የዛሬ የዳኞች ገፅ እንግዳችን ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት በጀመረው የዳኞች ገፅ አምዳችን የቀድሞ አንጋፋ ዳኛ እና ኮሚሽነር ጌታቸው ገብረማርያምን እንግዳ አድርገን ማቅረባችን ይታወቃል። የዛሬው እንግዳችን ደግሞ ለ31 ዓመታት ከጥንካሬ እና ከመልካም ስብዕና ጋር በዳኝነት መዝለቅ የቻለው ረዳት ዳኛ ቦጋለ አበራ ነው። ቦጋለ ከሰማንያዎቹ ትውልዶች ከሙሉጌታ ከበደ እና አሰግድ ተስፋዬ አንስቶ መሐል ላይ ያሉትን ትውልዶች ከዳዊት እስጢፋኖስ ፣ ሳላዲን ሰዒድ አልፎ አሁን እሳካሉት አቡበከር ናስር ሱራፌል ዳኛቸው ትውልድ ድረስ አጫውቷል ፤ እያጫወተም ይገኛል። በአዲስ አበባ ዑራኤል አካባቢ የተወለደው ይህ የጥንካሬ ተምሳሌት የሆነው ዳኛ በዳኝነት ዘመኑ ያጋጠሙትን አዝናኝ እና አሳዛኝ ገጠመኞች እንዲሁም ይሄን ያህል ዓመት አቋሙን ጠብቆ የዘለቀበትን ሚስጢር አሁን ለሚገኘው ትውልድ ካስተላለፈበት መልዕክቱ ጋር አካተን ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ አዘጋጅተነዋል።

ወደ ዳኝነቱ ከመግባትህ በፊት እግርኳስን ትጫወት ነበር ?

በትልቅ ደረጃ አልተጫወትኩም እንጂ አንደማንኛው ሰው በሠፈር ውስጥ በቀበሌ ደረጃ እና በትምህርት ቤት ተጫውቼ አልፍያለው። እግርኳስ ከልጅነቴ ጀምሮ የማዘወትረው ስፖርት ነበር።

ታዲያ ዳኛ እንድትሆን ያነሳሳህ ምክንያት ምንድን ነው?

ዳኛ ለመሆን እድገትህ ይወስነዋል። እድገትህ ስል ምን ለማለት ነው። በእግርኳስ አካባቢ የምትኖር ከሆነ ያው ሁሉም ሰው ዝንባሌው ከሚውልበት ይጀምራል። በነገራችን ላይ ከስምንት ዓመቴ ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታስየም ኳስ እያቀበልኩ ነው ያደኩት። በዚህ ወቅት እነ ዓለም አሰፋ ፣ ጌታቸው ገ/ማርያም ፣ በቀለ ኪዳኔ እና ሌሎችም ስመጥር የሆኑ ዳኞችን ሜዳ ውስጥ እያየው ነው ያደኩት። ይህ ብቻ አልነበረም። ድሮ ዳኞች በእረፍት ሰዓት ይቀርብላቸው የነበረው ሻይ ነበር። እርሱን እየያዝኩ ልሰጣቸው ዳኞች ክፍል እገባ ነበር። በዚህ አጋጣሚ እነርሱን እየተመለከትኩ የዳኝነት ፍቅር ውስጤ እያደረ መጣ። እንደ አጋጣሚ በአዲስ አበባ ስታድየም የዳኝነት ስልጠና እንደሚሰጥ በድምፅ ማጉያ ሲነገር ለምን አልማርም ብዬ በ1982 በጀመርኩት የዳኝነት ስልጠና እስከ ኢንተርናሽናል ዳኛ ድረስ መድረስ ችያለው።

ፌደራል ዳኝነትን መቼ አገኘህ? ኢንተርናሽናል ዳኝነቱንስ ? ዳኝነት ስትጀምርስ በረዳት ዳኝነት ነው ?

በቀድሞ ዘመን ረዳት ዋና የሚባል ነገር የለም። በቅርቡ ነው ዳኛ በየፊልዱ የተከፈለው እንጂ በኛ ጊዜ አንድ ዳኛ ሁሉንም ኮርስ ይወስድና እየተቀያየረ ሁለቱንም ያጫውታል ፤ የዳኝነት እጥረት ስለነበር። በኃላ ነው ኢንስትራክተሮች እና ኮሚቴዎች አይተው ‘ረዳትነቱ ላይ የተሻለ ነገር ስላለህ በረዳትነቱ ብትቀጥል ጥሩ ነው’ በማለት የሰጡኝን ሀሳብ ተቀብዬ ወደ ረዳት ዳኝነት ልሆን የቻልኩት። ፌደራል ዳኛ የሆኑኩት ከሰባት ዓመት በኋላ በ1989 ሲሆን በ2002 ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆኜ ለአንድ ዓመት ብቻ አገልግያለው። በኢንተርናሽናል ዳኝነቱ ብዙም አልቀጠልኩበትም፤ አሁን በፌደራል ዳኝነት እያገለገልኩ እገኛለው።

ከአንተ ጋር ዳኝነት የጀመሩ ሁሉ አሁን አቁመው ወደ ኮሚሽነርነቱ ገብተዋል። በዚህ ዘመን ደግሞ የአካል ብቃቱ ፈተና ጠንከር ያለ ሆኗል። እንዴት ነው አንተ ፈተናውን በብቃት የምታልፈው?

በዓመት ውስጥ በተለያየ ጊዜ ውስጥ የአካል ብቃት እንዲሁም የንድፈ ሀሳብ ፈተና ይሰጣል። በእኔ ፈተናውን ማለፍ ብዙዎች ይገረማሉ። የሚያደንቁኝ ሁሉ አሉ። አንተ ባትሮጥም ንፋስ ይወስድሀል እያሉ ይቀልዳሉ። ፈተናውን የማለፌ ምክንያት ምንም የተለየ ነገር ኖሮ አይደለም። ራሴን በደንብ እጠብቃለው። ሁሌም ራሴን ወደ ጦርነት እንደሚሄድ ወታደር በደንብ አዘጋጃለው። ፈጣሪም ረድቶኝ ይሄው ከዓመት እስከ ዓመት ፈተናዎቹን እያለፍኩ እዚህ ደርሻለው።

ማንም ሰው ይሄን ያሳካዋል ብዬ አልጠብቅም። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ1990 ከጀመረ ጀምሮ እስካሁን ለ22 ዓመታት ከአዲስ አበባ ክልል እየተዘዋወሩ ማጫወት እጅግ ፈታኝ ነው። ይሄን ያህል ዓመት በጥንካሬ የመዝለቅህ ሚስጥር ምንድን ነው ?

ዋናው ፍላጎት እና እራስህን ለሙያው መስጠት ነው። በመቀጠል ይህ ሙያ የሚጠይቀውን ነገር ማሟላት ነው። አንደኛ የአካል ብቃትህን ሁሌ መከታተል ነው። ሁለተኛ ራስህን ካልባሌ ቦታዎች ማራቅ ነው። ሦስተኛ ስለሙያው ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንዲኖርህ በየጊዜው የሚወጡ ህጎችን ማንበብ እና ያነበብከውን ደግሞ ወደ ተግባር መቀየር ነው። ይህ ይመስለኛል እስከ ዛሬ በዳኝነት ውስጥ እንድቆይ ያደረገኝ።

ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር ከዛም አስቀድመው ከአንተም በኃላ የመጡ በተለያየ ምክንያት ዳኝነትን አቁመው ወደ ሌላ የስራ መስክ ተሰማርተዋል። አንተ ብቻህን ግን አለህ። ብቻህን በመሆንህ ብቸኝነት ይሰማሀል ?

ኧረ እንዲያውም በጣም ነው ደስ የሚለኝ ፤ ምንም ብቸኝነት አይሰማኝም። አሁን ካለው ትውልድ ጋር እየተፎካከርኩ መሄድ በራሱ አስደሳች ነው። ይገርምህል እኔ ዳኝነት ስጀምር ካልተወለዱ ከ22 ዓመት ወጣቶች ጋር ነው አብሬ እየሰራው የሚገኘው። እነርሱም በጣም ያከብሩኛል ፤ ይወዱኛል። በዓምላክ ተሰማ ዳኝነትን ሲጀምር የመጀመርያውን ማልያ የሰጠሁት እኔ ነኝ እርሱም ለማስታወሻ እንዳስቀመጠው ይነግረኛል። ዛሬ እርሱ በጥረቱ እና በነበረው ከፍተኛ ዓላማ እዚህ ደረጃ ደርሶ ለኢትዮጵያውያን ዳኞች በዕውቀቱ እና በቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ ስትመለከት ትደሰታለህ። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። በዓምላክ እና ቴዎድሮስ ባገኙኝ ቁጥር ‘አንተ እኮ ለእኛ ሎው ኦፍ ዘጌማችን ነህ’ ይሉኛል። ከዚህ የበለጠ ምን የሚያስደስት ነገር አለ ?

አሁን ካለው ትውልድ ጋር መላመድ አትቸገርም ? የዕድሜ ልዩነት አለ። አብዛኛዎቹ ከአንተ በኃላ የመጡ በመሆኑ?

የሚገርምህ ይሄን ያህል ዓመት በዳኝነቱ ስሰራ ሚዲያ ላይ አንድም ቀን ቀርቤ አውርቼ አላቅም። ፍላጎቱም አላማውም የለኝም። ሁሉም ሰው ቲፎዞ ይፈልጋል። እኔ ራሴን መግለፅ አልፈልግም ፤ ሰዎች ሁል ጊዜ የተሻሉ ነገሮች እንዲያገኙ ነው የምፈልገው። ለመጀመርያ ጊዜ ነው ይሄን ቃለ መጠይቅ ያደረኩት። እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው። የኢትዮጵያ ዳኞች ስለ እውነት ነው የምልህ ለእኔ ያላቸው አክብሮት በቃላት የምገልፀው አይደለም። ከትንሽ እስከ ትልቁ እውነት ነው የምልህ ለእኔ ያላቸው አክብሮት እና ፍቅር ፈጣሪ የሰጠኝ እንጂ በምንም የማገኘው አይደለም። እኔ ደግሞ ያለኝን ልምድ በምንም መንገድ ልደብቅ አልፈልግም። ያለኝን ልምድ ሁሉ አካፍላለው። እነሱም የሚሰጡኝ ግብረ መልስ አለ ፤ ጥሩ እንደሆንኩ ይነግሩኛል። አንተ ሁሌ ራስህን ጥሩ ነኝ ልትል ትችላለህ የበለጠ ግን ስለእኔ እነርሱ ይመስክሩ። ስለዚህ አሁን ካለው ትውልድ ጋር በደንብ ተግባብቼ ነው የምሰራው።

አብረውህ ያሉት ዳኞች ብቻ ሳይሆኑ የምታጫውታቸው ተጫዋቾች ከአንጋፋዎቹ እስከ አሁኖቹ ድረስ ያከብሩሀል ? ይሄስ እንዴት ነው?

በመሠረቱ ምን እንደሆነ ታውቃለህ። አንተ ሰዎችን ስታከብር ነው ሌሎች አንተን የሚያከብሩህ። እኔ ለተጫዋቾች ትልቅ ክብር ነው ያለኝ። ከተጫዋቾች ጋር ጤናማ ግኑኝነት ነው ያለኝ። ለእኔም እስከዛሬ ለመቆየቴ አንዱ አስተዋፅኦ እርሱ ነው ብዬ አስባለው። ሜዳ ውስጥ መወሰን ያለብኝን ነገር በትክክል ነው የምወስነው ተጫዋቾች ራሳቸው ያውቃሉ። ጤናማ ቅርርቡ እንዳለ ሆኖ ግን ማንም ሰው ወንድሜም ቢሆን እንኳን የሚጫወተው ህግ ህግ ነው እኔ ጋር። በዚህ የተነሳ ተጫዋቾች ለኔ ያላቸው ከበሬታ ትልቅ ነው። ከበፊትም አዳነ ግርማን ፣ ሳላዲን ሰዒድን ከፕሮጀክት ጀምሮ እስካሁን እያጫወትኩ ነው። በኢትዮጵያ ተጫዋቾች ውስጥ እኔን ነክቶ ያላለፈ የለም። አንዋር ሲራጅ(ትንሹን) ፣ ባዩ ሙሉ ፣ ዘሪሁን ሸንገታ ፣ ፋሲል ተካልኝን ጨምሮ ከታች ከ “ሲ” ቡድን ጀምሮ ነው አጫውቼ ያመጣኋቸው። እስካሁን ድረስ መጥፎ ባህሪ ቢኖረኝ ኖሮ ይጠሉኝ ነበር። አሁንም የት እንደሆኑ ሳላያቸው መኪና እያቆሙ ቦጌ እያሉ ወርደው ሰላም የሚሉኝ ጥሩ በመሆኔ ነው። እነርሱን በማክበሬ ነው እኔም ክብር ያገኘሁት።

ከአንተ ጋር ዳኛ ሆነው ያጫወቱ፤ ለምሳሌ ይግዛው ብዙዓየሁ ፣ ሰለሞን ገብረሥላሴ፣ ሸረፋ ዶሌቾ ሌሎችም አሁን ኮሚሽነሮች ሆነው አንተን እና ጨዋታውን ይቆጣጠራሉ። እንዴት ነው ነጥብ አሰጣጥ? አድሎ አለ ?

(እየሳቀ) ኧረ እንዲህ ያለ ነገር የለም። እንዲያውም እነርሱ እኔን የጥንካሬ፣ የጥረት ምሳሌ ነው የሚያደርጉኝ። ከቦጋለ ጋር ከዚህ በፊት አብረነው ስለስራን የሚል ነገር የለም ሁሉም በስራው ነው የሚመዘነው። ሰው ነኝ እና ባጠፋ እና ብሳሳት በሚገባ ያርሙኛል።

የመጀመርያ ዳኛ ስትሆን እና አሁን የሚከፈልህ የሙያ አበል ስንት ነበር ?

(በጣም እየሳቀ) ኧረ አይነሳ ኡ…! መነሻ በሆነኝ በአዲስ አበባ ደረጃ ከሆነ ሰባት ብር በኢትዮጵያ አርባ አምስት ብር ነበር። አሁን እንደ ጊዜው ከፍ ብሎ በመቶዎች የሚቆጠር ሆኗል። ይህም ቢሆን በቂ አይደለም ዳኞች እንደሚሰጡት አገልግሎት በቂ ክፍያ እየተፈፀመ አይደለም።

በዚህ ሁሉ የዳኝነትህ ዘመን ያጋጠመህ አሳዛኝ እና አስቂ ገጠመኝ አለህ ?

የሚገርምህ 1991 መሰለኝ ሀዋሳ እና ቡናን ሀዋሳ ላይ እናጫውት ነበር። ከዚህ በፊት በዓመቱ ትንሽ ረብሻ ብጤ ነበር። እነ አሰግድ ተፈንክተውበት የነበረበት ማለት ነው። ይሄኛው ጨዋታ በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ውጥረት ነበረው። በቡና በኩል እነ ካሳዬ አራጌ ፣ አሰግድ ተስፋዬ ፣ ዓሊ ረዲ እና ሌሎችም ነበሩ። በሀዋሳ በኩል እነ ግሩም ነፍሱን ይማረው እና ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የነበረው በረከት እና አብይ ነበሩ። ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር። በሆነ አጋጣሚ ከሀዋሳ ከመስመር የተሻገረን ኳስ በግንባሩ አንድ ተጫዋች ጎል ያስቆጥራል። እኔ ደግሞ ጎሉን ያስቆጠረው ተጫዋች ከጨዋታ አቋቋም ውጭ መሆኑን ስላየው ምልክት አንስቻለው። በዛን ሰዓት አጥር የለ ስታድየሙ ድብልቅልቁ ወጣ ሰዉ ወደ ሜዳ ገባ እኔ አጋጣሚ በትሪቡን በኩል ነኝ። ነፍሱን ይማረውና መኩርያ አሸብር አሰልጣኝ እና ይስሐቅ ሽፈራው ሐኪሙ ነበሩ። ከየት እንደመጣ ያላየሁት እየሮጠ መጥቶ መሳርያ (ሽጉጥ) ግንባሬ ላይ ደቀነ ‘ስማ ይህንን ጎል ሻረውና በዚህ ሽጉጥ ግንባርህን ነው የማፈርሰው’ ሲለኝ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩ ተጫዋቾች እየሮጡ መጥተው አድነውኛል። አስበው ድንጋጤውን ፤ ሽጉጥ ግንባርህ ላይ። ከዛ ምን ቢሆን ጥሩ ነው ? ግርግሩ ተረጋግቶ ጨዋታው አልቆ ማታ ከተማ ውስጥ በእግር እየሄድን አንድ ቦታ ራት ልንበላ ሆቴል ገብተን ተመግበን እንደጨረስን ሂሳብ ስንል ተከፍሏል ተባን ማናው የከፈለው ብለን ስንጠይቅ አንዱ መጣ እና እኔነኝ ጌታዬ የከፈልኩት አለን። ሰውዬውን አናቀውም ‘ይቅርታ ለምን ከፈልክ አልነው።’ ‘አላወከኝም ? ሜዳ ውስጥ መሳርያ (ሽጉጥ) ያወጣሁብህ እኔ ነኝ። በኋላ ግን ስረዳ የአንተ ውሳኔ ትክክል ነው። በዚህ ወጣትነት እድሜያችሁ ይህን ትልቅ ኃላፊነት ወስዳችሁ ትክክለኛ ውሳኔ በመወሰናችሁ ልትመሰገኑ ይገባል። ይቅርታ አድርጉልኝ።’ ብሎ የሄደበትን ቀን መቼም አልረሳውም።

በዳኝነት ህይወትህ ያዘንክበት አጋጣሚ አለ?

ብዙ ያዘንኩባቸው ነገሮች ይኖራሉ። ግን መቼም ፈጣሪህን እና ህሊናህን አትዋሸውም የእውነት ለመስራት ጓጉተህ ሰርተህ ለመውጣት ስታስብ የማትጠብቀው ሰው የማይሆን ነገር ሲናገርህ ለስድቡ የተለያዩ ቃላቶች ሲጠቀሙ ያሳዝናል። ይህ ብዙ ቦታ የሚያጋጥመኝ ነው። እኔ እንደማስበው ሰዎች ሳያስቡልኝ ሲቀሩ በጣም አዝናለው።

በዳኝነትህ ያገኘሀቸው የኮከብነት ሽልማቶች አሉ ?

በዳኝነት ቆይታዬ ያላሳካሁት ነገር የለም። በጣም ደስተኛ ነኝ ፤ ሁሉን ነገር አግኝቻለው። ጅማሮዬ በሆነው አዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሁለት ጊዜ ኮከብ ዳኛ ሆኜ ተሸልሚያለው። በኢትዮጵያ በፕሪምየር ሊግ በተከታታይ ሁለት ዓመታት ኮከብ ረዳት ዳኛ ሆኜ ተመርጫለው። በ2000 እና 2001 ማለት ነው። የሀገሪቱን ትልቅ ደርቢ ጨዋታ ቡና ጊዮርጊስን ከ13 ጊዜ በላይ አጫውቻለው። ይህ ለእኔ ትልቅ ስኬት እና ሽልማት ነው።

አሁን ላሉት እና ወደ ፊት ዳኛ መሆን ለሚያስቡ ካለህ ልምድ በመነሳት የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ ልቀበልህ ?

ዳኝነት ማንንም ማስደሰት አይችልም። ለራስህ ግን እርካታ ታገኝበታለህ። ሁለት ቡድኖችን ነው የምታጫውተው አንደኛው አሸንፎ ሲደሰት አንደኛው ሊከፋ ይችላል። አሁን ላሉት ዳኞች የምለው ምንም ዓይነት አጋዥ ነገሮች ባልነበረበት ሰዓት እኛ እዚህ ደረጃ የደረስነው በራሳችን ጥረት ነው። ዳኝነት ከታች ስትነሳ ዕድሉ ሰፊ ነው። ወደ ላይ ስትወጣ እየጠበበ ነው የሚመጣው። አሁን ያሉት ዳኞች የምመክረው ራሳቸውን በዚህ ሀገር ውስጥ ብቻ መገደብ የለባቸውም ራዕይ ሊኖራቸው ይገባል። ‘ለምን በዓምላክ የደረሰበት ደረጃ አልደርስም ?’ ብለው ራሳቸው ማሰብ አለባቸው። ሌላው ቅንነት ፣ የልብ ንፁሑነት ሊኖር ያስፈልጋል። እጃቹሁ ንፁህ ሊሆን ይገባል እላለው። እኔ እንደዚህ ደረቴን ነፍቼ የምናገረው የትኛውም ተጫዋች ፣ የትኛውም ክለብ፣ የትኛውም አሰልጣኝ ስለ ለኔ ይሄን አደረገ የሚል ነገር ካለ ይውጣ። ይሄን የምናገረው ንፁህ ስለሆንኩ ነው። እኔ እኮ እላቸዋለው አሰልጣኝ ዛሬ እዚህ ቢሆን ነገ ሌላ ቡድን ነው የምትሄደው፣ ተጫዋችም ቢሆን እንደዛው። እኔ ግን እዚሁ ሆኜ ነው የምጠብቅህ ስለ እኔ መጥፎ ባህሪ ፣ ጥሩ ነገር ቢኖር እዛ ሄደህ ነው የምታወራው እላቸዋለው። እነርሱም ቦጌ ጋር እንዲህ የለም እያሉ ይመሰክራሉ። ቦጌ ጋር አንድ እና አንድ ሁለት ነው። ሦስት ሆኖ አያቅም። ስለዚህ ሙያቹሁን አክብራቹ ስሩ እላለው።

የቤተሰብ ህይወትህ ?

ባለትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነኝ። በኑሮዬ እና በቤተሰብ ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ