“አሁን ጥሩ ቦታ ደርሻለሁ” ተስፈኛው ተከላካይ መናፍ ዐወል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ብቅ ካሉ ወጣት ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል፡፡ በእርጋታ እና ብስለት ሲጫወት ለተመለከተው በሊጉ ለበርካታ ዓመታት የተጫወተ ያስመስለዋል። ወጣቶችን በማሳደግ ረገድ ሥሙ በመልካም ከሚጠራው አዳማ ከተማ የተገኘው መናፍ ዐወል በዛሬው የተስፈኛ አምዳችን ተመልክተነዋል፡፡

መናፍ ትውልዱ እና ዕድገቱ አዳማ ከተማ ነው፡ እግርኳስን የመጫወት ህልም ኖሮት ጅማሮውን ባያደርግም በትምህርት ቤት የስፖርት ሰዓት ላይ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ግን እሱን እያጎሉ እና ተጫዋች መሆን እንደሚችል እያሳበቁበት መጡ። በተማሪነት ጊዜው በአዳማ ውስጥ በሚደረጉ የትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ ተሳታፊ በመሆን በሚገባ ራሱን ማብቃትን ቢጀምርም ተጫዋች መሆን እንደሚችል የገባው እሱን ሲመለከቱ የነበሩት መጫወት እንደሚችል ግፊትም ማሳደር ሲጀምሩ ነበር።

በትምህርት ቤት ውድድር ላይ በተደጋጋሚ አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ ከቆየ በኃላ ታዲዮስ በሚባል አሰልጣኝ ተጠርቶ እርሳቸው በሚያሰለጥኑበት የታዳጊ ወጣቶች ቡድን ውስጥ በመካተት በፕሮጀክት ታቅፎ ሁለት ዓመታትን ካሳለፈ በኃላ ከ17 ዓመት በታች የፕሮጀክት ውድድር በሚደረግበት ወቅት እሱም ቡድኑን ወክሎ በመጫወት ላይ እያለ ነበር የአዳማ ከተማ “ቢ” ቡድን አባል እንዲሆን ጥሪ የቀረበለት። ወደ ክለቡ እንዲገቡ የተጠሩት ተጫዋቾች በርከት ያሉ በመሆናቸው በሙከራ ዕድል ሲሰጣቸው እሱም በዚህ ሙከራ ውስጥ እንዲካተት ተደረገና መናፍም አሳማኝ ብቃቱን በማሳየቱ በ2008 መስከረም ወር ላይ የአዳማ ከተማን የቢ ቡድን መቀላቀል ቻለ። ፈጣን ለውጥን በዚህ ታዳጊ ቡድን ውስጥ ማሳየት በመቻሉ በ2009 በወቅቱ አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ አማካኝነት ወደ ዋናው የአዳማ ቡድን አደገ። ሆኖም ለአንድ ዓመት ከግማሽ ከሱ የተሻለ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በዋናው ቡድን በመኖራቸው ዕድሉን በጊዜ ማግኘትን ግን አልቻለም። በአዕምሮ ረገድ ጠንካራ እንደሆነ የሚነገርለት መናፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚገባ ራሱን እያዳበረ እና እያበቃ በመምጣት በተለይ በዚህ ዓመት የአዳማ ከተማ ወሳኝ ተጫዋች እና ተከላካይ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

ዘንድሮ በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ተወዳጅ መሆን የተየቻለው እና በሜዳ ላይ ጠንካራ አቅሙን ሲያሳይ ያየነው መናፍ ዐወል ስለ እግርኳስ ህይወቱ እና ቀጣይ እቀዱ ይህን ብሎናል፡፡

“ወደ አዳማ ዋናው ቡድን ሳድግ ትንሽ ተቸግሬያለሁ፤ ለመልመድም ትንሽ ጊዜ አስፈልጎኝ ነበር። ሦስተኛ ዓመቴ ውል መጨረሻዬ ስለነበር ይህን ዓመት መጠቀም አለብኝ ብዬ አስቤ ስለነበር በደንብ ተጠቅሜበታለሁ። ሊጉ ይከብዳል፤ ግን ከጎኔ የሚጫወቱ ተጫዋቾችም አሰልጣኞችም ስላሉ ብዙም እንዲከብደኝ አልሆነም። አይዞህ እያሉ ስለሚያበረቱኝ ብዙም ችግር አላመጣብኝም። አሁን ጥሩ ቦታ ላይ ደርሻለሁ። በቀጣይ ሁሉም ተጫዋች እንደሚያስበው ማሰብ እፈልጋለሁ። በትልቅ ደረጃ መጫወትን ፈልጋለሁ፤ አዳማ መቀጠልን እመኛለሁ። ካለኝ አቅም አንፃር የተሻለ ነገርን ለማግኘት እና የተሻለ ቦታ ላይ ለመቀመጥ ጠንክሬ መስራት አለብኝ። ይሄን ማድረግ ግድ ነው። አንድ ተጫዋች የጎደለውን ያውቃል፤ እኔም የጎደለኝን ለማሟላት መስራትም እንዳለብኝ ይሰማኛል።

“አሁን እግር ኳስ በኮሮና ምክንያት የለም። እኔም ይህን ጊዜ ቁጭ ብዬ አላሳልፈውም፤ ጠዋት ጠዋት እንቅስቃሴዎችን እሰራለሁ። ከዛ በመቀጠል ግን ቤት ነው የምዋለሁ፤ ከቤተሰቤ ጋር እጫወታለሁ፣ ሲመሽ ደግሞ ፊልሞችን አያለሁ። አንድ አንድ የኳስ ቪዲዮኖችንም እያየሁ አሳልፋለሁ።

“ቤተሰቦቼን ማመስገን እፈልጋለሁ። ሲቀጥል አሰልጣኞቼ የነበሩትን ኤፍሬም፣ ዳዊት የልጅነት አሰልጣኜ ምስጋናውን፣ ጋሽ በቄን፣ አሰልጣኝ አስቻለው፣ ተገኔ ነጋሽን፣ ደጉ ዱባሞን፣ ሀኪም ጃክን እንዲሁም አሸናፊ በቀለ ዕድሉን ስለሰጠኝ ማመስገን እፈልጋለሁ”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ