ስለ ኢዮብ ማለ (አሞካቺ) ሊያውቋቸው የሚገቡ ዕውነታዎች

ብዙዎች ሜዳ ላይ ቀልደኛ ነው ይሉታል። እንደ አጥቂነቱ ግብ ለማስቆጠር ካለው ፍላጎት የተነሳ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾችን በቀልዱ በማፍዘዝ ያለመውን ግብ ከመረብ በማሳረፍ ቡድኑ ውጤት ይዞ ከሜዳ እንዲወጣ የእሱ ድርሻ እጅግ ላቅ ያለ መሆኑን አብረውት የተጫወቱ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ይደመጣል፡፡

እልህኝነቱ እና አልሸነፍ ባይነቱ ከተጫዋችነት ጊዜው አንስቶ እስከ አሁኑ የአሰልጣኝነት ህይወቱ የዘለቀው እዮብ ማለ ወይንም አሞካቺ ትውልዱ እና ዕድገቱ የእግር ኳስ ከተማ እንደሆነች በሚነገርላት አርባምንጭ ከተማ ቀበሌ 03 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በልጅነት ዕድሜው ወላጅ አባቱ በስራ ምክንያት ኑሯቸውን አዲስ አበባ ለማድረግ ሲገደዱ እሱም አባቱን ተከትሎ ወደ መዲናይቱ ተጓዘ። ምንም እንኳን ትውልዱ አርባምንጭ ውስጥ ቢሆንም ከእግርኳስ ጋር የተዋወቀው ግን ወደ አዲስ አበባ ካመራ በኃላ እንደሆነም ይናገራል።

በተጫዋችነት ህይወቱም በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሙገር ሲሚንቶ ፣ ወሎ ኮምቦልቻ ፣ ታሪካዊ በሆነው አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፣ አየር መንገድ ፣ ወንጂ ስኳር እና መተሐራ ስኳር ለአስራ ስድስት ዓመታት ያህል ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ 2000 ላይ ኳስን ካቆመ በኃላ ከፋርማሲስት ትምህርት ጎን ለጎን የአሰልጣኝነት ስልጠናን ወስዶ 2003 አርባምንጭ ከተማን በረዳት አሰልጣኝነት ፣ በ2008 ሀድያ ሆሳዕናን በረዳትነት 2009 እስከ ግማሽ ዓመት በዋና አሰልጣኝነት ሰርቷል። በዛኑ ዓመትም አርባምንጭ ከተማን ለሁለተኛ ጊዜ በዋና አሰልጣኝነት ደረጃ በመያዝ ለአጭር ጊዜ ቆይታን አድርጓል፡፡ ደሴ ከተማን እና አሁን የለበትን ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን ይዞም ወደ ከፍተኛ ሊጉ አሳድጓል፡፡

አጭር ቢሆንም ከተከላካዮች መሀል ተነስቶ ግብ ሲያስቆጥር ጉልበተኛ እና ቀልደኛ መሆኑ ረድቶታል ሲባል ይሰማል፡፡ ‘ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ እንኳን ራሱን ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ እንዳለ ይቆጥራል’ ሲሉም አብረውት በወቅቱ ሲጫወቱ የነበሩ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በአንድ ወቅት በቅዱስ ጊዮርጊስ የልምምድ ሜዳ ላይ የዕርስ በዕርስ ጨዋታ ወቅት ለአንደኛው ቡድን ሲጫወት ጎል እንቢ ይለዋል። ከልምምድ በኃላ በስብሰባ ወቅት አንድ የክለቡ አመራር ይመጣና “የት አለ ከአርባምንጭ የመጣው ? አንተ ነህ አሞካቺ ? አዎ ለምን ግብ እንቢ አለህ ? ሲል በቁጣ ይናገረዋል። እሱም “አዎ አሞካቺ እኔ ነኝ ፤ ታድያ 1500 ብር እየበላሁ ዋናውን አሞካቺ ልሁንህ እንዴ ? ” ብሎ በመመለስ የቡድኑን አባላት ፈገግ አሰኝቷል። እኛም በዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከብ ቀልደኛው እና ብሎም ፊት ለፊት ተናጋሪ እንደሆነ የሚነገርለትን እዮብ ማለን ይዘን ቀርበናል፡፡

“ተወልጄ ያደኩት አርባምንጭ ከተማ ቢሆንም ኳስን የጀመርኩት ግን አባቴ አዲስ አበባ ለስራ በመምጣቱ እኔም እሱን ተከትዬ በመምጣቴ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከመጣው በኃላ አባቴ ለቅዱስ ጊዮርስ ቢ እንድሞክር አደረገኝ። በወቅቱ እኔም ጥሩ ስለነበርኩኝ እነ ፋሲል ተካልኝ ፣ ባዩ ሙሉ ፣ ጌትነት ሞትባይኖር ዓይነት ተጫዋቾች ጋር ተቀላቀልኩ። ቡድኑም በጣም ከባድ ነበር ፤ አሰልጣኛችንም ስዩም ከበደ ነበር። በጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን የቆየውት አንድ ዓመት ብቻ ነበር። አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ አይቶኝ በቶሎ አሳደገኝ፡፡ በ’ቢ’ቡድን ቆይታዬ ከነፋሲል ጋር ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለሁ። ቻምፒዮንም ሆኛለሁ። እኔም ትኩረት ለራሴ እየሰጠሁ ስመጣ የእግር ኳስ ህይወቴ ትክክለኛ መንገዱን ያዘ። ተጫዋች መሆኔንም አረጋገጥኩ።

“በቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ ዓመታትን አሳልፌያለሁ አንደውም አሞካቺ የሚለውን ስም ራሱ ያገኘሁት በክለቡ እያለሁ ሙሉጌታ ከበደ ነበር ያወጣልኝ። ይሄን ስም ሲያወጣልኝ እንዲሁ እንደቀልድ አልነበረም ‘እኔን የሚተካኝ ከአርባምንጭ የመጣው አሞካቺ ነው’ እያለ ይናገር ስለነበረም ጭምር ነው፡፡ ጊዮርጊስን ከደቡብ መጥቶ የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች እኔ ነኝ። ከዛ በመቀጠል ነው የሰፈሬ ልጅ የሆነው ስንታየው (ቆጬ) የተከተለኝ። አንድ ላይ አብረንም ጭምር ነው የተማርነው። እሱ ጉሙሩክ ገባ ከዛ እኔ ጊዮርጊስ ቢ እየተጫወትኩኝ ወደዋናው ቡድን አድጌ ከ1986 እስከ 89 ድረስ በቡድኑ ቆይቻለሁ። ጊዮርጊስን 1990 ላይ ስለቅ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ይፈልገኝ ስለነበረ ሙገር ሲሚንቶም ጥሩ ከፋይ ከሚባሉ ቡድኖች መሀል በመሆኑ ለእኔም 850 ብር ትልቁ ደመወዝ ሆኖ ሲቀርብልኝ ወደ ቡድኑ ገባሁ። ሙገርም ትልቅ ቡድን ነበር። በሙገር ቤትም ሁለት ዓመት ቆየው የሙገር ቆይታዬ ሲጠናቀቅ ወደ ወሎ ኮምቦልቻ ሄጄ የመጫወቱ ዕድሉ ነበረኝ። እንደውም ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እነንዲገባ አድርጊያለሁ። ከዛን በመቀጠል ግን ታሪካዊ ቡድን ወደነበረው አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ነው የተቀላቀልኩት፡፡

“1995 የአርባምንጭ ጨርቃ ደስ የሚሉ ግን የሚያስቆጩ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ። የቡድን ስሜቱ ፣ ትግላችን ፣ አሰልጣኝ መለሰ ሸመና እንዴት ዓይነት ቡድን እንደሰራ ይገርማል። እነ ደጉ ደበበ ወጣቶች ናቸው የዛን ሰዓት ለምሳሌ ደጉ ሚድፊልድ ነበር በሰዓቱ ከዛን በኃላ ነው ተከላካይ የሆነው። እነ አዱኛ ገላና አንተነህ መሳ ፣ ስለሺ ዊሀ ያለው የቡድን መንፈስ አክብሮቱ ደስ ይል ነበር። ዘጠና ደቂቃው ያለቀ አይመስለንም ነበር። እንደአሁኑ የአርባምንጭ ሜዳ ሳር አይምሰልህ አፈር ነው ፤ እሳት ነው። ከስር እሳት ከላይ የአርበምንጭ ፀሀይ አለ። ዳቦ ሆነን ነው የምንጫወተው። በዛ ላይ ሜዳው እሾክ ነበረው። ብዙ መስዋትነት የተከፈለበት ቡድን ነበር ያ ቡድን። እኔ ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና አለመሳተፋችን ዛሬም ይቆጨኛል። የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያጣነው ራሱ ብዙ ደባ ተሰርቶብን ነው፡፡ ተሳክቶልን በአፍሪካ ውድድር ላይም ተሳታፊ ሆነን ቢሆን ኖሮ ብዙ ፈር መቅደድ እንችል ነበር። በአንዳንድ ምክንያቶች ተቀጨ እንጂ አሁንም ዕድሉ አለ። ያንን የቀደመውን የአርባምንጭ ቡድንን በተጫዋችነት አገልግያለሁ ያን ፈጥሮ ማሰልጠን አሁንም ብችል ደስ ይለኛል። ጥሩ አመራሮች ከመጡ ህዝቡ ያውቀዋል እውነታውን። ነገ ፈጣሪ ከፈቀደ በብሔር በጎሳ ሚል አመራር ካልመጣ ተመልሼ ያን ታሪክ መመለስ እፈልጋለሁ። አርባምንጭ በተጫዋቾች ሀብታም ናት። ስንቶቹ ግን ባክነዋል። ሴቻ ሲቀላ ተብሎ ሳይከፋፈል ያን ቱባውን ጨረቃጨርቅ የነበረውን ቡድን አሁንም ከሰራን ካመጣነው እንደ አርባምንጭ ቡድን ይኖራል ብዬ አላስብም። ዘንድሮ ኮሮና ባይመጣ መሳይም ሞክሮት ነበር። ማንም መጥቶ ይስራ የአርባምንጭ ስም ተነስቶ እንዳይ ነው አሁንም የምፈልገው። መልካም አመራሮች ከመጡ ድጋሚ ሄጄ በቁጭት አርባምንጭን ማገልገል እፈልጋለሁ። በፕሪምየር ሊጉ ላይም ዋንጫ ማንሳት ፈልጋለሁ። ለእኔ የ1995ቱ ቡድን ሞዴሌ ነው። ያንን መነሻ አድርጌ አሁን አርባምንጭ ላይ መስራት እፈልጋለሁ። እውነት ነገ ስትወጣ አምላክ የፈቀደ ዕለት ያንን ቡድንን በቁጭት አስታውሰዋለሁ ፤ ተተክቶ ባየው ደስ ይለኛል፡፡

“ከአርባምንጭ እንደለቀኩ ወደ አየር መንገድ ሄድኩኝ። በአየር መንገድም ደስ የሚሉ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ እንደነ ታረቀኝ አሰፋ (ዳኜ) ጥላሁን መንገሻ እና እነ ይልማ ካቻማሌ ዓይነት ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ ነበሩ። በጣም ጠንካራ ቡድን ነበረ። ቡድኑም የሚወዳደረው አዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ ነበር፡፡

“እግር ኳስ ደስ እያለኝ በፍቅር የምጫወተው ጨዋታ ነው፡፡ አየር መንገድ ውስጥ ጥሩ ጊዜን በማሳለፌ አሰልጣኝ ወርቁ ደርገባ ወንጂን ይዞ ስለነበረ ወደዛ ሲጠራኝ ወንጂ ተጫውቼ አሳልፌያለሁ። ከሁለት ዓመት በኃላ ወንጂን ለቅቄ መተሀራም ሄጄ ነበር። እነ ሺማሙ ፣ ጊግስ እና ቴዲ ባሪያው የነበሩት ቡድን ነበር ሌሎች ቡድኖች ውስጥ በቆየውት ልክ እዚህም ሁለት ዓመት ከቆየው በኃላ 2000 ላይ እግር ኳስን አቆምኩኝ። ወደ አሰልጣኝነት ህይወት ከመግባቴ በፊት መማር አለብኝ ብዬ ሦስት አመት ተማርኩ። በፋርማሲ ሙያ ከአፍሪካ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተምሬ ተመረኩኝ። ከዛን ወዲያው የአሰልጣኝነት ትምህርት ሲመጣ የአንደኛ ደረጃ ስልጠና መውሰድ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ አሰልጣኝ አብረሀም ተብለሀይማኖት መተሀራ ያሰለጥነኝ ስለነበረ እሱ ነው እንደውም ‘የአሰልጣኝነት ኮርስ መውሰድ አለብህ’ ብሎ የነገረኝ እና የወሰድኩት።

“ልክ ትምህርቴን ተምሬ የአሰልጣኝነት ስልጠናን እንደጨረስኩ ወደ አርባምንጭ ተመለስኩ። እኔ ኳስን ስጫወት የሚያውቁኝ የአካባቢው ልጆች ፓራሜድ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚባል ቡድንን እንድይዝ ነገሩኝ። ቡድኑን ሰብስቤ ያዝኩኝ። ከዛን ወልቂጤ ላይ የክልሉ ውድድር ነበር። እዛ ውድድር ላይ ቡድኑን አሳልፌ ብሔራዊ ሊግ ለመግባት ሻሸመኔ ላይ ቡድኑን ይዤ ቀረብኩ። ቡድኑም በወቅቱ አራተኛ ሆኖ ጨረሰ። ወደ ብሔራዊ ሊጉ ገባ። ያን ቡድን ይዤ ውጤታማ በመሆኔ በዓመቱ አርባምንጭ ከተማን ከአሰልጣኝ ታደሰ መላኩ ጋር እንድይዝ ጥሪ ቀረበልኝ። እኔም ደስ ብሎኝ ወደ ቡድኑ ገባ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ፈርሶ ከረጅም ጊዜ በኃላ የተመሠረተ ቡድን በመሆኑ አንድ ነገር ማሳየት አለብን ብለን ቆርጠን ተነሳን። ከየሠፈሩ ከየአካባቢው ልጆችን ሰበሰብን በአምስት መቶ እና ስድስት መቶ ብር እነ እንዳለ ከበደ ፣ አንተነህ ተስፋዬ እንደ እነሙሉአለም መስፍን (ዴኮ) እና ሌሎች ወጣቶችን ከየአካባቢው ጠርተን በአነስተኛ ደመወዝ ያንን ቡድን 2003 ላይ ፕሪምየር ሊግ አስገባነው። የአርባምንጭ የኳስ ትንሳኤም የመጣበት ሰዓት ነበር። ብዙ ስራ በቡድኑ ውስጥ ሰራን። ያው እኛ ሀገር ችግሩ ታች እያለህ የሚያይህ የለም ወደ ላይ ስትወጣ በስራህ ላይ ጣልቃ የሚገባ ይበዛል። እኔ ደግሞ ፊት ለፊት ስለምናገር እንዲህ ዓይነት የድብብቆሽ ጨዋታን ስለማልወድ ስድስት ጨዋታ እየቀረን ለአሰልጣኝ ታደሰ ‘አመሰግናለሁ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ሰርቻለሁ በቃኝ’ ብዬ ጥዬ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ።

“የአሰልጣኝነት ስራን በአንደኛ ደረጃ ብቻ ነበር የምሰራው ወደ አዲስ አበባ እንደተመለስኩ ተጨማሪ ስልጠና እየወሰድኩ ላይሰንሴን ማሳደግ ጀመርኩ። እኚህን እያደረኩ ስመጣ የማሰልጠን ትክክለኛ ህይወቴ ተጀመረ። ከአሰልጣኝ ማንጎ ጋር ሆሳዕናን ይዘናል እስከ መጨረሻው ድሬዳዋ ላይ እስከነበረው ውድድር መቐለ የገባበት ዓመት ነበር። ያን ወቅት ይዘነው ተጉዘናል ሊሳካ አልቻለም። በዓመቱ ማንጎ ሲለቅ ለእኔ ቡድኑን ሰጡኝ። ከዛ እያሰለጠንኩ እያለ በመሀል 2009 ከአርባምንጭ ከተማ ጥያቄ ሲመጣልኝ ወደዛ ሄድኩኝ። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ይዞት አንደኛ ዙር ሊያልቅ ሦስት ጨዋታ ሲቀረው እሱ ሲለቅ እኔ ያዝኩ። በሦስቱ ጨዋታ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ በሜዳችን አሸነፍኩ። ከሜዳ ውጪ ከሀዋሳ ነበረን አቻ ወጣን ከዛ በሜዳችንም የመጨረሻ ጨዋታን አሸንፈን ጥሩ ውጤት ይዘን ጨረስን። በሁለተኛው ዙርም ቡድኑ መጀመሪያ ይዞት ከነበረው ነጥብ በተሻለ ይዞ እየተጓዘ እያለ አሁንም ጣልቃ ገብነቱ ሲመጣ ስራዬንም በአግባቡ ልሰራ ባለመቻሌ ለቅቄ ሄድኩኝ። ከዛ ደሴ ከተማን ይዤ ጥሩ ጊዜ አሳለፍኩ። ወደ ከፍተኛ ሊጉም ይዤው ገብቻለሁ። ጥሩ የሚሰራ እና የሚለፋ በእኛ ሀገር አይከበርም። የግድ ተናጋሪ እና አስመሳይ መሆን አለብህ። የእኔ ባህሪ ደግሞ ከዚህ ጋር የሚሄድ አይደለም። የሞሞዳሞድ ዓይነት ባህሪን ዛሬም ሆነ ነገ ልቀበል አልችልም አሁን ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀንን እያሰለጠንኩኝ እገኛለሁ። ከብሔራዊ ሊግ አምጥቼው በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ ሊግ ላይ እየተወዳደረ ይገኛል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ተቀባይነት አለኝ። ደስ የሚሉ ወቅቶችን አሳልፌያለሁ። ዘንድሮ ውሌ ይጠናቀቃል ቀጣይ ወደየት እንደምሄድ ግን አላውቅም።

“እግር ኳስ በእኔ የማንነት ጥያቄ ነው። ከልጅነት ጀምሮ እኔን ያሰለጠነኝ አስራት ኃይሌ ነው። ከቢ አምጥቶኝ ማሰልጠን ብቻ ሳይሆን እውነትንም ጭምር ነው ያስተማረኝ። እውነት ማለት ደግሞ ተጫዋቾች ዲሲፕሊን መሆን አለባቸው። በዚህ አምናለሁ። በዛኑ ልክ አንድ ተጫዋች የለፋበትን የደከመበትን የላቡን ማግኘነት አለበት። ሜዳ ላይ ጥሩ የሆነ ተጫዋች ይገባል ያላደረገ ደግሞ አይገባም። አሁን የሚገርምህ ነገር ከሰርቪስ ሹፌሩ ጀምሮ ከምግብ ቤት ሰራተኛ ድረስ እግር ኳስ አዋቂ ነኝ የሚል አለ። አሰላለፍ አውጪ እኔ ነኝም የሚሉ አሉ። ያን ሲሉ ደግሞ ከእኔ ጋር አይሄዱም። እከሌ መግባት አለበት እከሌ መውጣት አለበት ይሉሀል። ኃላፊነቱ ለእኔ ከተሰጠኝ ልጠየቅ ምችለው እኔ ነኝ። ይሄ ደግሞ መንገዱ ሆኖ ሳለ በተለይ አርባምንጭ አካባቢ በይበልጥ በስራ ላይ ጣልቃ ይገባ ነበረ። ሁለቴ ቡድኑን ይዤ ሁለቴ ተጋጭቼ የወጣሁበት ምክንያት ምንድነው የአንድ ሠፈር ኃላፊ ይመጣና እከሌ ይግባ ይልሀል። ይሄ ደግሞ ከእኔ ጋር የሚሄድ አይደለም። የውሳኔ ሰው እንድሆን ያደረገኝ ደግሞ አስራት ነው። ባመንክበት ነገር መሞት እንዳለብህ ይነግርሀል። እኔም በአጭር ጊዜ የአሰልጣኝነት ህይወቴ ወጤታማ የሆንኩት የጋሽ አስራትን መርህ ተከትዬ ነው። እና እሰራለሁ እለፋለሁ ከኳሱ ውጪ በጣም ጭምተኛ ነኝ። ወደ ኳሱ ስመጣ ግን አልደራደርም። በተለይ በውጤት በቃ ውጤት ነው። ምማንም ተጫዋች ስርዓት ይዞ መስራት አለበት። የእኛ ሀገር ኮሚቴ ደግሞ ተሞዳሙደህ እንድታልፍ ነው የሚፈልገው ስራ ላይ ስራ ነው ከስራ ውጪ ደግሞ እጫወታለሁ ….(ሳቅ) እንደሁም እንደኔ ፎጋሪ እና ተጫዋች የለም ሜዳ ላይ እለወጣለሁ፤ ኮምፕሊትሊ።

“እኔ ተጫዋችም እያለሁ ይሄ ባህሪዬ አብሮኝ ነበር። ሜዳ ላይአሰልጣኞች ለሚያሰሩኝ ነገር በጣም ሲሪየስ ነኝ። አንድ አሰልጣኝ መግባት ባለብኝ ቦታ ያጫውተኛል። ካልገባውኝ ግን የቡድኑን መንፈስ በመጠበቅ እኔ ከአሰላለፍ ውጪ ብሆን እንኳን ምበላበት ላቤን ጠብ አድርጌ ቤተሰቤንም ማስተዳድርበት ስራዬ ስለነበረ ቡድን የሚከፋፍል ሰው አልወድም። ተጫዋች ሆኜ በአሰልጣኝነት ህይወቴ ውስጥም ይሄንን ነው ይዤ የመጣሁት። በዛን ሰዓት አሰልጣኙ ካመነብኝ ያጫውተኛል ካላመነብኝ አያጫውተኝም። ከአሰላለፍ ውጪ ሆኜ ጓደኞቼን አበረታታለሁ። አስቄያቸው ቀልጄ ነፃ ሆነው ሜዳ እንደዲገቡ ነው የማደርገው። ለምሳሌ አርባምንጭ እያለሁ እነ ደጉ እና አዱኛ ለፍተው መሬት ሲሸለሙ እኛም ተሸልመናል። ይህ የቡድን ስራ ነው። እግር ኳስ በተጫዋችነት ዘመኔ ቡድንን በማፋቀር አንድ በማድረግ አሁንም ድረስ በአሰልጣኝነት ህይወቴ ተጫዋቾቼ ላይ እንዲሰርፅ እያደረኩኝ ነው። ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞችም ይናገራሉ። እነ ወርቁ ደርገባን ብትጠይቅ ይነግሩሀል። ‘እሱ ካለ ቡድናችንን አንድ ያደርግልናል ያነቃቃልናል’ ሲሉ ይናገራሉ። እዛ ውስጥ ግን ቡድን የሚከፋፍል አልተሰለፍኩም ብሎ የሚያሳምፅ ተጫዋችን ተጫዋች ሆኜ እጄን አውጥቼ አጋልጣለሁ። አሁንም ያለኝ ባህሪ ልክ ተጫዋች በነበርኩበት ልክ ነው፡፡

“የተለየ ባህሪ አለኝ ብዬ አላስብም። ሽንፈትን ስለማልወድ ለመሸነፍ ብዙም ቦታ አልሰጥም። ከመጣ ትቀበለዋለህ የተለየ ባህሪ ብዬ በአሰልጣኞችም የሚነገርልኝ ምንድነው ለምሳሌ አንዴ መኮንን ገላነህ (ዊሀ) በጣም ጥሩ ሆኖ በአንድ ወቅት አሰላለፍ ውስጥ አልገባም። አርባምንጭ ጨርቅ ጨርቅ 1995 መሰለኝ ከብርሀን እና ሰላም ነው ጨዋታው በጣም ጠንካራ የስዩም አባተ ቡድን ነበር። አርባምንጭ ሜዳ ላይ ነው እና እጄን አንስቼ ‘ኮች’ አልኩት አሰልጣኝ መለሰን። እኔ የዛን ሰዓት ተቀያሪ ነኝ። ‘ሰሞኑን በሰራነው እንቅስቃሴ መኮንን ከእከሌ ይሻላል ለቡድናችን ውጤት ይጠቅማል።’ ብዬ ፊት ለፊት ተናገርኩኝ። አሰልጣኝ መለሰም እኔ ያልኩት አደረገ። መኮንን ገላናም ገብቶ ጎልም አስቆጥሮ በሱ ጎል 1ለ0 አሸንፈን የወጣንበትን አልረሳውም። አሁን ግን በዚህ ዘመን እሱ ስላልገባ ነው ቡድን የሚበጣጥስብህ እንጂ ጓደኛዬ ነው ከእኔ ይሻላል የሚል የለም። ከማሳመፅ ውጪ የተሻለው እከሌ ብሎ ሳይሆን እኔ ነኝ የሚል ነው የበዛው። ይሄ እንዳይኖር ትኩረት አድርገህ ከሰራህ የኢትዮጵያ ተጫዋች አንዱ ከአንዱ አይተናነስም እና የተለየ ባህሪዬ ማንም ይሁን ማን እጄን አንስቼ የመናገር ድፍረቱ አለኝ። ተቀይሬ በምወጣበት ሰዓት የሚገባውን አስቄ ፎጋግሬ ገብቶ ውጤታማ ሆነን እንወጣለን፡፡

“ሰዎች ስለእኔ እንዲያውቁ የምፈልገው እግር ኳስን በደንብ መስራት አሰልጥኜ ውጤታማ መሆን እንደምችል እና ትልቅ ቦታ መድረስ እንደምችል ሁሉም እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ። አሁን ባለኝ ባህሪም ቢሆን ይሄ ሰውን ጋብዞ አጭበርብሬ መስራትን መቼም አልመኝም። ሰርቼ መብላት እግዚአብሔር በሰጠኝ ሙያ ትልቅ ቦታ መድረስ እየፈለኩ ግን አንድአንዴ የኮሚኒኬሽን ችግር አለብኝ። በብዛት ቤተክርስቲያን ነኝ ከዛ ቤቴ ነው የምውለው። ሁሌም መማር እና ይበልጥ ማወቅ ስለምፈልግ ነገ ለምሰራሁ ምን ማዘጋጀት አለብኝ ሚለውን ከአሁን ተነስቼ እየሰራሁኝ እገኛለሁ እና ሁሌም በማንበብ ሁሌም ራሴን በማሻሻል ላይ ነው ጊዜዬን ማጠፋው። የግድ ሚዲያ ላይ ገብተህ ስለተናገርክ አይደለም። ከማንም ተጫዋች ጋር በገንዘብ የማልነካካ እና በፈርሀ እግዚአብሔር እያሰለጠንኩ እንዳለሁ ሰዎች እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ። ሰው የራሱን ላብ ማግኘት አለበት። እኔ እግዚአብሔር የሰጠኝን ሳልጠቀም የሰውን ገንዘብ በእጅ መንሻ ወደ ኪሴ እንደማላስገባ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። ለምሳሌ ደብረብርሃን ሁለት ዓመት ስቆይ ከላሊበላ ድረስ ሄጄ መልምዬ ተጫዋችን አምጥቼ ነው ማጫውተው። ለዚህ ደግሞ ልጆቹ ምስክር እንደሚሆኑ አልጠራጠርም። ስለ ንፁህነት መስራትን ተቀዳሚ አድርጌ የምሰራ አሰልጣኝ ነኝ። ይሄ ደግሞ በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈለግ አይመስለኝም …(እየሳቀ)። ብዙ የተደበቁ አሰልጣኞች አሉ። እንደውም እኔ ዕድሉን አግኝቼ እያሰለጠንኩ ነው። ከፍተኛ ሊግ ስንቱ ጎበዝ ሆነው ተቀብረው ያሉ አሉ እና ዕውነት ያላቸው ብዙ ስላሉ እግዚአብሔር ያውጣቸው፡፡

“በወጣት ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ሰውነት እና ስዩም የመጠራት ዕድሉ ነበረኝ። ግን መጫወት አልቻልኩም በህመም ምክንያት ተመለስኩ። ጊዮርጊስ ተጫውቶ ብሔራዊ ቡድን አለመጠራት አይቻልም። ግን ጉልበቴ ላይ ህመም ደርሶብኝ ተመልሻለሁ። ጤናማ ሆኜ አጋጣሚው አግኝቼ ቢሆን ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር። በወቅቱ ግን ጊዮርጊስ መግባቴ ራሱ ብሔራዊ ቡድን የመግባት ያህል ነው። የተሰማኝ ህመም ነበረብኝ እንጂ እጫወት ነበር። በጊዮርጊስ ቤት ግን ከነ ሙሉጌታ ከበደ ብዙ ነገር ቀስሜ ከነ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስም ብዙ ነገር መማሬ ለእኔ ጠቅሞኛል ከአሰልጣኝነት ስልጠና በላይ ነበር ለኔ።

“ባለትዳር ነኝ። ከልጅነት ጀምሮ አብራኝ የነበረችን ጓደኛዬን ነው ባለቤቴ ያደረኩት። የሦስት ልጆች አባት ነኝ። የመጀመሪያ ልጄ ኬብሮን እዮብ ይባላል ወደ ሰባት ዓመት ተጠግቷል። ሁለተኛዎቹ ግን መንታ ናቸው የቀደሙኝን በአንዴ ነው የደረስኩት በዶቤ..(እየሳቀ)…ባለቤቴ ፍሬህይወት ታዬ ትባላለች አብረን ነው ከችግር ተነስተን አሁን ላለንበት ደረጃ የበቃነው ፤ እየታገልን ነው አሁንም።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: