ነፃነት ገብረመድህን ወደ ምዓም አናብስት ማምራቱ እርግጥ ሆኗል

ወደ መቐለ 70 እንደርታ ለመዘዋወር በቃል ደረጃ ተስማምቶ የነበረው የስሑል ሽረው ወጣት አማካይ ነፃነት ገብረመድህን ዛሬ በክለቡ ፅሕፈት ቤት በመገኘት የቅድመ ስምምነት ፈፅሟል።

ከስሑል ሽረ ሁለተኛ ቡድን ተገኝቶ ላለፉት ዓመታት ከክለቡ ጋር ቆይታ የነበረው ይህ አማካይ በተቋረጠው የውድድር ዓመት ጥሩ ብቃት ካሳዩ የአማካይ ተጫዋቾች አንዱ ነው። በተለይም በሊጉ መጀመርያ ላይ ደካማ እንቅስቃሴ ላሳየው የቡድኑ የመከላከል ክፍል ሽፋን በመስጠት በቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ጥሩ አስተዋፅኦ የነበረው ይህ ወጣት ተጫዋች በይፋ መቐለን መቀላቀሉ ተከትሎ ለቋሚ ተሰላፊነት ከሙሉጌታ ወልደጊርጊስ ጋር ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በተያያዘ ዜና ላለፉት ሦስት ዓመታት የክለቡን ግብ በብቃት ሲመራ የቆየው ኢኳቶሪያል ጊኒያዊው ፍሊፕ ኦቮኖ ዛሬ በኢትዮጵያዊው ወኪሉ ሳምሶን ናስሮ አማካኝነት ወደ ሀገሩ ክለብ ፉትሮ ኪንግስ ያደረገውን ዝውውር ሙሉ ለሙሉ አጠናቆ በይፋ መቀላቀሉን ተከትሎ ቡድኑ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ወደ ገበያ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ