የአትሌቲክ ቢልባኦ የቴክኒክ ዳይሬክተር ለሃገራችን አሰልጣኞች ስልጠና ሰጡ

በበይነመረብ መቋረጥ ምክንያት ተስተጓጉሎ የነበረው የኦንላይን የአሰልጣኞች ስልጠና ዛሬ ምሽት ቀጥሎ ተከናውኗል።

በኮቪድ-19 ምክንያት ውድድሮች ከተቋረጡ በኋላ የሃገራችን አሰልጣኞች ስልጠናዎችን እና የማነቃቂያ ትምህርቶችን በኦን ላይን (በZoom ቴክኖሎጂ) እየወሰዱ ይገኛሉ። በተለይ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና አሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታሁን በአስተባባሪነት በሚያዘጋጁዋቸው መርሐ ግብሮች የሃገራችን አሰልጣኞች ትምህርቶችች ሲያገኙ ሰንብተዋል። ይሁህ እንጂ በሃገራችን በነበረው የበይነመረብ (ኢንተርኔት) መቋረጥ ስልጠናዎችን በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንዳይከወኑ አድርጎ ነበር። ነገር ግን በዛሬው ዕለት የአትሌቲክ ቢልባኦ የቴክኒክ ዳይሬክተር ጋሪኮትዝ ፉላንዶ (ጋሪ) ለ2 ሰዓታት የቆየ ስልጠና ሰጥተዋል።

አንድ ቡድን በምን ዓይነት መልኩ መገንባት እንደሚችል እና አንድ አሰልጣኝ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ እንዴት ስልጠና መስጠት እንዳለበት በተብራራበት በዚህ መርሃ ግብር ላይ 31 የሃገራችን አሰልጣኞች ትምህርቱን እንደወሰዱ ለማወቅ ተችሏል። ከሃገራችን አሰልጣኞች በተጨማሪ መሃመድ ማጋሱባ (ከማሊ)፣ ማያሲኒ ኬር (ከሴኔጋል)፣ ሚለር ጎሜዝ (ከአንጎላ)፣ ስቴቭ ኮስት (ከደቡብ አፍሪካ) እና ዶክተር ቤልሃሰን ማሉቼ የተባሉ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተሮች በተጋባዥነት ተገኝተው ስልጠናውን ወስደዋል። ኢንስትራክተሮቹ የተጋበዙበት ምክንያትንም አብርሃም መብራቱ ለሶከር ኢትዮጵያ ሲያብራሩ እውቀትን ለአህጉራችን ሃገራትም ለማጋራት በማሰብ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ለ2 ሰዓታት ያክል ከቆየው የገለፃ መርሃ ግብር በኋላ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን እያነሱ ለ30 ደቂቃዎች ያክል ማብሪያዎች እና ውይይቶች መደረጋቸውን ኢንስትራክተር አብርሃም አያይዘው ገልፀዋል።

በዙም አማካኝነት የሚሰጠው ይህ ስልጠና በቀጣይ ሳምንትም እንደሚቀጥል አሰልጣኙ ጠቁመዋል። በተለይ በቀጣይ አርብ ከአሜሪካ እና እንግሊዝ (ቼልሲ) በሚጋበዙ የእግርኳስ ሰዎች ስልጠና ሊሰጥ መታቀዱም ተነግሯል።

ከዚህ በፊት ከኳታር እግርኳስ ፌደሬሽን ጋር በነበረ ግንኙነት የተለያዩ ስልጠናዎች ከብራዚል፣ ኖርዌ፣ ስፔን እና ቤልጄም በተገኙ የእግርኳስ ሰዎች ስልጠናዎች መሰጠቱ አይዘነጋም።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ